በገነት ደጉ
መንግሥት የጤና፣ የትምህርትና ሌሎች የማህበራዊ አገልግሎቶችን ለህዝብ ለማቅረብ በየጊዜው እየጨመረ የሚሄድ ሀብት ይመድባል፡፡ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ እና የባህላዊ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን፣ አንቀጽ 12 (1) እና (2) (መ) አባል ሀገራት ማንኛውም ሰው ሊደረስበት የሚችለውን ከፍተኛውን የአካል እና የአእምሮ ጤና የማግኘት መብትና ዕውቅና ይሰጣሉ።
የዚህን መብት ሙሉ ተፈጻሚነት ለማረጋገጥ አባል ሀገራት የሚወስዷቸው እርምጃዎች በህመም ጊዜ ሁሉንም የህክምና አገልግሎት እና ክትትል አቅርቦት መኖሩን የሚያረጋግጡ ሁኔታዎችን መፍጠርን ይጨምራል።
የሀገራችን ህገ መንግሥት፣ አንቀጽ 41 (4) መንግሥት የጤና፣ የትምህርትና ሌሎች የማህበራዊ አገልግሎቶችን ለህዝብ ለማቅረብ ሀብት እንደሚመድብ ያትታል፡፡
እኛም በሲዳማ ክልል ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ምን እንደሚመስል የክልሉ ጤና ቢሮ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የፕሮግራም ዘርፍ አስተባባሪ አቶ በላይነህ በቀለ የሀገራችን የጤና ፖሊሲ ቅድመ መከላከል ላይ የተመሰረተ የህክምና አገልግሎቶችን ለማህበረሰቡ ፍትሀዊ በሆነ መልኩ እና ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ ማድረግ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በዓለም ጤና ድርጅት የተቀመጠውን ስታንዳርድ መሰረት በማድረግ ለህብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጡ የጤና ተቋማት ምን ያህል ነው? የሚለውን ለማወቅ አካባቢዎችን በመለየት እየተሰራ ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡ ይህን መሠረት በማድረግ በተሰራው ሥራ የሲዳማ ክልል የጤና ተደራሽነቱ ማሳደግ ችሏል፡፡ አሁን ላይ በክልሉ 142 የመንግስት ጤና ጣቢያዎች ለህብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡
የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች በቁጥር 14 ሲሆኑ 7 አጠቃላይ ሆስፒታልና 1 ሪፈራል ሆስፒታል በክልሉ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ይህም ካለው የህዝብ ቁጥር አንፃር በቂ ባለመሆኑ በቀጣይ ስራዎች እንደሚጠብቁ ታሳቢ ተደርጎ እየተሰራ ስለመሆኑ ነው ያነሱት፡፡
ክልል ከመሆኑ በፊት ሁለት ጠቅላላ ሆስፒታሎች የነበሩ ሲሆን አሁን አምስት ተጨማሪ ጠቅላላ ሆስፒታሎች በማስፈለጋቸው የመጀመሪያ ሆስፒታል የነበሩትን አምስት ሆስፒታሎችን ወደ ጠቅላላ ሆስፒታልነት ለማሳደግ ስራዎች ስለመሰራታቸው ነው የጠቀሱት፡፡
ይህም ሲሰራ የሰው ሀይል አስፈላጊ የሆኑ የተቋም መሰረተ ልማትን፣ ተጨማሪ ግንባታዎች፣ እና የአገልግሎት እርካታን ሊጨምሩ የሚችሉ እና ወቅቱን ታሳቢ ያደረጉ ግብዓቶችን ያሟሉ ሆነው እንዲደራጁ እየተደረገ ነው፡፡ በሙያ ስፔሻላዝ ያደረጉ ሀኪሞች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መምጣታቸውን የጠቀሱት አስተባባሪው፡፡
ከዚህ በፊት ህብረተሰቡ ከእሩቅ አካባቢ ተጉዞ የሚያገኘውን የጤና አገልግሎት እዛው በቅርበት እንዲያገኝ የማድረግ ስራዎች ስለመሰራታቸው ጠቁመዋል፡፡ በዚህም ተደራሽነቱ የሰፋ ስለመሆኑ ነው ያስረዱት፡፡
ከዚህም ባሻገር የእናቶችንና የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ ሆስፒታሎችን ተደራሽ ማድርግ የማንችልባቸው አካባቢዎችን በመለየት የቀዶ ህክምና ለመድረግ የሚያስችል ብሎኮችን እዛው ገንብቶ ወደ ስራ የማስገባት ስራዎች ተሰርተው ወደ ተግባር ለመቀየር በቂ ዝግጅት ስለመደረጉም አስረድተዋል፡፡
የህብረተሰቡን የጤና አገልግሎት ፍላጎት ለማሻሻል እና እንግልት ለማስቀረት ስራዎች ስለመሰራታቸው ያስረዱት ምክትል የቢሮ ኃላፊው፣ ህዝቡም ጊዜውንና ጉልበቱን ሳያባክን አገልግሎቱን በቅርበት የሚያገኝበት ዕድል ስለመፈጠሩ ነው የጠቀሱት፡፡
ክልል ከመሆኑ በፊት 64 በመቶ የነበረውን ሽፋን አሁን ላይ በ12 በመቶ በማሳደግ 76 በመቶ ማድረስ መቻሉን አቶ በላይነህ አስታውቀዋል። በዚህም የህዝብ ቁጥሩ በየጊዜው እየጨመረ ከመሄዱ ጋር ተያይዞ በዚያ ልክ መሰረተ ልማቶችን የማስፋት እና ጉድለት ያለበትን በመለየት ለዚያ የሚመጥን ምላሽ የመስጠት ስራዎች ተሰርተዋልም ብለዋል፡፡
ከዚህም ጋር ተያይዞ ተደራሽነት ብቻ ሳይሆን ጥራቱንም ለማስጠበቅ እና የባለሙያን አቅም ከመገንባት አንፃር ከዚህ በፊት ዲፕሎማ ፕሮግራም ብቻ ያሰለጥን የነበረውን የሀዋሳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲግሪንና ስፔሻሊቲን እንዲያሰለጥን ስለመደረጉ ነው ያስረዱት፡፡
በተለይም አሁን ላይ ያለውን የበሽታ ጫና እና እየመጣ ያለውን ችግር ሊቋቋምና ለዚያም የሚመጥን ምላሽ መስጠት የሚችል ባለሙያ የማፍራት ስራዎች እየተሰሩ ስለመሆናቸው ነው የገለፁት፡፡
“እናት ህይወት እየሰጠች ህይወት ማጣት የለባትም” በሚለው መርህ መሰረት፣ ያረጁትን የእናቶች ማቆያዎች ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ በህዝብ ንቅናቄ 95 በመቶ በሚሆኑት ገጠር ባሉት የጤና አጠባበቅ ጣቢያዎች ላይ ግንባታቸው ተጠናቆ እና በግብዓት ተሟልተው ወደ ስራ ስለመግባታቸው ነው ያስረዱት፡፡
ነፍሰጡር እናቶችን በየቀበሌያት በመለየት የእናቶች ፎረም በየጊዜው የሚደረግ ሲሆን ጥራቱን የጠበቀ የቅድመ ወሊድ እንዲኖር ከማድረግ አንፃር እናቶች አገልግሎቱን በጊዜ እንዲጀምሩ የማድረግ ስራ ስለመሰራቱ ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም የአልትራ ሳውንድ ምርምራ ለማድረግ አንድ ሆስፒታል በስሩ አምስትና ከዚያ በላይ የጤና አጠባበቅ ጣቢያዎች ስላሉት ባለሙያው መሳሪያ ይዞ በመውረድ የሚሰራ ሲሆን ችግር ካለ ሪፈር የማድረግና የመከታተል ስራዎች እየተሰሩ ስለመሆናቸው አንስተዋል፡፡
የእናቶች ሞት ቅነሳ በወሊድ ወቅት ብቻ ሳይሆን በወሊድ እና ወልደውም እስከ 42ኛው ቀናቸው ድረስ ክትትል እንደሚደረግ ነው የጠቀሱት፡፡ በዚህም በእናቶች ጤና ላይ በክልሉ ትልቅ ለውጦች እየተመዘገቡ ስለመምጣታቸው ነው የተናገሩት፡፡
የጤና መድህን ስራዎች በተመለከተ እንደ ሀገር 2030 ላይ ሁሉ አቀፍ የሆነ የጤና አግልግሎት ማግኘት የሚቻልበት ስርዓት መፍጠር አለብን በሚል እየተሰራ ሲሆን ሰዎች ከኪሳቸው አውጥተው የሚታከሙበትን ሁኔታ በመቀየር በጤና መድህን መታከም አለባቸው የሚል ስርዓት ስለመፈጠሩ ነው የጠቀሱት፡፡
በአሁኑ ሰዓት የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተግባራዊ እየሆነ ሲሆን እንደ ክልል በ2016ዓ.ም 68 በመቶ የነበረው አፈፃፀም በዚህ ዓመት ወደ 72 በመቶ ለማሳደግ በቀጣይም መቶ ለማድረግ እየተሰራ ስለመሆኑ ጠቁመዋል፡፡
በቢሮው የህክምና አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳምጠው ደንግሶ በበኩላቸው፣ የጤና ሽፋንን ተደራሽ ለማድረግ የአገልግሎት ተደራሽነት እና ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ ስለመሆናቸው ገልፀዋል፡፡ ይህም ተቋማትን ካሉበት ደረጃ ወደ ተሻለ ደረጃ ማሳደግ እና በሌሉባቸው አካባቢዎች ደግሞ የግንባታ ስራዎችን ስለመሰራታቸው ነው የጠቀሱት፡፡
እንደ ክልል ከዚህ በፊት ከነበረው የአገልግሎት አሰጣጥ ሽፋንን ለመጨመር አሁን ላይ 22 ሆስፒታሎች ያሉ ሲሆን 6 የጤና ጣቢያዎች ግንባታ እና ጥገና እየተደረገ ስለመሆኑ ነው ያስረዱት፡፡
በዚህም አገልግሎቱን ተደራሽና ጥራት ያለው ለማድረግ የጤና ጣቢያዎችን ደረጃ በማሻሻል ወደ ኮንፐሬንሲቭ ለማሳደግ እየተሰራ ስለመሆኑ ነው የጠቆሙት፡፡
ከዚህ ቀደም በጤና ጣቢያዎች የውሃ ችግር ያለ ሲሆን አሁን ላይ ግን ወደ ዘጠኝ የሚሆኑ ጤና ጣቢያዎች ከውሃ ችግር ነፃ በመሆን ጥራት ያለውን አገልግሎት እየሰጡ ስለመሆናቸው ነው ያስታወሱት፡፡
አገልሎቱንም ለህብረተሰቡ ምቹ ለማድረግ ከዚህ በፊት ያልነበሩ አገልግሎቶች እየተሰጡ ቢሆንም ቀሪ ስራዎች እንዳሉ ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በተለይም በጤና ጣቢያዎች መለስተኛ የቀዶ ህክምና የሚሰጥባቸው ብሎኮችን በመገንባትና አገልግሎቱን በማስጀመር ህብረተሰቡ ከእንግልትና ከአካባቢያቸው ሳይርቁ የጤና አገልግሎቱን እንዲያገኙ የማድረግ ስራዎች ስለመሰራታቸው ነው የገለፁት፡፡
የተቋማት ግንባታ ብቻውን አገልግሎቱን ሙሉ እንደማያደርግ የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፣ የሰው ሀይል የማሻሻል እንዲሁም የመድሀኒት እና የህክምና መገልገያ ግብዓት አቅርቦት የማሻሻል ስራዎች እየተሰሩ ስለመሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ከዚህም ባሻገር ተቋማትን ድጋፍና ክትትል እያደረጉ ማብቃት ለአገልግሎቱ ወሳኝ በመሆኑ ውጤታማነቱን እየገመገሙና እያበቁ ስለመሆኑ ነው የገለፁት፡፡
መንግስት የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህንና የህክምና ተቋማት ግንባታ እንዲሁም የጤና ባለሙያዎች ስልጠና ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል፡፡ በዚህም ሁለንተናዊ የጤና ሽፋንን ለማሳካት ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት፣ ማህበረሰቡን ማንቃትና ማብቃት እንዲሁም ጤናን በሁሉም ፖሊሲ ማካተት ወሳኝ ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡
በቅርቡ የተከለሰው የሀገራችን የጤና ፖሊሲ በሽታ ቅድመ መከላከል ላይ ያተኮረ ጥራቱን የጠበቀ የህክምና አገልግሎት በመስጠትና የማይበገር የጤና ስርዓት በመገንባት ሁሉ አቀፍ የጤና ሽፋን ማሳደግን ዓላማ ያደረገ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋንን ለማሳደግ በ2016 በጀት ዓመት በቤተሰብ እቅድ፣ የእናቶችና አፍላ ወጣቶች ጤና፣ በቲቢና ኤች.አይቪ/ኤድስ ፕሮግራም፣ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መከላከልና የጤና መድህን ሽፋን የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ገልፀዋል።
የጤና ሴክተር ስራዎችን በተቋሙ ብቻ በመስራት ውጤታማ ማድረግ እንደማይቻል አንስተው የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ ቅድመ መከላከሉ ላይ ትኩረት ማድረግ አለባቸው ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
More Stories
“መታመሜን ነግሬያችሁ ነበር”
“ዓላማን ማሳካት የግል ጥረትን ይጠይቃል” – አቶ መንግስቱ ዘውዴ
“ዋናው በፅናት ዝቅ ብሎ መሥራት ነው” – ወ/ሮ ዘሪቱ ጨነቀ