የአርባምንጭ ማረሚያ ተቋም የህብረ ብሔራዊነት ማሳያ እና የምርታማ ዜጋ ማፍሪያ ተቋም ነው – ኮሚሽነር ብርቱካን መንግስቱ

የአርባምንጭ ማረሚያ ተቋም የህብረ ብሔራዊነት ማሳያ እና የምርታማ ዜጋ ማፍሪያ ተቋም ነው – ኮሚሽነር ብርቱካን መንግስቱ

ሀዋሳ፡ ጥር 18/05/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የአርባምንጭ ማረሚያ ተቋም የህብረ ብሔራዊነት ማሳያ እና የምርታማ ዜጋ ማፍሪያ ተቋም መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ማረሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ብርቱካን መንግስቱ ገለጹ፡፡
‎
‎በክልሉ ማረሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ብርቱካን መንግስቱ የተመራው ልዑክ በተቋሙ የመስክ ጉብኝት አድርጓል።
‎
‎ማረሚያ ተቋሙ የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት የስራ አፈፃፀም ገምግሟል።
‎
‎የአርባምንጭ ማረሚያ ተቋም ኃላፊ ኮማንደር አለሙ ከኒቶ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ወቅት፥ ከታድሶ ወዲህ ተቋሙ በሚጨበጡ ለውጦች ውስጥ እንደሚገኝ አብራርተዋል ።
‎
‎በተቋሙ የታራሚዎች አገልግሎት ምቹና ጤናማ እንዲሆን መደረጉንና በሰብዓዊ መብት አያያዝና በማረምና ማነፅ ስራ የተሻለ አፈፃፀም መመዝገቡን ጠቁመዋል።
‎
‎ማረሚያ ተቋሙ አነስተኛ መሬትን በመጠቀም በጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ተሰማርቶ ገቢን ለማሳደግ እየተሰራ እንደሚገኝ ያወሱት ኮማንደር አለሙ፥ በቴክኖሎጂ ዘርፍም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ በመሰራቱ ለውጥ በማምጣት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
‎
‎የጋሞ ዞን አስተዳደር ተወካይ አቶ ተስፋፅዮን ዘነበ በበኩላቸው፥ ማረሚያ ተቋማት በሪፎርም እሳቤ በመመራት የዘመነ አሰራር ማስፈን እንደሚጠበቅባቸው አሳስበው፥ ታራሚዎችን ማስተማር፣ መምከርና የስራ እድል መፍጠር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
‎
‎የታራሚዎችን ሁለንተናዊ ችግር መፍታት የሚያስችል መደላድል ከመፍጠር ባሻገር ሰብዓዊ መብቶቻቸውን ለማክበርና ለማስከበር እየተደረገ የሚገኘው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን የገለፁት አቶ ተስፋፅዮን ፥ ተቋሙን ምቹ ለማድረግ ተደጋግፎ መሔድ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።
‎
‎የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ማረሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ብርቱካን መንግስቱ፥ የአርባምንጭ ማረሚያ ተቋም የህብረ ብሔራዊነት ማሳያ ከመሆኑ ባሻገር በማረምና ማነፅ ተግባሩም አበረታች እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
‎
‎በክልሉ ከሚገኙ ማረሚያ ተቋማት ቀዳሚውን የታራሚ ቁጥር ቢይዝም በሙያ ብቁ፣ በስነ-ምግባር የተሻለ፣ በልማት ዘርፍ የተለወጠ ዜጋ እንዲፈራ ባከናወናቸው ተጨባጭ ተግባራት አበረታች ለውጥ ታይቷል ሲሉ አረጋግጠዋል ።
‎
‎በመርሀ-ግብሩ የተቋሙ የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት የስራ አፈፃፀም የቀረበ ሲሆን በዚህም ከማረምና ማነፅ ፣ ሰብዓዊ መብትን ከማስጠበቅ ባሻገር በጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ፣ በአሳ እርባታ በኢትዮ ኮደርስ እንዲሁም በሌሎች የልማት መስኮች የተከናወኑ አበይት ተግባራት በሪፖርቱ ቀርበዋል።
‎
‎በቀረበው ሪፖርት ዙሪያ የተለያዩ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች የተሰነዘሩ ሲሆን ከመድረኩ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።
‎
‎በመጨረሻም ማረሚያ ተቋሙ የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ የተቋሙ ሰራተኞች የማበረታቻ ሽልማት እና ሰርተፊኬት ተበርክቶላቸዋል።
‎
‎አንዳንድ ተሸላሚዎች የተሰጣቸው እውቅና ለቀጣይ ተግባር የሚያነሳሳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡‎
‎
ዘጋቢ፡ ተመኙ ገረሱ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን