ማንቸስተር ዩናይትድ ከአርሰናል ዛሬ ምሽት የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል

ማንቸስተር ዩናይትድ ከአርሰናል ዛሬ ምሽት የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል

በ28ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚዬርሊግ በኦልድትራፎርድ ስታዲየም ማንቸስተር ዩናይትድ ከአርሰናል ዛሬ ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ የሚያካሂዱት ጨዋታ ይጠበቃል።

በሊጉ ፈታኝ ጊዜን እያሳለፈ በሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ እና የፕሪሚዬርሊጉን ዋንጫ በሊቨርፑል ሊነጠቅ በተቃረበው አርሰናል መካከል የሚደረግ ጨዋታ ነው።

በ33 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ በዘንድሮው የውድድር ዘመን በፕሪሚዬርሊጉ የመጀመሪያ ሁለተኛ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል።

በሻምፒዮንስ ሊጉ ፒኤስቪ 7 ጎሎችን ማዝነብ የቻለው የሰሜን ለንደኑ ክለብ በበኩሉ በፕሪሚዬርሊጉ ከሁለት ጨዋታዎች ነጥብ መጣል በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርገው ጨዋታ ነው።

ሚኬል አርቴታ የአርሰናል አሰልጣኝ ሆኖ 200ኛ የፕሪሚዬርሊግ ጨዋታውን ዛሬ ያከናውናል።

በዚህም ስፔናዊው አሰልጣኝ በአንድ ክለብ ይህን ያኽል የፕሪሚዬርሊግ ጨዋታ የመራ 14ኛው አሰልጣኝ ይሆናል።

በማንቸስተር ዩናይትድ በኩል በዩሮፓ ሊጉ ከሪያል ሶሴዳድ ጋር በተካሄደው ጨዋታ ያልነበሩት ሀሪ ማጓር እና ማኑኤል ኡጋርቴ ለምሽቱ ጨዋታ ሊደርሱ እንደሚችሉ ተገልጿል።

በአርሰናል በኩል ወጣቱ ተከላካይ ሌዊስ ስኬሊ ቅጣቱን በመጨረሱ ወደ ጨዋታ ይመለሳል።

አንቶኒ ቴለር ተጠባቂውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት የሚመሩት ይሆናል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ