ህብረተሰቡ የኤሌክትሪክ መስመሮችን ጨምሮ ለእሳት አደጋ መንስኤ የሚሆኑ የመጠቀሚያ ዕቃዎችን በጥንቃቄ በመጠቀም በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት መከላከል እንደሚገባ ተገለጸ
በሆሳዕና ከተማ ሰኔ 11/2018 ዓ.ም እኩለ ሌሊት 7 ሰዓት ገደማ በሴች ዱና ቀበሌ በንግድ አገልግሎት ተቋማት በተከሰተ የእሳት አደጋ ከ20 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙን በሆሳዕና ከተማ አስተዳደር የሴች ዱና ቀበሌ ፖሊስ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
በአደጋው በሰው ህይወት ላይ የደረሰ አደጋ እንደሌለ ተገልጿል።
በሆሳዕና ከተማ አስተዳደር የሴች ዱና ቀበሌ ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኢንስፔክተር ዳንኤል ጡምደዶ አደጋውን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፤ በከተማው በሴች ዱና ቀበሌ መንደር አራት ምሽት 7 ሰዓት ገደማ አደጋ መድረሱን ጠቁመው አደጋው ከዚህ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ በተደረገው ርብርብ እሳቱን ማጥፋት መቻሉን ገልጸዋል።
አደጋው ከተከሰተ በኋላ ከአካባቢው ነዋሪዎች፣ ከከተማ አስተዳደር ባለድርሻ አካላትና የእሳት አደጋ ማጥፊያ መኪናዎች ጋር በቅንጅት በመሰራቱ እሳቱን ለመቆጣጠር መቻሉን ገልጸዋል።
በአደጋው የአራት ንግድ ተቋማትና የአከራዩ ንብረት ብር ሲተመን 20 ሚሊየን 3 መቶ ሺህ ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን ምክትል ኢንስፔክተር ዳንኤል ገልጸው የአደጋው መንስኤ እየተጣራ መሆኑን አክለዋል።
በአደጋው ንብረት የወደመባቸው ተጓጂዎች በበኩላቸው የንግድ አገልግሎት እቃዎች፣ ሸቀጣሸቀጥና ገንዘብ ጭምር ሙሉ በሙሉ በእሳት መውደሙን ተናግረዋል።
በሰዓቱ የእሳት አደጋ መኪናዎች ደርሰው እሳቱን እንዳጠፉ ገልጸው መኪናዎቹ አደጋዎች ከመከሰታቸው በፊት ተዘጋጅተው በመቀመጥ በፍጥነት መድረስ እንዳለባቸውም ጠይቀዋል።
የህብረተሰቡ ድጋፍና ትብብር ከፍተኛ እንደነበርም ተጓጂዎቹ አንስተዋል።
በሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጽህፈት ቤት የማስፈፀም አቅም ግንባታና የመሰረተ ልማት ዘርፍ ኃላፊ እና ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ አብነት አባቢያ በበኩላቸው፤ የአደጋው ጥቆማ ከደረሰ በኋላ የእሳት አደጋ ማጥፊያ አገልግሎት የሚሰጡ መኪናዎች ፈጥነው እንዲደርሱ ጥረት መደረጉን ገልፀዋል።
የእሳት አደጋ ማጥፊያ መኪናዎች ምሽት ጭምር አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ በመሆናቸው መሰል አደጋዎች ሲከሰቱ ህብረተሰቡ ለፖሊስ ተቋማትና ለባለድርሻ አካላት በፍጥነት መረጃ መስጠት እንዳለበትም አቶ አብነት አሳስበዋል።
በከተማው በዚህ ሰሞን ሁለት ተመሳሳይ አደጋዎች መከሰታቸውን የጠቆሙት ኃላፊዎቹ ህብረተሰቡ የኤሌክትሪክ መስመሮችን ጨምሮ ለእሳት አደጋ መንስኤ የሚሆኑ የመጠቀሚያ ዕቃዎችን በጥንቃቄ በመጠቀም በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት መከላከል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፡ ኤርጡሜ ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሆሳዕና ከተማ ሰኔ 11 ቀን 2018 ዓ.ም በተከሰተው ድንገተኛ የእሳት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ተደረገ
በሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) የተመራል ኡክ በወላይታሶዶ ዩኒቨርሲ ቲየባዮ ጋዝ ማምረቻ ፕሮጀክትን የስራ እንቅስቃሴ ምልከታ አደረገ
የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለሕብረተሰቡ ግንዛቤን ከመፍጠር ጀምሮ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል – የሺንሽቾ ከተማ አስተዳደር ጤና ጽህፈት ቤት