በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሆሳዕና ከተማ ሰኔ 11 ቀን 2018 ዓ.ም በተከሰተው ድንገተኛ የእሳት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ተደረገ
የሀዲያ ዞን ቀይ መስቀል ቅርንጫፍ ከሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ጋር በመሆን ለተጎጂዎቹ መሠረታዊ የቤት ቁሳቁስ እና ጊዜያዊ መጠለያ ድጋፍ አድርጓል።
በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የሀዲያ ዞን ቀይ መስቀል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድሙ አበራ፤ በሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ሰኔ 11 ቀን 2018 ዓ.ም ከለሊቱ 7 ሰዓት በደረሰው ድንገተኛ የእሳት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ቤተሰቦች የመሠረታዊ ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።
በጊዜያዊነት የሌሊት ልብስ፣ መሰረታዊ የቤት ቁሳቁስና የወለል ንጣፍ ድጋፍ እንደተደረገ የገለጹት አቶ ወንድሙ፤ በቀጣይም የማቋቋም ስራዎች እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
ተጎጂዎችን ለመደገፍ ከመንግስት እና ሰብአዊ ድርጅቶች በተጨማሪ ማህበረሰቡ ያለው ሚና ጉልህ መሆኑን በመግለጽ አደጋው የደረሰባቸው ግለሰቦች በዘላቂነት እስኪቋቋሙ የተለመደው ድጋፉን እንዲቀጥል አስገንዝበዋል።
አክለውም ለመሠል አደጋዎች አጋላጭ ነገሮችን በመገንዘብ ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በድጋፉ ወቅት የተገኙት በሆሳዕና ከተማ አስተዳደር የሴችዱና ቀበሌ ሰላምና ጸጥታ ሀላፊ አቶ አለሙ ጂርጋ፤ በአደጋው በሰው ህይወት ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንዳልደረሰ በመግለጽ ንብረት ለወደመባቸው ቤተሰቦች የከተማ አስተዳድሩ ለጊዜያዊ መጠለያ የሚሆን የ3 ወር የቤት ኪራይ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
በቀጣይም ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደረግ የገለጹት አቶ አለሙ፤ ማህበረሰቡ ተጎጂዎችን ለመደገፍ የጀመረውን በጎ ተግባር አጠናክሮ እንዲያስቀጥል ጠይቀዋል።
ጉዳቱ የደረሰባቸው እና ድጋፍ የተደረገላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችም ለተደረገላቸው ድጋፍ የሆሳዕና ከተማ አስተዳደሩን እና የቀይ መስቀል ማህበርን እንዲሁም ማህበረሰቡን አመስግነዋል።
የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሽጉጤን ጨምሮ የከተማው አመራሮች እና ባለድርሻ አካላት በስፍራው ተገኝተው ጉብኝት ማድረጋቸውም ተገልጿል ።
ዘጋቢ፡ ኤደን ተረፈ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
በከምባታ ዞን ሺንሽቾ ከተማ አስተዳደር የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ስርአት (E-LMIS) ምዝገባ በይፋ መጀመሩን የከተማው ኢንተርፕራይዝና ሥራ ዕድል ፈጠራ ጽህፈት ቤት አስታወቀ
ህብረተሰቡ የኤሌክትሪክ መስመሮችን ጨምሮ ለእሳት አደጋ መንስኤ የሚሆኑ የመጠቀሚያ ዕቃዎችን በጥንቃቄ በመጠቀም በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት መከላከል እንደሚገባ ተገለጸ
በሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) የተመራል ኡክ በወላይታሶዶ ዩኒቨርሲ ቲየባዮ ጋዝ ማምረቻ ፕሮጀክትን የስራ እንቅስቃሴ ምልከታ አደረገ