በቴኳንዶ ስፖርት ስልጠና ጥራት ላይ ልዩ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ ተገለጸ

በቴኳንዶ ስፖርት ስልጠና ጥራት ላይ ልዩ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ መጋቢት 01/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በቴኳንዶ ስፖርት እየተመዘገበ ያለውን ውጤት ለማስቀጠል በስልጠና ጥራት ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ በኣሪ ዞኑ የዘርፉ አሰልጣኞች ገለፁ።

በዞኑ ሳይቦርጅ ወርልድ ቴኳንዶ ለ11ኛ ጊዜ ከቢጫ ቀበቶ እስከ ሁለተኛ ዳን ያሰለጠናቸውን 110 ሠልጣኞችን አስመርቋል።

የኣሪ ዞን በክልል ብሎም በሀገር አቀፍ የተሻለ ውጤት እያስመዘገበ ካለባቸው የስፖርት ዘርፎች የቴኳንዶ ስፖርት አንዱ ለመሆኑ ተመልክቷል።

በዞኑ በአራት ወረዳዎችና ሁለት ከተማ አስተዳሮች ከሃያ በላይ ህጋዊ የቴኳንዶ ስልጠና ተቋማት ያሉ ሲሆን የሳይቦርጅ ወርልድ ቴኳንዶ በ2017 ዓ.ም ለ11ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 110 ሠልጣኞች አስመርቋል።

በኣሪ ዞን የሳይቦርጅና ኒኮ ወርልድ ቴኳንዶ ዋና አሰልጣኝ ማስተር አረቡ ሠይድ እና ግሎባል ማስተር ማቴዎስ ውርሳይ የቴኳንዶ ስፖርት ከአካላዊ ብቃት ባሻገር በወጣቱ ሥነ ምግባርና ሥነ ልቦና ላይ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ መሆኑን አመላክተዋል።

አሰልጣኞቹ አክለው በዘርፉ ከሀገር አልፎ ለዓለም የሚበቁ ብቁ ስፖርተኞችን ለማፍራት ጥራት ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

የኣሪ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ይኸነው ተስፋዬ እንደገለፁት የቴኳንዶ ስፖርት ዘርፍ ዞኑ በክልልና ሀገር አቀፍ ውድድሮች የተሻለ ውጤት እያመጣ በመሆኑ በሁሉም የዞኑ መዋቅሮች ዘርፉን ለማሳደግ በልዩ ሁኔታ እየተደገፈ ይገኛል።

በምረቃ መረሐ ግብሩ ለ70 አቅመ ደካማዎችና አጋዥ ለሌላቸው ልጆች ማዕድ የማጋራት ፕሮግራም ተካሂዷል።

ዘጋቢ፡ መልካሙ ቡርዝዳቦ – ከጂንካ ጣቢያችን