ድርብ ጽናትን ያነገበች!

ድርብ ጽናትን ያነገበች!

በጋዜጣው ሪፖርተር

የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው በየዓመቱ በመላው ዓለም 2 ነጥብ 1 ሚሊየን ሴቶች ለጡት ካንሰር ተጋላጭ ይሆናሉ፡፡ አሃዛዊ መረጃው የጡት ካንሰር በዓለም ላይ እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ እየሆነ መምጣቱን ያመላክታል፡፡

የጡት ካንሰር የሚከሰተው ከቁጥጥር ውጭ በሆነ መንገድ በጡት ውስጥ ያሉ ሕዋሳት አድገው እና ተከፋፍለው እጢ ሲፈጥሩ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

የጡት ካንሰር ሲጀምር ህመም ሆነ ምልክቶች የሉትም:: አብዛኞቹ የጡት እብጠቶች ካንሰር ባይሆኑም ዋነኛው የጡት ካንሰር ምልክት ግን በጡት ላይ የሚከሰት ጠጣር እብጠት ነው፡፡

የጡት ካንሰር ምርመራ በዋነኛነት ሚሞግራፊና አልትራሳውንድ ነው፡፡ ሚሞግራፊ ለምርመራ ጥቅም ላይ የሚውል መሳሪያ ነው፡፡ እንዲሁም የራስ በራስ የጡት ምርመራ (ጡትን በእጅ በመንካት እና በመዳበስ) በየወሩ ማድረግ ህይወትን ከሞት ለመታደግ ያስችላል፡፡

ሌላኛው የጡት ካንሰር ህክምና ፡- ቀዶ ጥገና፣ ኪሞቴራፒ (ፀረ ካንሰር መድሀኒት መጠቀም)፣ ራዲዮቴራፒ (የጨረር ሕክምና)፣ የሆርሞን ቴራፒ ጨምሮ በርካታ የጡት ካንሰር ህክምና አማራጮች እንዳሉ  የጤና ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

ሕክምናው ቀደም ብሎ ከተሰጠ የመዳን ዕድሉ ከፍ ያለ ነው፡፡ ማንኛውም እነዚህ ምልክቶች ያለበት ሰው በተቻለ ፍጥነት የሕክምና ምርመራ ማድረግ አለበት። እንዲሁም የጡት ካንሰር ምልክቶች ባይታዩም ሴቶች በየጊዜው የካንሰር ምርመራ ማድረግ ቢችሉ ገዳይ የሆነውን የካንሰር ህመምን አስቀድሞ መከላከል ይቻላል፡፡ 

የጡት ካንሰር ህክምና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ የመጣ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት  በርካታ የህክምና አማራጮች አሉት፡፡ አብዛኛው ሰው ስለህመሙ በቂ የሆነ መረጃ ስለሌለው አስቀድሞ የመመርመር ብሎም ራስን በራስ የመመርመር ባህሉ ዝቅ ያለ ነው። በዚህ የተነሳ ብዙዎች ወደ ህክምና ተቋም የሚመጡት ህመሙ ከጠናባቸው በኋላ ነው። ብዙዎች የሚረዱት ህመሙ ገዳይ እንጂ፤ በጊዜ ከተደረሰበት ታክሞ መዳን የሚችል መሆኑን አይደለም። በዚህ ምክንያት ቅድመ ምርመራ የሚያደርጉ ሴቶች ቁጥር ዝቅተኛ ነው። ከዚህም ባሻገር ህመሙ እንዳለባቸው ሲነገራቸው ራሳቸውን የሚንከባከቡበት መንገድ ከሰው ሰው የሚለያይ ቢሆንም አብዛኞቹ ከህመሙ በፊት በጭንቀት ራሳቸውን ሲጎዱ ይስተዋላሉ። በአንፃሩ ለሌሎች ምሳሌ የሚሆኑ ጠንካራ ሴቶችም አሉ።

ይህን ርዕሰ ጉዳይ ለማንሳት ያስገደደኝ÷ ባሳለፍናቸው ወራት በአለም አቀፍ ደረጃ ለ 33ተኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ32 ተኛ ጊዜ “የአካል ጉዳተኞችን የመሪነት ሚና በማጎልበት አካታች እና ዘላቂ ልማት እናረጋግጥ!” በሚል መሪ ቃል የተከበረውን ክብረ በዓል ለመታደም ከመጡ እንግዶች መካከል ድርብ ጽናትን ያነገበችው አንዲት ሴት ናት፡፡

ወ/ሮ ጀሚላ መሀመድ ትባላለች፡፡ በጥንካሬያቸው ከሚነሱ ሴቶች አንዷ ናት። ተወልዳ ያደገችው በኦሮሚያ ክልል፣ በተለምዶ ቆሬ ተብላ በምትጠራው ከተማ ሲሆን ባለትዳርና የሶስት ልጆች እናት ናት፡፡ ወ/ሮ ጀሚላ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ፌደሬሽን ቦርድ አባል እና የኦሮሚያ ክልል የአካል ጉዳተኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ናት፡፡

ለአካል ጉዳተኞች ድምጽ ከመሆን ባለፈ ለጡት ካንሰር ታማሚዎች ምስክር መሆን እንደምትፈልግ ትናገራለች።

“ይህን ህመም ለበጎ ነው ብዬ ነው የተቀበልኩት፡፡ ምክንያቱም ህዝብ እንዳገለግል ሌላ እድል እንደገጠመኝ ስለምቆጥረው ነው፡፡” በማለት ፍጹም በደስታ ስሜት በመሆን ስለ ህመሟ አወጋችን፡፡ ወ/ሮ ጀሚላ የካንሰር ታማሚ መሆኗ አሉታዊ ስሜት እንዳልፈጠረባት መመልከት ችያለሁ፡፡ በተፈጥሮ ያላት በራስ መተማመን የደረሰባትን ድርብ ጉዳት በጽናት እንድታልፍ አግዟታል፡፡ አካል ጉዳተኛ ወይም የካንሰር ታማሚ በመሆኗ ወደ ኋላ የሚያስቀራት ነገር እንደሌለም በኩራት ትናገራለች፡፡

“በህይወታችን ቆራጥ እና ጠንካራ ከሆንን የማንወጣው አንድም ነገር የለም” የምትለው ጀሚላ÷ ድንገት ካጋጠማት የጡት ህመም ታክማ ዛሬ ላይ በሙሉ ጤንነት ላይ ትገኛለች፡፡

 የጡት ካንሰር ህመም እንዴት እንደገጠማት ስትናገር፡-

“ድንገት ጡቴ  ላይ ሙቀት ነገር ተሰማኝ፡፡ እህቴን ሳማክራት ‘መታየት አለብሽ’ አለችኝ” ትላለች፡፡ ሀሳቧን ስትቀጥልም፡-

“በአቅራብያችን ወደ ሚገኝ የጤና ተቋም ሄጄ ምርመራ አደረኩኝ፡፡ ነገር ግን ውጤቱ ጥሩ አልነበረም፡፡ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለተጨማሪ ምርመራ ተላኩኝ” ስትል ታወሳለች፡፡ ብዙ ሰዎች ካንሰር እንዳለባቸው ሲነገራቸው ፍርሀት፣ ጭንቀት እና ብቸኝነት ሊፈጠርባቸው ይችላል። ወ/ሮ ጀሚላ ግን በወቅቱ ምንም አይነት ስሜት እንዳልተፈጠረባት አጫውታናለች፡፡ ይህም  የጥንካሬዋን ጥግ ያሳያል፡፡

በተደረጉላት የህክምና አማራጮች ውስጥ ÷ አንዱ የሆነው ቀዶ ጥገና ነበር፡፡ ለአብዛኛው ታማሚ የመጀመሪያው ህክምና ካንሰሩን በቀዶ ጥገና ማስወገድ ነው። የተለያዩ የቀዶ ጥገና ዓይነቶች ቢኖሩም  በሀገራችን በስፋት የሚደረገው ቀዶ ጥገና ጡቱን ሙሉ በሙሉ እና ብብት ስር ያሉ ንፍፊቶችን ማስወገድ ነው፡፡

ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ ታማሚዎቹ ዘግይተው ስለሚመጡ ካንሰሩና በዙሪያው ያሉትን ብቻ በማስወገድ ማከም አደጋው የከፋ ስለሚያደርገው እንደሆነ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ፡፡ ስለዚህ ጡት ሙሉ በሙሉ ከብብት ንፍፊት አብሮ ይወገዳል፡፡

ወ/ሮ ጀሚላ በዚህ የህክምና አይነት ታክማ ጡቷ ሙሉ በሙሉ ተወግዷዋል፡፡ የጡት ካንሰር ብዙ የህክምና አማራጮች ያሉት ና የሚታከም በሽታ ሆኖ ሳለ÷ አብዛኞቹ የካንሰር ታማሚዎች ታክመው እንደሚድኑ አምነው አለመቀበላቸው ከበሽታው በላይ እየጎዳቸው ይገኛል።

በመሰል ጭንቀት ላይ ላሉ እህቶች እንዲህ ስትልም ትመክራለች፡-

“የታመመው አካላችን አንድ ወይም ከዛ በላይ ሊሆን ይችላል፤ ጤነኛውን አካላችንን ለምን እናሳምመዋለን፡፡ ለሆነው ነገር ሁሉ ፈጣሪያችንን አመስግነን እስካለን ጊዜ መኖር ነው” ስትል አጽኖት በመስጠት ትናገራለች፡፡

ወይዘሮ ጀሚላ ሁለት እግሮቿ በፖሊዮ ምክንያት የተጎዱ ሲሆን አንድ ጆሮዋ መስማት ተስኖት  አጋዥ ማዳመጫ ተገጥሞላታል፤ እንዲሁም  የካንሰር ታማሚ ናት፡፡ እንግዲህ ይህቺ ጀግና ሴት ድርብርብ ጉዳት ይዛ በጽናት ለሌሎች ምሳሌ ለመሆን ቆርጣ ተነስታለች፡፡

ቀድሞ ካንሰር ሲባል ሰዎች ወዲያው የሚያስቡት ሞትን ነበር፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን እንደ ወ/ሮ ጀሚላ ያሉ ካንሰርን ተቋቁመውና አሸንፈው ጤናማ ኑሯቸውን መቀጠል የቻሉ እየበረከቱ መምጣታቸው ለሌሎችም ተስፋ እየሰጠ ነው፡፡ ዋናው ነገር አስቀድሞ በግልም ሆነ በሀኪም በመታገዝ ተገቢውን ክትትል ማድረግ እንደሆነም ወ/ሮ ጀሚላ ታሳስባለች፡፡

ሰዎች ስለካንሰር ያላቸው ግንዛቤ መሻሻል እንዳለበት ዛሬም የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ።

በሀገራችን አብዛኛውን ጊዜ ወደ ሀኪም ዘንድ የሚሄዱ የካንሰር ታማሚዎች ችግሩ ከጠናና በህክምና ለመርዳትም ፈታኝ ደረጃ ሲደርስ መሆኑ፤ ካንሰር አይድንም ወደሚለው መደምደሚያ እንዲደርሱ ምክንያት ሆኗል።

ጡት ወደ መቆረጥ ደረጃ ከደረሰ “ከመቆረጥ ይልቅ መሞት ይሻላል” የሚሉም አይጠፉም። በዚህም የተነሳ በህክምና ተቆርጦ መዳን ሲችሉ÷ ከግንዛቤ እጥረት ለሞት የተዳረጉ በርካታ እህቶቻችንን ተመልክቻለሁ፡፡

የካንሰር ቅድመ-ምርመራ ማድረግ ህመሙ ከፍተኛ ደረጃ ሳይደርስና ህክምናው የተወሳሰበ ሳይሆን ለመግታት እንደሚያስችል እንደ ወይዘሮ ጀሚላ ያሉ ጠንክራ እህቶች ማሳያዎች ናቸው።