“ዓላማን ማሳካት የግል ጥረትን ይጠይቃል” – አቶ መንግስቱ ዘውዴ

“ዓላማን ማሳካት የግል ጥረትን ይጠይቃል” – አቶ መንግስቱ ዘውዴ

በአለምሸት ግርማ

በተለያዩ ሙያዎች የተሰማሩ ሰዎችን የኋላ ታሪክ ስንመለከት መነሻቸው የተለያየ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ስራውን በምንም ይጀምሩት በምን ዋናው ጉዳይ በተሰማሩበት ዘርፍ ምን ያህል ስኬታማ ሆነውበታል? የሚለው ነው። የዛሬው ባለታሪካችን የልጅነት ህልማቸው ሌላ ቢሆንም በአጋጣሚ በገቡበት ሙያ ተወዳጅነትን ከማትረፋቸው በላይ ለብዙ ወጣቶች የስራ ዕድል መክፈት የቻሉ ባለሙያ ናቸው።

አቶ መንግስቱ ዘውዴ ይባላሉ፤ ለቤተሰባቸው የመጀመሪያ ልጅ ናቸው። ተወልደው ያደጉት አርሲ ነጌሌ የገጠር መንደር ውስጥ ነው። ከቆይታ በኋላ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ወደ ዱራሜ ከተማ የሚሄዱበት አጋጣሚ ተፈጠረ። ኑሯቸውንም በዚያው አደረጉ። ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ እዚያው ዱራሜ ከተማ በሚገኝ ትምህርት ቤት ተከታትለው እስከ 12ኛ ክፍል ተምረው አጠናቀዋል።

በልጅነታቸው እንደአብዛኛው ልጅ ሀኪም የመሆን ህልም ነበራቸው። ሆኖም ወላጅ አባታቸው በሞት በመለየታቸው ምክንያት ያለሙትን ለማሳካት አልቻሉም። ይልቁንም እንደመጀመሪያ ልጅ ቤተሰቡን በሚችሉት የማገዝ ኃላፊነት በእሳቸው ላይ ወደቀ።

12ኛ ክፍልን እንዳጠናቀቁ ከዕለታት በአንዱ ቀን ከጓደኞቻቸው ጋር ፀጉር ቤት ተቀምጠው ባሉበት አንድ ሃሳብ ወደልባቸው መጣ። የፀጉር ቆራጩ እንቅስቃሴ ትኩረታቸውን ሳበው፡፡ የጓደኞቻቸውን ጨዋታ ችላ ብለው የፀጉር ቆራጩን እጅ መከታተል ጀመሩ። በዚያው ሙያውን ለማወቅ ያላቸው ጉጉት ጨመረ። ከዚያን ዕለት ጀምሮ በሙያው ለመሰማራት ፍላጎት አደረባቸው። በዚያው ከሰዎቹ ጋር ተነጋግረው መለማመድ ጀመሩ። ከፍተኛ ፍላጎት ስላደረባቸው ሙያውን ለመልመድ ጊዜ አልወሰደባቸውም። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሰዎችን ማስተካከል ጀመሩ። በዚያም የራሳቸውን ገቢ ማግኘት ጀመሩ።

ከዚያም ወደ ሃዋሳ ከተማ በመምጣት በሙያው ተቀጥረው በመስራት ከሚያገኙት ገቢ ታናናሾቻቸውን ማገዝና እናታቸውን መደገፍ ቋሚ ተግባራቸው ሆነ። ስለራሳቸው ሲናገሩ፦

”ተቀጥሬ ስሰራ ሁሌም የማስበው ራሴን ስለመቻል ነበር። ያም ረጅም ጊዜ ወስዶብኛል። ዓላማን ማሳካት ከባድ የሆነ የግል ጥረትን ይጠይቃል” ይላሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት በሃዋሳ አሉ ከሚባሉ የወንዶች ፀጉር ቤቶች ውስጥ የአቶ መንግስቱ (አባይ የወንዶች ፀጉር ቤት) አንዱ ነው። ይሄ ዕውቅና በቀላሉ የመጣ እንዳልሆነ ይናገራሉ። ለሃያ ዓመታት ያህል በሰው ቤት ተቀጥረው ሰርተዋል። በቆይታቸው ሙያቸውንም ማዳበር ችለዋል። ከዚያም በመቀጠል በማህበር በመደራጀት ወደ ስራ ገብተዋል። እንዲሁም ከሰዎች ጋር አብሮ የመስራትን ልምድ አግኝተዋል። ከቆይታ በኋላ ማህበሩ ሲበተን ሁሉም ወደሚፈልገው ሙያ ሲሰማራ እሳቸውም የራሳቸውን ፀጉር ቤት በመክፈት ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ የፀጉር ቤት ባለቤት ለመሆን በቅተዋል።

ከሃዋሳ በተጨማሪ ቁጥር ሁለት ደግሞ መቂ ከተማ አላቸው። ይሄ ሁሉ የተገኘው ዓላማቸውን ለማሳካት ባደረጉት ጥረት መሆኑን ይናገራሉ። በሃዋሳ ከተማ ባለው ፀጉር ቤት ከራሳቸው ውጪ ለስድስት ሰዎች፤ እንዲሁም መቂ በሚገኘው ደግሞ ፅዳትና ጥበቃ ሳይጨምር ለአምስት ሰዎች የስራ ዕድል መፍጠር ችለዋል።

እሳቸው በዋናነት እዚህ ሃዋሳ በሚገኘው የሚሰሩ ሲሆን፤ መቂ ደግሞ እየተመላለሱ እንደሚከታተሉና የሚያስፈልገውን ነገር እንደሚያሟሉ ነው ያጫወቱን።

“ልጅ ሆኜ መሆን የምፈልገውን ለመሆን ባልችልም እግዚአብሔር ረድቶኝ ብዙ ፈተናዎችን አልፌ አሁን ያለሁበት ደረጃ ደርሻለሁ። አንዱን እያስደሰትኩ ሌላውን እያስከፋሁ የጀመርኩት ሙያ ዛሬ ላይ ተፈላጊ ባለሙያ ሆኜበታለሁ። አዕምሮዬ ውስጥ ከነበረው ህልም ወደ ሌላ ሙያ ያመጣኝ እግዚአብሔር በዓላማ ነው” ሲሉም ያለፉበትን መንገድ ያወሳሉ፡፡

ወደ ትዳር የገቡት ሰው ቤት ተቀጥረው እየሰሩ በነበረበት ወቅት ነው። አሁን የሶስት ልጆች አባት ሆነዋል። ባለቤታቸው በንግድ ስራ ውስጥ መሰማራታቸውንም አጫውተውናል።

እሳቸው ጋር የሚሰሩ ባለሙያዎች በስራቸው ደስተኛ መሆናቸውንም ይናገራሉ። ለሰራተኞችም ሆነ ለደንበኞች ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ያምናሉ። በተለይም ደንበኞች የሚፈልጉትን አገልግሎት ካገኙ ደንበኛ ሆነው እንደሚቀሩ በልበ ሙሉነት ነው የሚናገሩት።

ስኬት በቀላሉ እንደማይመጣም እንዲህ በማለት ያስረዳሉ፦

“ስኬት በፍላጎት ብቻ አይገኝም። በስራ ህይወቴ ውስጥ ዛሬ የደረስኩበት ለመድረስ ብዙ መሰናክሎችን አልፌያለሁ። በተለይም በ2010 ዓ.ም የምሰራበት ኮንቲነር ሲፈረስብኝ ቤቱን ለማደራጀት ያወጣሁትን ወጪ እንኳን ሳይሸፍን በመሆኑ ለኪሳራ ተዳርጌያለሁ። በዚያም በጣም አዝኜ ነበር። ክስተቱ ሙያውን እስከመጥላት ስላደረሰኝ መቼም አልረሳውም ብዬ ነበር። ሆኖም ተስፋ ሳልቆርጥ በመስራቴ የተሻለ ደረጃ መድረስ ችያለሁ።

“ሙያው በባህሪው በየጊዜው እያደገ የሚሔድ ነው። ድሮ በመቀስ ሲቆረጥ ነበር። የተለያዩ ሒደቶችን አልፎ ዛሬ ላይ የተለያዩ ማሽኖችን በመጠቀም አገልግሎቱ እየተሰጠ ነው። እኛም ጊዜው የደረሰበትን አገልግሎት ለደንበኞቻችን በመስጠት ላይ እንገኛለን። ለፀጉር ውበትና እንክብካቤ የተዘጋጁ እንዲሁም፤ ለፊት ውበትም ጭምር የሚጠቅሙ አገልግሎቶችን በፀጉር ቤታችን እንሰጣለን።”

ቀጣይ እቅድዎ ምንድ ነው? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል፦

“ወደፊት ከወንዶች በተጨማሪ የሴቶች የውበት ሳሎን የመክፈት ዕቅድ አለኝ። እንዲሁም የወንዶችና የሴቶች የፀጉር ሙያ ማሰልጠኛ ለመክፈትም እንዲሁ አስባለሁ”።

ሥራቸውን አክባሪ እንደሆኑና ጥራት ያለው አገልግሎት እንደሚሰጡ ደንበኞቻቸው ይመሰክራሉ። ለስራ ያላቸው አቋም ጠንካራ መሆኑን እኛም ከንግግራቸው መታዘብ ችለናል። ስራቸውን በጥንቃቄ ነው የሚያከናውኑት። የደንበኞቻቸው ምስክርነትም ይህንኑ ነው ያረጋገጠልን።

“ስራ የለም የሚል ዕሳቤ የለኝም። መስራት ለሚፈልግ ስራ አለ። ዋናው ነገር ለተፈጠርንለት ስራ መትጋት ነው። በተለይም በዚህ ወቅት ስራ መፍጠር ያስፈልጋል። እኔ ስማር መሆን የምፈልገውን አልሆንኩም። የደረስኩበትን ነው እየሰራሁ ያለሁት። ነገር ግን አሁን ጥሩ ቦታ ላይ ነኝ። በስራዬ ደስተኛ ስለሆንኩ ሙያዬን እወደዋለሁ።

“ዛሬ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ሊስትሮ የሚሰሩ ሰዎችን እየተመለከትን ነው። ስራ ራሳችን እንፈጥራለን እንጂ ሌሎች እስኪሰጡን መጠበቅ የለብንም። ምናልባት ወጣቶች ተማሪ ሆነው መሆን የሚፈልጉትን ነገር በተለያየ ምክንያት ላያገኙ ይችላሉ። የሚፈልጉትን መሆን አለመቻል ደግሞ የብዙ ወጣቶች ፈተና ነው። ነገር ግን እንደዚህ ዓይነት ችግር ሲገጥም ሌላ አማራጭ መፈለግ ነው እንጂ ተስፋ ቆርጦ መቀመጥ ተገቢ አይደለም። ወጣቶች ከዚህ ሊማሩበት ይገባል።” ሲሉም ይመክራሉ፡፡

አቶ መንግስቱ እናታቸውንና ታናናሾቻቸውን የማገዝ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት የቻሉት ስራቸውን አክብረው በመስራታቸው ነው። ስራን ሳይንቁና ሳይመርጡ መስራት ለውጤት እንደሚያበቃ ጥሩ ማሳያ ናቸው። ሶስት ወንድሞቻቸውና አራት እህቶቻቸው ዛሬ ለቁም ነገር በቅተዋል።

እሳቸውም “በዚህ ሁሉ የህይወት ፈተና ውስጥ እግዚአብሔር በብዙ ረድቶናል። ከቤተሰቦቼ ጋር ተጋግዘን ፈተናዎቻችንን ማለፍ ችለናል። ይሔም ትልቅ ስኬት ነው” ይላሉ፡፡

ለደረሱበት ስኬት የብዙዎች ድጋፍ እንዳለም አልሸሸጉም። በተለይም በሃዋሳ ከተማ በማህበር ተደራጅተው በሚሰሩበት እና በግል ስራ በሚጀመሩበት ወቅት ከክፍለ ከተማ ጀምሮ የነበሩ አመራሮችን እንዲሁም በብዙ ሲደግፏቸው የነበሩ ጓደኞቻቸውን ምስጋናዬ ይድረሳችሁ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡