መልካም ግብር በኃይማኖት ተቋማት እይታ

መልካም ግብር በኃይማኖት ተቋማት እይታ

በኢያሱ ታዴዎስ

ታላቁ የረመዳን ወር በሒጂራ አቆጣጠር 9ኛው ወር ነው፡፡ ወሩ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ የተቀደሰ፣ የጾም፣ የፀሎት እና የመንፈሳዊነት ወር ነው፡፡

በተጨማሪም የረመዳን የጾም ወር ከ5 የእስልምና መሰረቶች ውስጥ የሚመደብ ነው። ይህንንም በመላው ዓለም የሚገኙ የእምነቱ ተከታዮች በመጾምና በመፀለይ፣ እንዲሁም መልካም ተግባራትን በማከናወን ያሳልፋሉ፡፡

ጾሙን ለአቅመ አዳምና ሄዋን የደረሱ የእምነቱ ተከታዮች ሁሉ ፀሃይ ወጥታ እስከምትገባ ድረስ የመጾም ግዴታ አለባቸው።

ለ29 ወይም ለ30 ቀናት የሚቆየው ይኸው ጾም፣ እንደተጠናቀቀም የኢድ አልፈጥር በዓል ይከበራል፡፡ በዓሉም እንደ ጾሙ ሁሉ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ የተለየ ስፍራ ይሰጠዋል፡፡

ታዲያ በረመዳን ጾምም ሆነ በኢድ አልፈጥር በዓል ወቅት፣ ሙስሊሙ ሕብረተሰብ ከምን ጊዜውም ይልቅ ራሱን ከፈጣሪው ጋር ያቆራኛል፡፡ ራሱን ከምግብ እና ከመጠጥ፣ እንዲሁም ከክፉ ምግባሮች ይቆጥባል፡፡

እርስ በእርስ መተሳሰብ፣ መደጋገፍ፣ መጠያየቅ፣ እንዲሁም ያለው ለሌለው ማካፈል በወቅቱ የሚፈጸም የእምነቱ ተከታዮች ዋነኛ ተግባር ነው፡፡ በተለይም አቅም የሌላቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች ማብላት፣ ማጠጣት፣ ማልበስ እና መደገፍ የግድ ነው፡፡

አሁን ያለንበት ወቅትም የረመዳን ጾም ተገባድዶ የኢድ አልፈጥር በዓል እየተከበረ ያለበት በመሆኑ፣ በጾሙም ሆነ በበዓሉ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ እንደ እሴት የሚታዩት በጎ ምግባሮች ሲስተናገዱ ታይተዋል፡፡

በሌላ በኩል በተያዘው መጋቢት ወር በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድም አብይ ጾም ተጋምሶ ወደ መገባደጃው የደረሰበት ጊዜ ነው፡፡ በክርስትናውም እንዲሁ ጾሙ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መጥቶ ስለ ሰው ልጆች መከራን በመቀበል እና እስከሞት ድረስ ዋጋ በመክፈል ትንሳዔ ያደረገበት የሚታወስበት ነው፡፡

በጾሙ ወቅት የእምነቱ ተከታዮች በጸሎት፣ በምስጋና እና በምልጃ ወደ አምላካቸው በመቅረብ ያሳልፋሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር ከሌሎች ጊዜያት ይልቅ ከስጋ ድሎት ራስን በመቆጠብና መልካም ተግባራትን በመፈጸም ነው ጾሙ የሚካሄደው፡፡

እንደ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ሁሉ በክርስትናም በአብይ ጾምም ሆነ በስቅለትና ትንሳዔ በዓላት ወቅት ምዕመናን እርስ በእርስ በመደጋገፍ፣ በመከባበር እና በመፋቀር ያሳልፋሉ፡፡ ያለው ለሌለው ማካፈል በዚህ ወቅት የተለመደ ዋነኛ ተግባር ነው፡፡

ምዕመናኑ ወደ ፈጣሪያቸው ስለመቅረባቸው ማሳያውም የሚከውኑት መልካም ተግባሮች ናቸው፡፡

ታዲያ ይህ አጋጣሚ ሙስሊም እና ክርስትያኑ ማህበረሰብ፣ ደግሞም የሌሎቹ እምነት ተከታዮች ተፋቅረው በአንድነት ለሚኖሩባት ኢትዮጵያ፣ ከምንም ነገር በላይ ትርጉም አለው፡፡

ሀገራችን በዚህ ወቅት በፖለቲካው፣ በማህበራዊው እና በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ተወጥራ በብዙ እየተፈተነች ትገኛለች። ፖለቲካው አሁን እየተረጋጋ ቢመጣም፣ በጎራ ራሳቸውን ለይተው ነፍጥ ያነገቱ አካላት የሰላም መደፍረስ በተለያዩ አካባቢዎች እንዲኖር ምክንያት መሆናቸው አልቀረም፡፡ ይህ ደግሞ ሕብረተሰቡ ተረጋግቶ የራሱን ኑሮ እንዳይመራ እንቅፋት ሆኗል፡፡

በሌላ በኩል የኑሮ ውድነቱ ያን ያህል ለውጥ አለማምጣቱ ሀገራችንን እየፈተነ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ለኑሮ ውድነቱ ሌሎች ምክንያቶች እንዳሉ ሆነው በተለይም ነጋዴው ማህበረሰብ በምርቶች ላይ አላስፈላጊ እጥረትና የዋጋ ንረት እንዲከሰት ማድረጉ ከገባንበት የኑሮ ጭንቀት እንዳንወጣ ሰቅዞ ይዟል፡፡ በንግዱ ዘርፍ የሚፈጸሙ አሻጥሮችም ሌላው አባባሽ ምክንያቶች ናቸው፡፡

ከዚህ ባሻገር በማህበራዊ ሕይወትም ቢሆን ብዙ የላሉ ነገሮች ይስተዋላሉ፡፡ ማህበረሰባችን እንደ እቁብ፣ ዕድር፣ ሰርግ እና ለቅሶ ያሉ መስተጋብሮቻችንን የሚያጠናክሩ እሴቶች ባለቤት መሆኑ ይታወቃል፡፡

እነዚህ እሴቶች ቢኖሩም ቅሉ፣ አሁን አሁን በኃይማኖት፣ በብሄር እና በሌሎች ጎራዎች በመከፈል ሀገር እስከመጉዳት ድረስ አደጋ የሚፈጥሩ ድርጊቶች ሲፈጸሙ እየተመለከትን እንገኛለን፡፡ ይህም ሕብረተሰቡን እርስ በእርሱ እንዳይተሳሰብ እና እንዳይተማመን እያደረገው ነው፡፡

ከዚህ ውጪ የሕብረተሰቡን መስተጋብር እንደሚያጠናክር የሚታመንበት ማህበራዊ ሚዲያው በአብዛኛው አሉባልታና የሃሰት ዜናዎች የሚፈበረኩበት መድረክ እየሆነ መምጣቱ የዜጎች ልዩነት እየሰፋ እንዲሄድ ምክንያት ሆኗል፡፡

አሁን አሁን ፖለቲካውም ሆነ የሰዎች የጓዳ ሕይወት አደባባይ እየወጣ የአሉባልታ ሲሳይ እየሆነ መጥቷል፡፡ በዕድሜ ያልተገደበው ማህበራዊ ሚዲያውም አብዛኞቹ ዜጎች ተሳታፊ በመሆናቸው የሚወሩ ወሬዎች ሁሉ ጆሮ ማግኘታቸው አልቀረም፡፡ የእያንዳንዱ ዜጋን በርም እያንኳኳ ይገኛል፡፡

የዚህ የማህበራዊ ሚዲያ ውጤት በአብዛኛው አሉታዊ መሆኑ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ ማህበራዊ ሚዲያው ማህበረሰቡ በአግባቡ እየያዘው ባለመሆኑ ሀገርን ከመጥቀም ይልቅ ጉዳቱ አመዝኗል፡፡ ለሀገሩ የማይቆረቆርና መልካም እሴቶችን የሚበርዝ ትውልድ ለመፈጠሩም መንስኤ መሆኑ አልቀረም፡፡

ታዲያ ይህንን ሁሉ ሊያድን የሚችለው የኃይማኖት ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ሚና በአግባቡ መወጣት ሲችሉ ነው፡፡ የኃይማኖት ተቋማት ለተከታዮቻቸው መልካም ስነምግባር የሚላበሱበትን አስተምህሮ ከማስተማር በዘለለ፣ ለዜጎች ትክክለኛውን የለውጥ መንገድ በመጠቆም ሀገሪቱ ከገባችበት ፈተና በቀላሉ እንድትወጣ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ በሙስሊሙ ማህበረሰብም ሆነ በክርስቲያኑ ዘንድ ሲፈጸም የቆየው የጾምና የጸሎት ተግባር፣ ከዚህ ሻገር ሲል የተጀመሩ መልካም ግብሮች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡

በተለይም መልካም ተግባራትን ማከናወን በፈጣሪም ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው እንደ መሆኑ መጠን በጾምና በበዓላት ወቅት ብቻ ሳይሆን የሁልጊዜ ግብር በማድረግ ሀገር የምትፈልገውን ለውጥ እንድታመጣ የሚያስችል ሁነኛ መሳሪያ እንዲሆን መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡