“ዋናው በፅናት ዝቅ ብሎ መሥራት ነው” – ወ/ሮ ዘሪቱ ጨነቀ

በጋዜጣው ሪፖርተር                                       

በግብርናው ዘርፍ ሁሉ ነገራቸውን ሰጥተው ለ19 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በዚህ ወቅት ረጅም ርቀት በእግር ተጉዘው ይሰሩ ነበር፡፡ ራሳቸው እየቀለጡ ለሌላው ብርሃን ሆነዋል፡፡ በሥራቸው ታታሪ ነበሩ፡፡ ሥራቸው አርሶ አደሮችን የማጀራጀት፣ የማብቃት እና ግብዓት የማቅረብና የመሳሰሉ ተግባራትን በማከናወን አርሶ አደሩን በሙያቸው መደገፍ ነበር፡፡ 

በአንድ ወቅት ውሃ ለማቆር ተብሎ 17 ሜትር ጥልቅ ጉድጓድ ተቆፍሮ ነበር፡፡ ገብተው ናሙና ሲያሳዩ መውለጃ ጊዜያቸው ተቃርቦ ነበርና ያላሰቡት ነገር ተፈጠረ፡፡ ሃኪም ቤትም ሳይደርሱ ወለዱ፡፡ ይሁን እንጂ ልጁ ሆዳቸው ውስጥ ታፍኖ ስለነበር ብዙም ሳይቆይ ሞተባቸው፡፡

በዚህም የተነሳ የመስክ ሥራ ለማቆም ወሰኑ። ወደ ቢሮ እንዲመልሷቸው ለመስሪያ ቤታቸው ማመልከቻ ቢያስገቡም ጽ/ቤቱ ግን ሊቀበላቸው አልቻለም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ መስክ ላይ የሚታይ ጥሩ ሥራ ይሰሩ ስለነበር ክፍተት ይፈጠራል የሚል ነበር፡፡ ምንም እንኳን የሚሰሩበት የቀበሌ ህዝብም ታታሪዋ ዘሪቱ ከሥራው ከተነሳች ለእኛ የሚጠቅመን ሌላ ሰው አይመጣም በሚል እንዲቆዩላቸው ይጠይቁ ነበር፡፡

ሁልጊዜ ከክልል ለሚመጡ አካላት የመስክ ሪፖርት የሚያቀርቡት እሳቸው ስለነበር መስሪያ ቤታቸው ትንሽ ቆዪ የሚል ምላሽ በመስጠት እንዲታገሱ ያስገድዳቸው ነበር፡፡ ምንም እንኳን ታግሰው ቢቆዩም ምላሽ ባለማግኘታቸው ሥራቸውን ለማቆም ተገደዱ፡፡

ይሁን እንጂ ሥራ ለቀኩ ብለው እጃቸውን አጣጥፈው ቁጭ አላሉም፡፡ “ችግር ብልሃትን ይወልዳል” እንዲሉ፤ ኑሯቸውን ለማሸነፍ ያገኙትን ሥራ ለመሥራት ወሰኑ፡፡ ምንም ዓይነት ሥራ ሳይመርጡ ራሳቸውን ዝቅ አድረገው መሥራትም ጀመሩ፡፡ ብዙ ዓይነት የሥራ አማራጮችን ቀያይረው ሞክረዋል፡፡ የሥራቸው መነሻ እንደ ሽሮ ያሉ ቶሎ የሚደርሱ ምግቦችን ለሰልባጅ ነጋዴዎች ሠርተው መሸጥ ነበር፡፡ 

እኚህ ብርቱ ወይዘሮ ዘሪቱ ጨነቀ ይባላሉ። ተወልደው ያደጉት በቡርጂ ዞን ቢሆንም ትምህርታቸውን የተማሩት በጋርዱላ ዞን ጊዶሌ 1ኛ እና 2ተኛ ደረጃ  ትምህርት ቤት  ነው፡፡ ከዚያም ወደ ወላይታ አቅንተው ዋዱ ግብርና ኮሌጅ በእንስሳት እርባታ (animal science) ትምህርት ክፍል ትምህርታቸውን ተከታትለው በሰርተፍኬት ተመርቀዋል፡፡ በድጋሚ በእንስሳት እርባታ ከዲላ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋም ዲፕሎማ አግኝተዋል፡፡ ቀጥሎም ኑሯቸውን ሃዋሳ ካደረጉ በኋላ ሀዋሳ ፋርማ ኮሌጅ በመግባት በድግሪ ፕሮግራም በቢዝነስ ማኔጅመንት ተመርቀዋል፡፡

ሕይወት መንገዷ ብዙ ነውና ዋጋ የከፈሉለትን ሙያ ትተው ዛሬ ሃዋሳ ላይ የራሳቸውን ሱፐርማርኬት ከፍተው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡

ወደ ንግድ ዓላም እንዴት እንደገቡ ላነሳንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፡- “ሥራ ለመሥራት  ዋናው  አምኖ መግባት ነው፡፡ የቢሮ ሠራተኛ አለባበሱን አሳምሮ ነው የሚሠራው፡፡ የለበሰውን ጥሩ ልብስ ጥሎ ሻይ ቡና መሥራት ማለት ከባድ ነው፡፡ እኔ ግን ስራ የጀመርኩት አሳንቡሳና ቆቀር ጠብሶ በመሸጥ ነበር፡፡

“ይህን ያዩ የሥራ ባልደረቦቼ በመንገድ ሲያልፉ ይስቁብኝ ነበር፡፡ ድንች፣ አሳንቡሳና ቆቀር ስጠብስ ይህቺ ሴትዮ አበደች እንዴ ይሉ ነበር፡፡ ሥራውን ጀምሬ ውጤታማ መሆኑን ሳውቅ መንግስት ቤት የሰራሁባቸው 19 ዓመታት የተጎዳሁበት ነው ወደማለት ደርሻለሁ፡፡ ለዚህም ነው ፈጣሪ በራሱ ሰዓት አስጨከነኝ የምለው” ሲሉ ያለፉበትን መንገድ ይናገራሉ፡፡

“ሻይ ቡናውን በደንብ እንሠራ ነበር፡፡ ልጆቼም ከፍ እያሉ ሲመጡ አሳንቡሳና ቆቀር በመጥበስ ይረዱኝ ነበር፡፡ እኔም አጋዥ ሳገኝ ድፎ ዳቦ እና አንባሻ መጋገር ጀመርኩኝ፡፡ በዚህም የማገኘውን ገንዘብ እቁብ እየጣልኩ ተጠረቃቅሞ ሲመጣ ሻይ ቤቱን ወደ ካፌ ደረጃ አሳደኩት። ካፌውን ለ7 ዓመታት ከሠራሁ በኋላ ደግሞ ወደ ኮስሞቲክስ ሥራ ገባሁ፡፡ ልጆቼም እየተማሩ የራሳቸውን ሥራ መሥራት ጀመሩ፡፡ 

“ከዚህም አለፍ ሲል የፎቶ ካሜራ ገዝቼላቸው ስቱዲዮ ተከራይተው ይሰሩ ነበር፡፡ ከዚያም ለመጀመሪያ ልጄ ከእኔ ጋር ዋጋ ከፍሎ ስለሠራ በስሙ የጭነት መኪና ገዛሁለትና ራሱን እንዲችል አደረኩ” ሲሉ በተሰማሩባቸው የሥራ ዘርፎች ስላገኙት ጥቅም ያስረዳሉ፡፡

በአንድ ሥራ ላይ ውጤት አይመጣም የሚል እምነት አላቸው፡፡ አዋጭ ነው ያሉትን ሥራ በድፍረት ይሞክራሉ፡፡ በመጨረሻም ትልቅ አስቤዛ ቤት ከፈቱ፡፡ ሥራቸው በአጭር ጊዜ ውጤታማ እንደሆነ በኩራት ይናገራሉ፡፡

ወ/ሮ ዘሪቱ ወደ ትዳር ዓለም የገቡት 12ተኛ ክፍል ተማሪ እያሉ ነበር፡፡ በትዳር ቆይታቸው 4 ወንድ ልጆችን አፍርተዋል፡፡ የመጀመሪያ ልጃቸው በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ በምህንድስና ትምህርት ክፍል በድግሪ ተመርቋል፡፡

ሁለተኛ ልጃቸውም እንደዚሁ በደንቢዶሎ ዩኒቨርስቲ በጤና መኮንንነት (HO) በድግሪ ተመርቋል፡፡ የተቀሩት ሁለት ልጆቻቸው የ8ተኛ እና 4ተኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው፡፡ ባለቤታቸው አሁንም ቡርጂ ዞን ሲቪል ሰርቪስ ባለሙያ ሆነው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡

እኚህ መለኛ እናት ሰዎች በዚህ ዘመን እንደዚህ አይነት ልጆች አሉ እስኪሉ ድረስ ልጆቻቸውን  አንፀው ማሳደጋቸውን ይናገራሉ። ገና በልጅነታቸው ለቤተሰብ ከመታዘዝ ባለፈ ቤተሰባቸውን ለማገዝ ሰፈር ላይ ሱቅ ተከራይተው ገቢ ለማምጣት ይሞክሩ ነበር፡፡

“ልጆቻችን የእኛን ከእጅ ወደ አፍ የነበረ ኑሮ ለማገዝ በልጅ አዕምሯቸው ይጥሩ ነበር። ያገኙትን ሳንቲም ይሠጡኝ ነበር፡፡ አባታቸው ሀዋሳ መምህራን ኮሌጅ ሲማር አጠራቅመው ልብስ ገዝተውለት ያውቃሉ” ሲሉም ገጠመኛቸውን አጋርተውናል፡፡

“ምንም እንኳን ልጆቼ የመንግስት ገጠር ትምህርት ቤት ቢማሩም፤ በትምህርታቸው በጣም ጎበዝ እና ተሸላሚ ተማሪ ነበሩ። በዩኒቨርስቲ ቆይታቸውም ሰቃይ ነበሩ፡፡ በተለይ ሁለተኛው ልጄ ዩኒቨርስቲው በውጤቱ አስቀርቶት ነበር፤ ግን አልፈልግም ብሎ መጣ፡፡ የእኔን ድካም አይተው ስላደገ ከእኔ ጋር መስራትን ምርጫቸው አድርገዋል” በማለት ስለልጆቻው መልካምነት ሲያወጉን ፍፁም በደስታ ስሜት ሆነው ነበር፡፡

እንዳው የልጆችዎ መልካም ባህሪ የመያዛቸው ሚስጥር ምንድ ነው? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፡-

“ዋናው ነገር የፈጣሪ ስጦታ ነው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ የእናትና የአባት ሚና ነው፡፡ ባለቤቴ መልካም ሰው ነው፡፡ ደመወዙ የነበረው 272 ብር ከ30 ሣንቲም ነበር፡፡ ለትምህርት ሀዋሳ ሲሄድ እንኳን ምንም ሳያስቀር ከነሣንቲም ቤቱ ይሰጠኝ ነበር፡፡

“ከደመወዝ ውጪም ሲያገኝ አንድም ሳያስቀር ይሠጠኛል፡፡ ለኪሱ ሳይሳሳ ለልጆቹ ቅድሚያ በመስጠት ያስባል፡፡ አባታቸው ጠንካራ መምህርም ስለነበር በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ያስጠናቸዋል፡፡ ባህሪያቸውን ለመቅረፅ የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡” ሲሉ ስለባለቤታቸው ትጋት ይመሰክራሉ፡፡

“በሌላ በኩል የእኛ መተሳሰብ ለልጆቻችን ስኬት መሠረት ሆኗል፡፡ የእኔ ድርሻ የነበረው በትምህርታቸው ጎበዝ እንዲሆኑ እና ፈጣሪያቸውን እንዳይዘነጉ በየጊዜው እመክራቸው ነበር፡፡ ቅዳሜ እና እሁድ ሲሆን ደግሞ ለእነሱ ጊዜ እንሰጣለን” ሲሉ ልጆቻቸው ያደጉበትን መንገድ አጋርተውናል፡፡

አሁን ባለንበት ዘመን እንዲህ ባለ ሥነ-ምግባር ልጆችን ቀርጾ ማሳደግ ጥቅሙ ለራስ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል ልጆቻቸው ከቤተሰብ በወረሱት መልካምነት መልሰው እነሱን ለመጦር የሚጥሩት፡፡

ዛሬ ላይ ቤተሰቦቻቸው የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ ሀዋሳ እንዲገቡ አድርገዋል፡፡ የራሳቸውን ኑሮ ሳይኖሩ ለቤተሰቦቻቸው ይጨነቃሉ፡፡ ለእናት አባታቸው ልብስ መርጠው የሚገዙት ልጆቻቸው ናቸው፡፡ ታናናሾቻቸውም የተሻለ ትምህርት እንዲያገኙ አድርገዋል፡፡

ሀዋሳ ላይ የንግድ ሥራቸውን በማስፋፋት በውጤታማነቱ እንዲቀጥል እያደረጉ ነው፡፡ አዲሱ መናኸሪያ አካባቢ ኪውን ሱፐር ማርኬት እና ኤሌክትሮኒክስ፣ ገብርኤል ፊት ለፊት ኪውን ስቲዲዮ፣ እንዲሁም በቅርቡ ደግሞ ዘመናዊ የቡና ቤት (ካፌ) ለመክፈት ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል፡፡

ባለታሪካችን የድካማቸውን ፍሬ ያገኙት ልጆቻቸው እና ባለቤታቸው ስለሚደግፏቸው ነው፡፡ ባለቤታቸው የመንግስት ሠራተኛ ቢሆኑም የሚሠሩትን ነገር አይቃወሙም፡፡ በትርፍ ጊዜያቸው ያግዛሉ፡፡ በተባበረ ክንድ ሠርተው ውጤታማ ሆነዋል፡፡ እንደነዚህ ያሉ ሥራ ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ከራሳቸው አልፈው ለሀገርም ስለሚጠቅሙ የሚመለከተው አካል አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር ቢያደርግ መልካም ነው፡፡

“ፈጣሪ የስኬት መንገዴን በማቅናት የሚያግዙ የትዳር አጋር እና ልጆች ስለሰጠኝ አመሰግነዋለሁ” ያሉት ወ/ሮ ዘሪቱ፤ “ቡርጂ ላይ የካፌ ስራ ስጀምር ቤት ያከራዩኝና ያበረታቱኝ ወ/ሮ አሚና እና ባለቤታቸው አቶ ጀሚል ደንቤ ባላችሁበት ምስግናዬ ይድረሳችሁ” ብለዋል፡፡

“ለሌሎች ሴቶች የማስተላልፈው መልዕክት ቢኖር ሥራ ለመሥራት ወኔ፣ ቁርጠኝነት እና ተነሳሽነት እንደሚያስፈልግ በመረዳት እስከመጨረሻ መትጋት ወሳኝ መሆኑን ነው፡፡ እንደ እኔ የመንግስት ሥራ አቋርጠው የግል ሥራ የጀመሩ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ተመልሰው ወደ ቢሮ የገቡ እንዳሉ ሁሉ ኪሳራውን መቋቋም አቅቷቸው ቤታቸው ገብተው የቀሩ አሉ፡፡

“የንግድ ሥራ ብዙ ውጣ ውረድ እንዳለውና አልጋ በአልጋ እንዳልሆነ መረዳት አስፈላጊ ነው። ጠንቃቃ ሆኖ ራስን ሰጥቶ ካልተሠራ ውድቀት አለው፡፡ በመሆኑም በንግድ ዓለም ማግኘት እንዳለ ሁሉ ማጣት ሊያጋጥም እንደሚችል በመረዳት ያለተስፋ መቁረጥ በጽናት ታገሉ” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡