የልጅነት ፍቅር
የልጅነት ጊዜ የሁሉም ሰው ደማቅ ትዝታ በልብ ውስጥ የታተመበት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ልጅነትንም ሆነ ትዝታውን ጣፋጭና አስደሳች ከሚያደርጉት ነገሮች ውስጥ ደግሞ አንዱ ፍቅር ነው – የልጅነት ፍቅር!
የልጅነት ፍቅር የሚረሳ አይደለም፡፡ ምን ጊዜው ቢረዝም፣ ትዝታው ድንገት ብልጭ እያለ ወደ ትናንት ይመልሳል፡፡ በበኩሌ የልጅነት ፍቅር በወቅቱ ከነበረው ሁኔታ ይልቅ፣ ይበልጥ ጣዕሙ ያለው ትዝታው ላይ ይመስለኛል፡፡ ብዕር አስነስቶ ወደ ትናንት የሚያነጉድ ሀያል ትዝታ! …
የሰማይ
አሞራ
ላዋይህ
ችግሬን፡፡
ብረር ሒድ ንገራት…
ከትልቁ ዛፍ ስር፤
ዱሮ በልጅነት
ከተጫወትንበት
ከትልቁ ዛፍ ስር
አታጣትም ፍቅሬን
ብረር
ሒድ
ንገራት፤
ንገር መናፈቄን፡፡
እንዲል ገጣሚው፡፡ በዚህ መነሻ፣ ለዛሬ ይህን የልጅነት ዘመንና ፍቅር የሚያወሱ ሁለት ሙዚቃዎችን መሰረት አድርጌ፣ በዚሁ ዙሪያ ጥቂት ነገር ለማለት ወደድኩ፡፡
ሙዚቃዎቹ የቅርቡን ሆነ የሩቁን ጊዜ ሁናቴ የሚያሳዩን ቢሆኑም፣ የግጥማቸው ይዘት ተመሳሳይ ስሜትን የሚያጭርብን ነው፡፡ ድምጻዊ ለምለም ኃይለ ሚካኤል ባለፈው ዓመት ለህዝብ ባደረሰችው አልበሟና “ልጅነት” በሚለው ሙዚቃዋ እነዚህን ስንኞች እናገኛለን፡-
ከማርያም ጣት አልፎ
ለማያድረው ኩርፊያ
ጸብና ፍቅራችን
የነበረው ጥድፊያ
እየተጠራራ ሁሉም ከየቤቱ
እሸት ይዞ ሽሚያው
ልፊያና ስሜቱ
በእነኚህ ስንኞች የአብዛኞቻችንን የልጅነት ጊዜ ሊያስታውሱ የሚችሉ ሀሳቦች ተገልጸዋል፡፡ ያ የእያንዳንዳችን መኖሪያ የሁላችንም ቤት የነበረበት፣ ያለውን ተካፍለን የምንበላበት፣ ጸባችን እንደ ጤዛ ወዲያው የሚያበቃበት፣ ፍቅራችን እንደ ጠዋት ጀንበር የሞቀ ደመቀ የሆነበት፣ ሮጠን፣ ዘለንና ቦርቀን የማንደክምበት ልጅነት እንደምን ይረሳል!?
ሙዚቃው ሲቀጥል፣ እንዲህ የሚሉ ስንኞችን ደግሞ እናገኛለን፡-
እሸት እሸት እሸት
እሸት ማር ወተት
እሸት እሸት እሸት
ጣፋጭ ነው ልጅነት
እሸት የማይጠገብና ተናፋቂ ነው – ልጅነትም እንደዛው፡፡ እርግጥ ነው፤ በዚያ ውብ የእድሜ ዘመን የነበረው ሳቅና ጨዋታ ትዝ ሲለው የማይመሰጥ ማን አለ? የኋሊት ሽምጥ ጋልቦ በትዝታ የማይነጉድ!
ቀጥሎ ደግሞ እነዚህን ስንኞች እናገኛለን፦
ትዝ ይለኝ ጀምሯል ከላይ
የልጅነታችን ሰማይ
እጅህን ጣል አርገህ ከአንገቴ
በለኛ ማርና ወተቴ
የእኛ ብቻ በሆነው ሰፊ ዓለም የምናውቀው ጣፋጩ ልጅነት፣ ከፍቅር ጋር በእነኚህ ስንኞች በዚህ መልኩ ተገልጿል፤ በትዝታ ተቃኝቶ፡፡
ቀጣዮቹ ስንኖች ደግሞ፣ ይህን ጣፋጭ ጊዜ መልሶ ከማስታወስ ባለፈ፣ ምነው ተመልሶ በመጣ የሚል ምኞትን ያረገዙ ጭምር ናቸው፤ ልጅነትን ከመናፈቅ ባሻገር፣ “አዋቂነትን” እየኮነኑ፡፡
ክፉ ደጉን ሳናውቅ
ያሳለፍነው ደስታ
ናፈቀኝ መልሶ
ላይገኝ ላንዳፍታ
ካሰገረህ ያንተም
ሀሳብ ወደ ኋላ
ልጅ እንሁን ሸሽተን
ከአዋቂነት ጥላ
ቆየት ወዳለው፣ የሂሩት በቀለ ሙዚቃ ደግሞ ልለፍ – በቀጣዮቹ ስንኞች፡-
ማዶ ለማዶ ነው
የእኔም እሱም መንደር
የተፈላለግነው
በዐይን ብቻ ነበር
ገና ሳምንታችን
ካወጋን በከንፈር
አወይ የልጅ ነገር
በልጅነት ፍቅር በግጥሙ በተገለጸው መልኩ ከዐይን ያለፈ ወግ ያወጋ ሰው ስሜቱን በይበልጥ ይገነዘበዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን፣ ከዚህ ድርጊትም በላይ የበለጠ ስሜት የሚሰጠው፣ ከዚያ በፊት ያለው ሂደት፣ መተፋፈሩና መፈራራቱ እንደሆነ ልብ ይሏል።
ቀጣዮቹ ስንኞችም ታዲያ፣ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ያለውን የሁኔታውን ሂደትና የስሜቱን ጥልቀት የሚገልጹ ናቸው፡-
እንደ ሜዳ ጥንቸል
ጥሻ ተደብቀን
የፍቅርን መጣፈጥ
በከንፈር ደጋግመን
አወይ የልጅ አመል
ሲመሽ ተለያየን
ብቻዬን ልሳቀው
ለዚህ በልብ ውስጥ ለታተመው ጥልቅ ስሜት፣ መነሻው አንድ ቅጽበታዊ አጋጣሚ መሆኑን ደግሞ ቀጣዮቹ ስንኞች ይነግሩናል፦
ስንዴ አጨዳ ወጥተን
ከጎኔ ባገኘው
ነዶ ሲያስታቅፈኝ
ጡቴን ቢነካው
ዐይኑ ቀደመና
ልቤን ወሰደው
አጋጣሚ ሆኖ
በዚህኛው (በሂሩት) የሙዚቃ ግጥም ውስጥ ያሉት ስንኞች፣ ከመጀመሪያው ሙዚቃ ስንኞች ይልቅ ምስል ከሳች ከመሆን ባሻገር፣ ስሜት በድርጊት ጎልቶ የሚንጸባረቅባቸው ናቸው፡፡ እጅን አንገት ላይ ከማሳረፍ ያለፈ የፍቅር መግለጫ ድርጊት፣ በሂሩት ሙዚቃ ባሉት የግጥም ስንኞች ላይ እናገኛለን፡፡ ይህም የስሜቱን ጥልቀት በማጉላት፣ በትንሿ የልጅነት ልብ ውስጥ የተጠነሰሰውን ታላቅ ፍቅር ያገዝፈዋል፡፡
More Stories
መልካም ግብር በኃይማኖት ተቋማት እይታ
“ሰው የሚለኝን ብሰማ ኖሮ፥ ለዛሬ አልበቃም ነበር”
ኢድ ሙባረክ