የኤም 23 ተዋጊዎች በኮንጎ

የኤም 23 ተዋጊዎች በኮንጎ

በደረጀ ጥላሁን

የኤም 23 ተዋጊዎች፣ በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ትጥቅ አንግበው መዋጋት ከጀመሩ ከአሥር ዓመታት በላይ አስቆጥረዋል፡፡ ዘንድሮም ተጠናክረው በከፈቱት ጥቃት በርካቶች እየተገደሉና እየተፈናቀሉ ይገኛሉ፡፡

ጦርነቱ ባገረሸበት የአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች እየተሰደዱ ነው፡፡ ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ደግሞ በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች መጠለያ ጣቢያ በሚገኙ ሆስፒታሎች እየታከሙ እንደሚገኙ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በዘገባቸው አመላክተዋል፡፡

የኤም 23 ታጣቂ ቡድን “ጦርነቱን እኛ አልጀመርንም፣ የጀመሩት የኮንጎ ወታደሮች ስለሆኑ ኃላፊነት አንወስድም፤” ቢሉም፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ ሰብዓዊ ድጋፍ አድራጊዎች ኤም 23 እና ሩዋንዳን ይወነጅላሉ፡፡

የተለያዩ ታጣቂዎች የሚያምሷት ኮንጎ ሰላሟን ካጣች ከ30 ዓመታት በላይ ያስቆጠረች ሲሆን በርካታ ቦታዎችን ተቆጣጥሯል የሚባለው ደግሞ “ኤም 23” ታጣቂ ቡድን ነው፡፡

ዘመናዊ መሣሪያ እንደታጠቀ የሚነገርለት ታጣቂ ቡድኑ፣ የቁጥጥር ድሮን እንደሚጠቀምና በሩዋንዳ እንደሚደገፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችም ይጠቁማሉ፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ፤ የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የኤም 23 አማጺያን በምስራቃዊ ዴሞክራሲያዊ ኮንጎ ከተቆጣጠሯቸው አካባቢዎች ለቀው እንዲወጡ ማሳሰቡን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በፈረንሳይ አማካኝነት የቀረበውን ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ከሰሞኑ ምክር ቤቱ ያጸደቀ ሲሆን በመንግስታቱ ድርጅት የፈረንሳይ አምባሳደር ኒኮላስ ደ ሪቬሪ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሉአላዊነት እንዲከበር አፋጣኝ የተኩስ አቁም እንዲደረስም ጠይቀዋል።

የውሳኔ ሃሳቡ የሩዋንዳ ጦር ለኤም23 አማጺያን የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያቋርጥ እና ከኪንሻሳ ለቆ እንዲወጣ የሚጠይቅ ነው።

የጸጥታው ምክር ቤት አባል ሀገራት ተወካዮች የሩዋንዳ ጦር ለአማጺ ቡድኑ “በቀጥታ ድጋፍ አድርጓል” ሲሉ መናገራቸውን ቪኦኤ ዘግቧል። ኪጋሊ ግን በኪንሻሳ እና ምዕራባውያን ሀገራት የሚቀርብባትን ወቀሳ በተደጋጋሚ ውድቅ ስታደርግ ቆይታለች።

ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሩዋንዳ ከእርስ በርስ መካሰስና ግጭት ወጥተው ወደ ዲፕሎማሲያዊ ንግግር እንዲመለሱ የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ጠይቋል።

ይሁን እንጂ በሺዎች የሚቆጠሩ የኤም23 አማጺያን በማዕድን ሃብት በበለጸገው የምስራቃዊ ኮንጎ በርካታ ከተሞችን እየተቆጣጠሩ ነው። ከታህሳስ አጋማሽ ጀምሮ በሰሜን እና ደቡብ ኪቩ ግዛቶች ላይ በጀመሩት ውጊያ የሁለቱንም ግዛቶች ዋና ከተሞችን መቆጣጠር ችለዋል።

ኪጋሊ ኤም23 አማጺ ቡድንን የምትደግፈው የኪንሻሳን የማዕድን ስፍራዎች ለመቆጣጠር በማለም እንደሆነ ቢነገርም ማስተባበሏን ቀጥላለች።

በምስራቃዊ ኮንጎ በተቀሰቀሰው ጦርነት ከ270 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው የገለጸው የመንግስታቱ ድርጅት የፍልሰተኞች ኤጀንሲ፥ ለተፈናቃዮቹ ድጋፍ ለማቅረብ ከ40 ሚሊየን ዶላር በላይ ያስፈልገኛል ብሏል።

በሌላ በኩል የኮንጎ ፕሬዝዳንት በምስራቃዊው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ግጭት እየተባባሰ በሄደበት ወቅት በቀውሱ አያያዝ ዙሪያ የሚሰነዘርባቸው ትችት እየጨመረ በመምጣቱ የአንድነት መንግስት እንደሚመሰርቱ ማስታወቃቸውን ኤፒ በዘገባው አስነብቧል።

የኤም 23 አማፂያን በምስራቃዊ ኮንጎ የሚገኙ ዋና ዋና ከተሞችን ከተቆጣጠሩ በኋላ፣ ፌብሩወሪ 22, ለመጀመሪያ ጊዜ ንግግር ያደረጉት የኮንጎ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ሺሴኬዲ ሀገሪቱን ለሚያስተዳድረው ጥምር ፓርቲ በውስጣዊ ግጭቶች እንዳይዘናጉ አሳስበዋል።

“በትግሉ ነው እንጂ በጦርነቱ አልተሸነፍኩም” ያሉት ፕሬዳንቱ “ሁሉንም ተቃዋሚዎች ማነጋገር አለብኝ; የብሔራዊ አንድነት መንግስት ይመሰረታል” ብለዋል። ይህ ጥምር መንግስት ምን ሊመስል እንደሚችል ወይም መቼ እንደሚፈፀም ግን ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በምስራቃዊ ኮንጎ የሚገኘው የኤም 23 አማፅያን ጦርነቱን በአስቸኳይ እንዲያቆም እና ከያዛቸው ግዛቶች እንዲወጣ የሚጠይቅ የውሳኔ ሃሳብ በሙሉ ድምጽ ያጸደቀ ሲሆን፤ ምክር ቤቱ ግጭቱን በሚያራዝሙ አካላት ላይ ማዕቀብ እንደሚጣልባቸውም ዝቷል።

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተልዕኮ ኃላፊ ቢንቱ ኬይታ እንዳሉት በሩዋንዳ የሚደገፉት ኤም 23 አማጽያን በምስራቃዊ ሰሜን ኪቩ ግዛት የሰላም ማስከበር ስራውን እያደናቀፉ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፥ በሩዋንዳ መከላከያ ሃይል በመታገዝ የሰሜን ኪቩ የተወሰኑ ክፍሎች በኤም 23 አማፅያን በመያዛቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም አስከባሪ ተልእኮን ተግባራዊ ለማድረግ አዳጋች አድርጓል ብለዋል።

ኬይታ አክለውም አማፅያኑ የተልእኮው ቡድን ሲቪሎችን የመጠበቅ እና የህይወት አድን ስራዎችን እንዳይሰራ እንቅፋት እንደሆኑም ጭምር ገልጸው፥ በዚህም ምክንያት የሰብአዊ አደጋ ስጋትም እየጨመረ መምጣቱን አስረድተዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪች በደቡብ ኪቩ በምትገኘው ኡቪራ እየተካሄደ ባለው ግጭት የሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞች ችግር ውስጥ የወደቁ ሰዎችን ለማግኘት እና የህክምና ዕርዳታ ለመስጠት ፈተና እየገጠማቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በግጭቱ አካባቢ የሚገኙ ሆስፒታሎች በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ሰላማዊ ዜጎች በየቀኑ ተቀብለው እያስተናገዱ እንደሆነም መረጃዎች እያሳዩ ይገኛሉ።