“ሰው የሚለኝን ብሰማ ኖሮ፥ ለዛሬ አልበቃም ነበር” – ገረመው ኢብራሂም
ታላቁ የረመዳን ወር በሒጅራ አቆጣጠር 9ኛው ወር ነው፡፡ ረመዳን የተቀደሰ የጾም፣ የፀሎት እና የመንፈሳዊነት ወር ነው፡፡ በእስልምና ሀይማኖት የረመዳን ጾም ከ5 የእስልምና መሰረቶች ውስጥ ይመደባል፡፡ ይህንን ወር ከአንድ ቢለዮን የሚልቁ ሙስሊሞች በመላው ዓለም በመጾም፣ በመልካም ተግባራትና በፀሎት ያሳልፋሉ፡፡
የመተሳሰብ፣ የርህራሄ፣ የምህረትና የእዝነትም ነው ታላቁ የረመዳን ወር። በዓሉ ወገኖቻችንን የምናስብበት፣ የተቸገሩትን የምንረዳበት፣ የታመሙትን የምንጠይቅበት፣ የታረዙትን የምናለብስበት፣ በሀዘን ላይ ያሉትን የምናፅናናበት ነው።
የዛሬ የችያለሁ አምድ ባለታሪካችን ገረመው ኢብራሂም በመጀመሪያ እንደ እምነቱ ተከታይ በዓሉን በማስመልከት መልካም ምኞቱን የገለፀ ሲሆን፥ የህይወት ተሞክሮውን እንደ ሚከተለው አካፍሎናል፦
ገረመው ኢብራሂም ተወልዶ ያደገው በሀላባ ዞን ቁፌ በሚባል ገጠራማ ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡ እድሜው ለትምህርት እንደ ደረስ እንደ ማንኛውም ልጅ ትምህርት ቤት ገብቶ ለመማር አልታደለም ነበር፡፡
ታናናሾቹ ትምህርት ቤት ያለበት አጎራባች ቀበሌ ሄደው ይማሩ ነበር፡፡ “የትምህርት ፍላጎት ቢኖረኝም ቁጭ ብዬ ከመመልከት ውጪ ምንም አማራጭ አልነበረኝ፡፡ ታናናሾቼ ተምረው ሲመጡ፣ ቤት ውስጥ መጥተው ሲያጠኑ፣ የቤት ሥራ ሲሰሩ እና ሲያነቡ ሳይ እቀና ነበር” ሲል በማዘን ነበር በወቅቱ የነበረውን ስሜቱን የገለፀልን፡፡
ከጊዜ በኋላ የመማር ፍላጎቱ ያየለበት ገረመው፣ ከቤት ጠፍቶ እግሩ ወደ መራው ሄደ። “በጉልበት ሥራ ተቀጥሮ በወላጆቼ ቤት ይሰራ የነበረ ልጅ ነበር፡፡ የእሱ ቤተሰቦች ሰፈር ትምህርት ቤት አለ ሲባል ሰምቼ ወደ ከምባታ ዞን ቀዲዳ ጋሜላ ወረዳ ሄድኩኝ፡፡ የልጁ ቤተሰቦቹ ደስተኛ ባይሆኑም ዝም ብዬ ተመዘገብኩኝ፡፡ በ1987 ዓ.ም 1ኛ ክፍል ገባሁ፡፡” ሲል ትምህርት የጀመረበትን አጋጣሚ አጫውቶናል፡፡
“እሳት ለብሶ፥ እሳት ጎርሶ” እንደ ሚባለው የትምህርት ጥማቱን ተወጣው፡፡ ከነባር ተማሪዎች በሙሉ አንደኛ ወጣ፡፡ መምህራኖቹም ጉብዝናውን ተመልክተው በዚህ እድሜ ለምን አንደኛ ክፍል ገባ ሲሉትም ትምህርቱን ላለማጣት ሲል ያልሆነ ምክንያት ተናግሮ መቀጠሉን ገልፆልናል፡፡
ከዚያም 1ኛ ክፍል ግማሽ መንፈቅ ዓመት እንደ ተማረ ወደ 2ተኛ ክፍል አዘዋወሩት፡፡ በቀጋ ገርባ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ 3ተኛ ክፍል ተከታትሏል፡፡
በ1989 ዓ.ም ወደ ሀላባ ተመልሶ 4ተኛ ክፍል እድገት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብቶ መከታተል የጀመረ ቢሆንም ከጉዳቱ የተነሳ ብዙ ርቀት መጓዝ አልቻለም ነበር፡፡ ቤተሰቦቹ ገጠር ስለነበሩ ከተማ ውስጥ ቁጭ ብሎ የሚማርበት ቤት አጣ። በመጨረሻም መማር እየፈለገ አቋረጠ። ተስፋ የማይቆርጠው ገረመውም ቁጭ ከምል ብሎ፥ ቤት በር ላይ ትንሽ ሱቅ ነገር ከፍቶ መስራት ጀመረ።
ሥራው ጥሩ ቢሆንም የመማር ሱስ አላስቀምጥ አለው፡፡ ቤትም ሳይከራይ በድፍረት ተመልሶ ወደ ከተማ መጣ፡፡ ካቋረጠበት ክፍል መማር ጀመረ፡፡ በጣም ጎበዝ ስለ ነበረ ጓደኞቹ በየተራ እንዲያስጠናቸው ስለሚፈልጉ ወደ ቤታቸው ይዘውት ይሄዱ ነበር፡፡
ጉብዝናውን የተረዱ ወላጆቹም “እኔ ጋር ኑር፥ እኔ ጋር ኑር” እያሉ ይሻሙበት ጀመር፡፡ ገረመውም ከቤት ቤት እየቀያየረ ልጆቻቸውን እያስጠና ትምህርቱን በጥሩ ሁኔታ መከታትል ቀጠለ፡፡
የ8ተኛ ክፍል ፈተናን 99.9 ውጤት በማምጣት አጠናቀቀ፡፡ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል በቁሊቶ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በጥሩ ውጤት ተምሮ አጠናቀቀ፡፡
በ2000 ዓ.ም ወደ አርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ በታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል ለ3 ዓመት ተከታትሎ በ2003 ዓ.ም መመረቅ ችሏል። በ2004 ዓ.ም በሀላባ ዞን ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት በባህል ጥናት ዘርፍ ባለሙያ ሆኖ ተቀጥሮ እስካሁንም እያገለገለ ይገኛል፡፡
2ተኛ ድግሪውንም በማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ተምሮ ተመርቋል፡፡ በዚህ ሁሉ ሒደት ውስጥ ውጣ ውረዱ ቀላል አልነበረም፡፡ “እኔ ነገን እያሰብኩኝ ሁሉንም ችግሮች ችዬ ነበር የምማረው። ከሰዎች ዘንድ ብዙ እታዘብ ነበር፥ ሰው በጣም ይገረማል፡፡ እኔ ነገን የምደርሰውን ቦታ ብቻ ነበር የማስበው” በማለት ሲማር ያጋጠመውን ውጣ ውረዱን አውግቶናል።
የዩኒቨርስቲ ቆይታው ምን ይመስል እንደ ነበር ሲያጫውተኝ፡-
“በጣም አሪፍ ነበር፥ ልዩ እንክብካቤ ነበር የሚደረግልኝ፡፡ የተማሪዎች ህብረት ልዩ ድጋፍ ነበር የሚያደርጉልኝ፡፡ ለምረቃዬም ሱፍ ገዝተው ነው የሰጡኝ። ዶርም ላይ ደግሞ የምትንከባከበኝ ሰራተኛ ተቀጥሮልኝ ልብሴን የምታጥብልኝ፣ ምግብ የምታመላልስልኝ እና ዶርም የምታፀዳልኝ ሰራተኛ ተቀጥሮልኝ ነበር፡፡
“ትንሽ ችግር የነበረው በዛን ጊዜ የነበረው ግንባታ አካል ጉዳተኞችን ያማከለ አለመሆኑ ነው። ቢሆንም ግን እኔ ፎቅ ላይ እወጣ ነበር፡፡ እና እኔ ምንም ነገር አልችልም አልልም፡፡ አልችልም ማለት በተፈጥሮዬ አልወድም፡፡ ቀድሞ ውስጡን የሚያደክም ሰው አልወድም፡፡ ውስጤ ባለው ጠንካራ ወኔ ተነሳስቼ ነው እንቅፋቶችን አልፌ ለዛሬ የበቃሁት፡፡
“ሌላው በዩኒቨርስቲ ቆይታዬ የማልረሳው ገጠመኝ፡- በአንድ ወቅት በምግብ ጥራት ዙሪያ ተማሪዎች አምፀው ረብሻ ተነሳ፡፡ ከዚያም ተማሪ ሞተ፣ ምግብ አቅራቢ ሠራተኛም ሞተ። ፖሊሶችም ተጠርተው መጡ፡፡ ግቢው በሙሉ ጭስ በጭስ ሆነ፡፡ በዚያን ወቅት ሁሉም ጥለውኝ ሄደው እኔ ብቻዬን ዶርም ውስጥ ቀረሁ፡፡
“አጋጣሚ ሆኖ ዶርሜ ዳር ላይ ነበር። የአካባቢው ሰዎች ገጀራና ጦር ነበር ይዘው የገቡት። ዶርም ገብተው ሲወጡ የመኝታዬ ሽፋን ውስጥ ገብቼ ተደብቄ ስለነበር አላገኙኝም። በመጨረሻ ፖሊሶች አግኝተውኝ አወጡኝ። እና አላህ አተረፈኝ፡፡” ሲል ነበር የዩኒቨርስቲ ቆይታውን ያካፈለን።
አካል ጉዳት የገጠመው የ2 ዓመት ልጅ እያለ ነበር፡፡ “ወላጆቼ የሰው አይን ነው ቢሉም፥ አሁን ላይ ባለኝ የእውቀት ደረጃ ሳስበው ፖሊዮ ይመስለኛል፡፡ በጊዜው ህክምናም አልተስፋፋም ነበር፡፡ ከቆይታ በኋላ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ወስደውኛል፡፡ በጊዜው ያከሙኝ ፈረንጆች ነበሩ። የህፃናት አምባ ውስጥ ለሦሥት ዓመት ያክል በህክምና ቆይቻለሁ፡፡
“በህክምና ውጤቱም ፖሊዮ መሆኑ ታውቋል። የተሻለ ህክምና ለማግኘት ወደ ውጪ ሀገር ሄዶ ይታከማል ብለው ቀጠሮ ይዘው የነበረ ቢሆንም ቤተሰቦቼ ግን ከሄደ ይረሳናል ብለው ስላሰቡ አይሆንም ብለው ከልክለዋል። ‘ገረመው’ የሚለውንም ስም እናቴ ከጉዳቱ በኋላ ነው ያወጣችልኝ” ሲል አካል ጉዳት እንዴት እንደገጠመው አጋርቶናል።
አካል ጉዳተኛ በመሆኑ ያዘነባቸውን ጊዜያት ሲገልጽልን፡-
“በትምህርት ዓለም ብዙ ፈተናዎችን አልፌ ነው የመጣሁት፡፡ ምግብ ሳልበላ ትምህርት ቤት የምሄድባቸው ጊዜያቶች ነበሩ፡፡ ትልቁ ፈተና የሆነብኝ ደግሞ የመንቀሳቀስ ችግር ነበር፡፡ ሥራ ስይዝ ችግሩ ይቀላል ብዬ ባስብም፥ በተቃራነው ግን ይባስ ችግሩ አፈጠጠ፡፡
“የሚከፈለኝ ደመወዝ ትንሽ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ቤት ተከራይቼ በየጊዜው ለታክሲ እየከፈልኩ ኑሮዬን መግፋት ከበደኝ፡፡ ይህ ችግር እንዲቀረፍልኝ የሚመለከተውን አካል በተደጋጋሚ ብጠይቅም ምላሽ አላገኘሁም፡፡ ለቢሮ ሠራተኞች ተሽከርካሪ ቢገዛም ለእኔ ግን አካል ጉዳተኛ በመሆኔ አልተገዛልኝም፤ በዚህም በጣም ሞራሌ ይነካ ነበር፡፡” ብሏል፡፡
በዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ ችግሩን ለመቅረፍ ወደ ሚመለከተው አካል ለ7 ዓመታት ያክል ተመላልሶ ቢጠይቅም በጎ ምላሽ አለማግኘቱ አሁን ድረስ ይቆጨዋል፡፡
ወደ ትዳር ዓለም እንዴት እንደገባ ሲገልፅልን፦
“ከባለቤቴ ጋር በመግባባት ነው ወደ ትዳር የገባነው፡፡ በ1997 ዓ.ም የተመሰረተው ትዳሬ፣ ዛሬ የ2 ሴት ልጆች እና የ2 ወንድ ልጆች አባት አድርጎኛል፡፡” ብሏል፡፡
“ቤተሰቦቿ ካገባች በኋላ ሊያለያዩን ያላረጉት ጥረት የለም፤ እኔ ግን በፍቅር አሸነፍኳት፡፡ ልጃችን አይደለሽም ብለው እስከ ማግለል ድረስ ደርሰው ነበር፡፡ እሷ ግን አቋሟ ጠንካራ ነበር፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ እሷም ወለደች ከቤተሰቦቿ ጋርም ታረቅን” ሲልም በትዳር ዓለም የገጠመውን አጫውቶናል፡፡
ገረመው ኢብራሂም ለአካል ጉዳተኞች ምክረ ሃሳቡን ሲለግስ፡-
“መጀመሪያ አካል ጉዳተኝነታቸውን አምነው መቀበል አለባቸው። እኔ አሁን አካል ጉዳተኛ መሆኔን ረስቼዋለሁ፡፡ ምንም አይመስለኝም። አንዳንድ ሰው ግን ይሸማቀቃል፡፡ እኔ የምችለውን አሰራለሁ፤ ከጤነኛው በላይ ዘና ብዬ ነው የምኖረው። ሰው አየኝ፣ አላየኝ፣ ተገረመ፣ አልተገረመ ደንታዬም አይደለም፡፡
“ሰው ፊቱ የሚገርፈኝንና የሚያማኝን ባይ ኖሮ ለዛሬ አልበቃም ነበር፡፡ እኔ የእግር ጉዳት ነው ያለብኝ፡፡ እንደ ልብ ተንቀሳቅሼ መስራት አልችልም፡፡ አንዳንድ የማያቸው አካል ጉዳተኞች ትንሽ ጣታቸው ላይ ጉዳት እንኳን ደርሶባቸው ይለምናሉ። እንዲሁም ሙሉ አካል ኖሯቸው ሲለምኑ ይታያል፡፡ የሰው ልጅ ውስጡን ከገደለ በተግባር ለመስራት ቢሞክርም አይሰራም፤ አይችልም፡፡ ለምንም ነገር ወኔ ያስፈልጋል፡፡” ብሏል፡፡
More Stories
የልጅነት ፍቅር
መልካም ግብር በኃይማኖት ተቋማት እይታ
ኢድ ሙባረክ