“አንባቢ ያደረገኝ አባቴ ነው” – ወይዘሮ ይመኙሻል አየለ

“አንባቢ ያደረገኝ አባቴ ነው” – ወይዘሮ ይመኙሻል አየለ

በአለምሸት ግርማ

ንባብ ሰውን ሙሉ እንደሚያደርግ አለም ያረጋገጠው እውነት ነው። ምስጢሩ የገባቸው ብልሆችም ሰፊ ጊዜያቸውን ለንባብ ያውላሉ። ይህም ህይወታቸውን በብዙ መልኩ ሲለውጥ ይታያል። እንደእነዚህ ዓይነት ሰዎች ከራሳቸው አልፈው ለቤተሰብ፣ በዙሪያቸው ላሉ፥ አለፍ ሲል ደግሞ ለሀገር አዎንታዊ አሻራቸውን ያሳርፋሉ።

የዛሬዋ እቱ መለኛችንም በንባብ ሰፊ ልምድ ያላቸው እንስት ናቸው። በቅርበት የሚያውቋቸው ሰዎችም ስለአንባቢነታቸው ይመሰክራሉ። እኛም ለሌሎች ምሳሌ ይሆን ዘንድ ልምዳቸውን ልናካፍላችሁ ወደናል፦

ወይዘሮ ይመኙሻል አየለ ይባላሉ። ተወልደው ያደጉት በተፈሪ ኬላ ከተማ ነው። ለቤተሰባቸው የመጀመሪያ ልጅ ሲሆኑ ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ ትምህርታቸውን መከታተል ጀመሩ። ተፈሪ ኬላ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመግባት እስከ 6ኛ ክፍል ድረስ ከተማሩ በኋላ በከተማው ከደረሱበት ክፍል በላይ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ምክንያት ወደ ሌላ ከተማ ሔደው ለመማር ተገደዱ።

7ተኛና 8ኛ ክፍልን አለታ ወንዶ ከተማ ተቀምጠው ተማሩ። ከዚያም ወደ ይርጋለም ከተማ በማቅናት ከ9ኛ ክፍል ጀምሮ ትምህርታቸውን መከታተል ቀጠሉ። ይሁን እንጂ፥ 12ኛ ክፍል ሲደርሱ ድንገተኛ የጤና እክል ገጠማቸው። በዚህም ምክንያት ትምህርቱን ለማቋረጥ ተገደዱ። ከቆይታ በኋላ ጤናቸው ሲስተካከል ወደ ዲላ ከተማ በማቅናት 12ኛ ክፍልን እዚያ ሊማሩ ችለዋል። በትምህርታቸው ጎበዝ የነበሩ ቢሆንም በገጠማቸው የጤና እክል ምክንያት የጠበቁትን ያህል ውጤት አላገኙም። በወቅቱ ውጤታቸውን በግል ለማሻሻል ባደረጉት ጥረት የተወሰነ ለውጥ ቢያገኙም እንደሚፈልጉት ሊሆንላቸው ግን አልቻለም።

በመቀጠልም ወደ ሃዋሳ መጥተው በወቅቱ በነበረው የአብዮታዊ ኢትዮጵያ ሴቶች ማህበር አማካኝነት ታይፕ መሰልጠን ጀመሩ። ለአንድ ዓመት ያህል ስልጠናቸውን ተከታትለው ቢጨርሱም በሰለጠኑበት ሙያ ስራ ማግኘት ግን ቀላል አልሆነላቸውም።

በዚህ ሁኔታ እያሉ ነበር የአሁኑን ባለቤታቸውን የተዋወቁት። በእጮኝነት እያሉ እጮኛቸው ባሌ እርሻ ልማት ስራ አገኙ። በአጋጣሚ እሳቸውም እዚያው ስራ በማግኘታቸው ወደ ባሌ አቀኑ። ትዳር ሲመሰርቱ ወቅቱ የደርግ ዘመነ መንግስት ማብቂያና የኢህአዴግ መንግስት መግቢያ እንደነበር አጫውተውናል፤ “ትውውቃችን በደርግ፥ ትዳራችን ደግሞ በኢህአዴግ ነበር ”ሲሉ በትዝታ ወደ ኋላ መለስ ብለው በማስታወስ። ከጥቂት ዝምታ በኋላ ንግግራችንን ቀጠልን፦

“በባሌ እርሻ ልማት ውስጥ በሂሳብ ክፍልና በንብረት አገልግያለሁ። በትዳራችን ደስተኞች ነበርን፤ ልጆችንም አፍርተናል።

“ይሁን እንጂ ከዘጠኝ ዓመታት ቆይታ በኋላ ባለቤቴ የስራ ቅያሪ ሲያገኝ፥ እኔ ስራዬን በመተው ወደ ሃዋሳ የምንመጣበት አጋጣሚ ተፈጠረ። የመጨረሻ ልጄ ሃዋሳ ነው የተወለደችው። ልጄን እያሳደኩ ሳለ፥ ሃዋሳ ዛየን ቢዝነስና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ሲመሰረት ማለትም በ1998 ዓ.ም በኮሌጁ በጓደኛዬ አማካኝነት ስራ አገኘሁ። በቤተ-መፅሐፍት ውስጥ ረዳት ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። ከስራዬ ጎን ለጎንም የዲፕሎማ ትምህርቴን በላይብረሪ ሳይንስ መከታተል ጀመርኩ። ትምህርቴን ሳጠናቅቅ የቤተ-መፅሐፉ ሐላፊ ሆንኩ። የወር ገቢዬም ተሻሻለ” ሲሉ ነበር በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ያጫወቱን።

በመቀጠልም በትምህርት ራሳቸውን ለማሳደግ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ በሒሳብ መዝገብ አያያዝ(በአካውንቲንግ) ትምህርታቸውን ተከታትለው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። በተመደቡበት ሙያ ለአስር ዓመታት ካገለገሉ በኋላ የስራ ዘርፍ ለውጥ ተደረገላቸው። ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በኮሌጁ ሪከርድና ማህደር ክፍል በኃላፊነት እያገለገሉ ይገኛሉ።

አንባቢ እንዲሆኑ ያደረጋቸው በቤተ-መፅሐፍ ውስጥ መስራታቸው ሊሆን ይችላል የሚል ድምዳሜ ቢኖረኝም፥ ነገሩ ግን የተለየ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ንባብ የጀመሩበትን አጋጣሚ እንዲህ በማለት ነበር ያጫወቱን፦

“ልጅ እያለሁ አባቴ አንባቢ ነበር። እኔም የእሱን ፈለግ እከተል ነበር። የጋዜጣ ኮንትራት ነበረው። ሁል ጊዜ ጋዜጣ ቤታችን ይመጣ ነበር። እኔም እነዚያ ጋዜጦች ላይ ያሉ ዜናዎችንና ሌሎችንም ፅሑፎች ሁልጊዜ አነብ ነበር። በዚያ ነው ንባብ የጀመርኩት። አንባቢ ያደረገኝ አባቴ ነው”

በርካታ መፅሐፍትን በማንበባቸው ያገኙትን ጥቅምም እንዲህ በማለት ነበር የገለፁልን፦

“ንባብ ሰውን ሙሉ ያደርጋል” የሚባለው አባባል ሳይሆን፥ እውነት ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ በርካታ መፅሐፍትን አንብቤያለሁ። ንባብ ስለሰዎች ባህሪ እና ስለህይወት ያለንን ግንዛቤ ያሰፋል። ከዚህም በላይ ቤተሰብን እንዴት መምራት እንደሚቻል በተለይም በልጆች አስተዳደግ ላይ ሰፊ ግንዛቤ እንድናገኝ ያስችለናል”

ለቤተሰብ መሰረቱ ወላጅ መሆኑን ከወይዘሮ ይመኙሻል የህይወት ተሞክሮ መረዳት ይቻላል። ይህን ማለት ያስቻለኝ እሳቸው ከወላጅ አባታቸው የወረሱትን የንባብ ባህል ለልጆቻቸው ማውረስ ችለዋል ነው። ስለልጆቻቸው ሲናገሩ፥

“እኔ ያልተወጣሁትን ልጆቼ ተወጥተውታል። በዚህም ደስተኛ ነኝ። በትምህርት ላይ የነበረኝን ፍላጎት በልጆቼ አይቼዋለሁ” ሲሉ ነበር ቁጭት በተሞላበት ድምፅ የተናገሩት።

ወንዱ ልጃቸው የጤና እክል ቢገጥመውም፥ የመጀመሪያና ሁለተኛ ልጆቻቸው በሁለተኛ ዲግሪ ተመርቀዋል። የመጨረሻ ልጃቸው ደግሞ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አራት ኪሎ ሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ትምህርት እየተከታተለች ትገኛለች።

ልጆቻቸው አንባቢዎች በመሆናቸው ደስተኛ እንደሆኑ ደጋግመው ይናገራሉ፤ አንባቢነታቸው አሁን ለደረሱበት ደረጃ እንዲደርሱ ማስቻሉን በመናገር። እሳቸው ጋ በሚማሩበት ወቅት ያለማንም አጋዥ በራሳቸው ጥረትና በእግዚአብሔር እርዳታ እዚህ መድረሳቸውን እንዲሁ።

በአሁኑ ወቅት ባለቤታቸው ጡረታ የወጡ ሲሆን፤ እሳቸው በስራ ላይ ይገኛሉ። ሁለቱ ልጆቻቸው አዲስ አበባ በስራ ላይ ሲሆኑ፤ የመጀመሪያ ልጃቸው የጤና ባለሙያ ፣ ሁለተኛ ልጃቸው ደግሞ ኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ምሩቅ ናት። ሁለቱም ትዳር መስርተውም አራት የልጅ ልጆችን አሳይተዋቸዋል። በዚህም “ዕድለኛ ነኝ” በማለት ሲናገሩ፥ ደስታ በተሞላበት ስሜት ውስጥ ሆነው ነው።

ስለዚህም ይላሉ ወይዘሮ ይመኙሻል፥ “ሴቶች ጊዜያቸውን በማይጠቅም ነገር ማባከን የለባቸውም። እኔ በርካታ የታሪክ፣ የፍልስፍና፣ የስነ-ልቦና፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ልቦለዶችንና ሌሎች መፅሐፍትን አንብቤያለሁ። ከዚህም በርካታ ጥቅም አግኝቼበታለሁ። በመሆኑም በማንበባቸው ስለህይወት የተለያዩ መረጃዎችን ያገኛሉ። በተለይም በልጆች አስተዳደግ ዙሪያ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ሊያነቡ ይገባል። እነሱ አንባቢ ሲሆኑ፤ ልጆቻቸውም አንባቢ ይሆናሉ” ሲሉ ይመክራሉ።