በጋዜጣው ሪፖርተር
ፍፁም ርህራሄ የተላበሱ፣ መልከ መልካም፣ ዝምተኛ፣ ሰው አክባሪ እና መካሪ መሆናቸውን በቅርበት የሚያውቋቸው ሰዎች ይናገራሉ። እንኳን ለወለዱት ልጃቸው ይቅርና የሥራ ባልደረቦቻቸውን፥ በተለይ ሴቶችን የእናትነት ፍቅር እያሳዩ ስለሚመክሯቸው ትምህርት ቤታችን ነሽ ሲሏቸው ይደመጣሉ፡፡ የታዘቡትን ከመምከር ወደ ኋላ አይሉም፤ ለቀረባቸው ሰው ሁሉ መካሪ ናቸው፡፡
ለሥራ ያላቸው ተነሳሽነትና ቅንነት ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ተግባብተውና ተከባብረው በመዝለቅ እስከ ጡረታ ጊዜያቸው እንዲቆዩ አግዟቸዋል፡፡
መምህርት ወርቅዓለም ክፍሌ በአዲስ አበባ ልደታ ክፍለ ከተማ በ1949 ዓ.ም የተወለዱ ሲሆን፤ አሁን 68 ዓመታቸው ነው።
ቤተሰቦቻቸው በሥራ ምክንያት የተለያዩ ሀገራት ተዟዙረው ሰርተዋል። በዚህ ምክንያት ትምህርታቸውን በተለያዩ ቦታዎች ተከታትለዋል። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የጀመሩት አርሲ ነገሌ “እቴጌ መነን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት” ሲሆን፤ በዚያም እስከ 6ተኛ ክፍል ድረስ ተምረዋል፡፡
ከ7ተኛ እስከ 8ተኛ ክፍልን ቦረና ነገሌ፣ ከ9ኛ እስከ 10ኛ ክፍል ደግሞ “ይርጋለም ራስ ደስታ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት” ቤት ከተማሩ በኋላ፤ ከ1967 እስከ 1968 ዓ.ም ድረስ በነበረው “የዕድገት በህብረት ዘመቻ” ላይ ቡርጂ ሶየማ የሚባል ቦታ በመሄድ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ ከዚያ ከተመለሱ በኋላ ከ11ኛ እስከ 12ኛ ክፍል በሀዋሳ ታቦር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረው አጠናቀዋል፡፡ በ1970 ዓ.ም 12ኛ ክፍልን ሲያጠናቅቁ በሀገር አቀፍ ፈተና ለሰርተፊኬት የሚያበቃ ውጤት ማምጣት ችለዋል፡፡
በመሆኑም በነበረው መስፈርት መሠረት ተወዳድረው በማለፍ፥ በ1972 ዓ.ም በሀዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ገብተው በመምህርነት ሙያ በሁለገብ ትምህርት ስልጠና በሰርተፊኬት ተመርቀዋል፡፡
ከዚያም ሀዋሳ ዙሪያ በሚገኙ የተለያዩ የገጠር ትምህርት ቤቶች፤ ለአብነትም “ዮዎ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት” ለ2 ዓመት አስተምረዋል፤ እዛው አካባቢ“ አቤላ ወንዶ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት” ለ1 ዓመት፤ እንዲሁም “ቱላ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት” ለ1 ዓመት ሠርተዋል። ከዚያ በኋላ ወደ ሀዋሳ በመዘዋወር “ሀዋሳ ገበያ ዳር የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት” አጠቃላይ ሁለገብ መምህር ሆነው አገልግለዋል፡፡
ከቆይታ በኋላ የትምህርት እድል አግኝተው ከሀዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በጂኦግራፊ ትምህርት ክፍል በዲፕሎማ በ1991 ዓ.ም ተመርቀዋል፡፡
በመቀጠልም በዲላ ዩኒቨርስቲ በ1992 ዓ.ም የክረምት ትምህርት እድል አግኝተው በዚያው በጂኦግራፊ ትምህርት ክፍል በድግሪ ፕሮግራም ተከታትለው በ1996 ዓ.ም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ማግኘት ችለዋል፡፡ ቀጥሎ በታቦር የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እና ታቦር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በጂኦግራፊ መምህርነት ሠርተዋል፡፡ በአጠቃላይ ለ28 ዓመታት በመምህርነት አሳልፈዋል፡፡ በመምህርነት በቆዩባቸው ጊዜያት በርካታ ተማሪዎችን በማስተማርና በሥነ-ምግባር በመቅረፅ ጥሩ ደረጃ አድርሰዋል፡፡
መምህርት ወርቅዓለም ክፍሌን የመምህርነት ህይወት ምን ይመስል እንደ ነበር ጠይቀናቸው ሲመልሱ÷
“የመምህርነት ህይወት በጣም ደስ ይል ነበር፡፡ ስራው ነፃ እና ደስተኛ ያደርጋል። ምክንያቱም ከህፃናት ጋር መዋሉ፣ እድገታቸውን፣ ጫወታቸውን እና ለትምህርት ያላቸውን ትጋት ማየቱ በጣም ያስደስተኝ ነበር፡፡
“ልጆቹ የትምህርት ደረጃቸው ከፍ እያለ ሲሄድ ግን መምህርነት ፈተኝ ነው፡፡ ተማሪዎችን በትምህርት ለማብቃት መጣር፣ ባህርያቸውን ለማረቅ መታገል፣ መስመር ሲስቱ ለመመለስ መጣር እና ለእነዚህ ሁሉ ተግባራት ትዕግስት ለማግኘት መታተሩ ድካም ነው፡፡ ይህ ውጣ ውረድ ኖሮም ክፍያው ግን ተመጣጣኝ አይደለም። ይሁን እንጂ የተማሪዎቻችንን ፍሬ ስናይ እንጽናናለን” ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ከ28 ዓመታት የመምህርነት ቆይታ በኋላ፥ በ1999 ዓ.ም በንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ በወጣ ማስታወቂያ ተወዳድረው በማለፍ የሰው ሀብት ሥራ አመራር ሥራ ሂደት ውስጥ ባለሙያ ሆነው ተቀጠሩ፡፡ ከዚያ የቀድሞው የደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ራሱን ችሎ ሲወጣ በባህልና ታሪክ ጥናትና ልማት ሥራ ሂደት ውስጥ የባህል ጥናትና ልማት ከፍተኛ ባለሙያ ሆነው ሠርተዋል፡፡ እንዲሁም የመደብ ለውጥ አድርገው በቋንቋና ሥነ-ጥበብ ሥራ ሂደት ውስጥ የእደ-ጥበብ ጥናትና ልማት ከፍተኛ ባለሙያ ሆነው ጡረታ እስከወጡበት 2009 ዓ.ም ድረስ ለ11 ዓመታት አገልግለዋል፡፡
“ከመምህርነት ወደ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ስመጣ በጣም የተለየብኝ ነገር ነበር፡፡ የቢሮ ሠራተኞች ላይ ብዙም የስራ ጫና የለም፡፡ ትምህርት ቤት ላይ ግን በጣም ውጥረት አለ፡፡ ትምህርት ቤት እያለሁ ምንም እረፍት አልነበረኝም፡፡ በክፍለ ጊዜዬ አስተምራለሁ፣ በእረፍት ጊዜ እዘጋጃለሁ፣ አነባለሁ፣ አርማለሁ፣ እና ፈተና አወጣለሁ ብቻ ምንም እረፍት የለኝም ነበር፡፡ ወደ ቢሮ እንደመጣሁ ግን ግራ ገባኝ፡፡ መልመድ አቃተኝ፡፡ እና አለቃዬ መምህር ስለነበር፥ ሁኔታዬን ተረድቶ ቀን ሙሉ የምሰራው ሥራ ሰጠኝ፡፡ ከዛ በኋላ ለመድኩት፡፡ መምህርነትና እና የቢሮ ስራ ምን ያህል ልዩነት እንዳላቸው የዚያን ጊዜ ነው ያየሁት” ሲሉ ያብራራሉ።
በስራ ዘመንዎ ሌሎችን ከመደገፍ እና ከማብቃት አኳያ የሚያደርጉት ጥረት ነበር? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፡-
“አንዳንድ ሰዎች ልትመክረን ትችላለች ብለው ሲያስቡና ሲመጡ፥ የምችለውን ያህል መንገዶችን ለማሳየት፣ ካነበብኳቸው ነገሮች በማካፈል፣ መስመር እንዲይዙ ለማድረግ ጥረት አደርጋለሁ፡፡ ሌላው መምህር እያለሁ ሁል ጊዜ ተማሪዎቼን ለማብቃት ጥረት አደርግ ነበር” ሲሉ አጫውተውናል፡፡
“ሰውን ቶሎ አልቀርብም፡፡ ካልቀረብኩ ደግሞ አልናገርም ዝምታን እመርጣለሁ አድማጭ ነኝ፡፡ ያለ እቅድ የሆነ ነገር አያስደስተኝም። ለምሳሌ አንድ ሰው መጥቶ ያለ ምክንያት ገንዘብ ቢሰጠኝ አያስደስተኝም፤ ምክንያቱም አቅጄ ሠርቼ ያገኘሁት ገንዘብ ስላልሆነ፡፡
“ሌላው ሁል ጊዜ ነሐሴ ወር ላይ እንደ ውጪ ሰው የራሴን የገንዘብ ቁጥጥር (ኦዲት) አደርጋለሁ፡፡ ምን ያህል ገንዘብ በዓመት ውስጥ አስገባሁ?፣ ምን ያህል ገንዘብ በሚታይ ነገር አዋልኩ?፣ ምን ያህል ገንዘብ በማይታይ ነገር አጠፋሁ፣ እና ምን ያህል ገንዘብ ቆጠብኩ? ብዬ ሁል ጊዜ ራሴን እገመግማለሁ፡፡ ይህ ልምድ አብሮኝ ያደገና ያረጀ ስለሆነ፤ አሁንም ቢሆን ባቀድኩት ነገር ላይ ነው ገንዘቤን የማወጣው፡፡ ባላቀድኩት ነገር ገንዘቤን ማባከን አልፈልግም፡፡
“ይህ ልምድ ጠቅሞኝ በኑሮዬ ሳልቸገር ነው ያሳለፍኩት፡፡ ሀዋሳ ላይ ስኖር የራሴን ቤት ሰርቼ ነበር የምኖረው፡፡ በጡረታ በተገለልኩ ጊዜም አልተቸገርኩም፡፡ የሀዋሳ ቤቴን ሸጬ አዲስ አበባ÷ ጎሮ ሰፈር ቤት ገዝቼ ደስተኛ ሆኜ እየኖርኩ ነው” ሲሉ ተሞክሯቸውን አጋርተውናል፡፡
የተለየ ተሰጥኦ ካሎት ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፡-
“ማንበብ እወዳለሁ ያነበብኩትን ለሰው ማጋራት ያስደስተኛል፡፡ ትኩረት ሰጥቼ የማነበው የስነ-ልቦና እና የምርመራ መጻህፍቶችን ነው። ማንበቤ በጣም ጠቅሞኛል። ሰዎችን ቀድሜ የማጥናት፣ አመለካከታቸውን ቶሎ የመረዳት እንዲሁም አንድን ሰው በምን አይነት መንገድ መቅረብ እንዳለብኝ ለማወቅ አግዞኛል” ሲሉ አብራርተዋል፡፡
“በህይወቴ በጣም ደስተኛ የሆንኩበትና የማልረሳው፥ ልጄ በትምህርቷ ተሳክቶላት ያየሁበትን ጊዜ ነው። በሀዘን ደግሞ የማልረሰው የእናቴን ሞት ነው፡፡ እናቴ ከሞተች ከ30 ዓመት በላይ ቢሆንም ሀዘኑ አሁንም ከልቤ አልወጣም” ሲሉ ይደመጣሉ፡፡
ቁምነገር አዘል ውይይቶችን በቴሌቭዥን ማየት፣ በሬዲዮ ማዳመጥ እና ተፈጥሮን ማድነቅ የመሳሰሉት በትርፍ ጊዜያቸው የሚዝናኑባቸው ነገሮች ናቸው፡፡ ደራሲ የመሆን ምኞት ነበራቸው። ያሳለፉትን እና የተመለከቱትን ነገሮች በብዕር ባሰፍራቸው ብለው ይመኙ እንደነበር ሳይገልጹ አላለፉም፡፡
መምህርት ወርቅአለም ተማሪ እያሉ ነበር ትዳር የመሰረቱት፡፡ ነገር ግን አለመግባባት ተፈጥሮ አንድ ልጅ ከወለዱ በኋላ ትዳራቸውን መቀጠል አልቻሉም፡፡ ልጅነት ሳይበግራቸው፣ ትምህርታቸውን እየተማሩ፥ ጎን ለጎን አይተኬ የእናትነት ድርሻቸውን እየተወጡ ልጃቸውን ያሳድጉ ነበር፡፡ ልጃቸውም ዛሬ ላይ በጂኦ ቴክኒካል ኢንጂነሪንግ በማስተርስ ደረጃ ተምራ አዲስ አበባ የመንግስት የልማት ድርጅት ውስጥ እየሰራች ትገኛለች፡፡ በልጆች አስተዳደግ ላይ ልምዳቸውን ሲያጋሩን፡-
“መጀመሪያ ብዙ የማላውቃቸው ነገሮች ነበሩ። ብዙ ጊዜ ስለልጄ ከኔ ታላላቅ የሆኑ እና ሴት ልጅ ያላቸውን ጓደኞቼን አማክር ነበር። ለልጄ አስተዳድግ ጥሩ ማስታወሻ ጥላልኝ ያለፈችው ጓደኛዬ መምህርት ባዩሽ በላይ ትባላለች፡፡ ነብሷን ይማር፥ በጣም ትመክረኝ ነበር” በማለት ያወሳሉ፡፡ ሀሳባቸውን ሲቀጥሉም፡-
“አብዛኞቻችን ልጆቻችንን የምናሳድገው በዘፈቀደ ነው። ብንችል እንዴት እናሳድግ ብለን መፅሐፍ አንብበን፤ እንዲሁም ጥሩ የልጅ አስተዳደግ ልምድ ያለውን ሰው አማክረን ብናሳድግ ጥሩ ነው። እኔ እስካሁን ድረስ ጠቅሞኛል” ሲሉ ለወላጆች ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡
ልጅነት የዋህነት ይበዛበታል፤ በየዋህነት ብዙ ስህተቶችን እንሠራና የወደፊት ህይወታችን ችግር ውስጥ ይገባል። ስለዚህ ያ ከመሆኑ በፊት በተቻለን መጠን በወጣትነት በተለይ ሴቶች በችኩልነትና በስሜታዊነት ምንም ነገር ውስጥ መግባት አያስፈልግም። ማመዛዘንና ወደ ፊት ምን ችግር ያመጣል? ብለን ማሰብ፤ ከአቅም በላይ ሲሆን ደግሞ በአስተሳሰብ የበሰለን ሰው ማማከር አለብን፡፡
በሰዓቱ ደብቀን የምናደርጋቸው ማናቸውም ነገሮች በተለይ አዲስ የወንድ ጓደኛ ለመተዋወቅ እና ትዳር ለመመስረት የምናስባቸው ነገሮች መጨረሻ በጥሩም ሆነ በመጥፎ መጋለጡ አይቀርም፡፡ ስለዚህ ከመወሰናችን በፊት በግልፅ ማማከር ያስፈልጋል፡፡
“በህይወቴ የደረሰብኝን ነገር ሳስብ፥ ሰው ይሰማብኛል ብዬ መጥፎ ነገር ውስጥ ገብቻለሁ፡፡ መጨረሻ ማዘን ይመጣል፡፡ ያ እንዳይሆን ሁልጊዜ የምናደርጋቸውን ነገሮች በእርጋታ፣ በትዕግስት እና በዘዴ መያዝ እንዲሁም በጉዳዩ ላይ የተሻለ የህይወት ልምድ ያላቸውን ሰዎችን ወይም ደግሞ በጉዳዩ ላይ እውቀት ያላቸውን ሰዎች ማማከር ያስፈልጋል። ወጣቶች ከሆንን ደግሞ መጀመሪያ የተለያዩ መፃህፍቶችን በማንበብ መረዳት እንዲሁም በተለያዩ ሚዲያዎች የሚተላለፉ መረጃዎችን መከታተል አለባቸው” ሲሉ በትዳር ህይወታቸው ያጋጠማቸውን አጋርተውናል፡-
“እነዚህን ሁሉ አልፈን ወደ ትዳር ዓለም ከገባን፤ ትዳራችንን ላለመፍታት ጥረት ማድረግ አለብን። ምክንያቱም በወላጆች መለያየት ልጆች ይጎዳሉ፡፡ ለምሳሌ፦ የኔ ትልቁ ስህተት ቆም ብሎ ያለ ማሰብ ነበር፡፡ አንዴ የተገነባውን ትዳር ለማዳን የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቅመን ለምሳሌ አማካሪ በማማከር እና የተለያዩ መፃህፍቶችን በማንበብ ራሳችንን በማብቃት ጥረት ማድረግ ተገቢ ነው” ሲሉም አክለዋል፡፡
“በህይወት ስንኖር ደግሞ በዚህ እድሜዬ የት መድረስ አለብኝ የሚለውን ነገር ማሰብ አለብን፡፡ ለምሳሌ ትዳር ውስጥ እንገባለን፤ በትዳር ውስጥ ስንኖር ዕቅድ ሊኖረን ይገባል። በዚህ ዓመት ንብረት ማፍራት አለብኝ፤ ቤት መስራት አለብኝ፤ እና ልጆቼን እዚህ ደረጃ ማድረስ አለብኝ ብለን በእቅድ እየተመራን ብንሄድ የመጨረሻ ውጤታችን ጥሩ ይሆናል፡፡ ትዳራችን የማይሆን እንኳን ቢሆን ትዳራችንን ለማዳን እስከ መጨረሻው ያሉ ዕድሎችን ተጠቅመን ከወጣን አይቆጨንም” በማለት አስተያየታቸውን አስቀምጠዋል፡፡
አሁን ለደረሱበት ስኬት ለመብቃት ድጋፍ ስላደረጉላቸው ሰዎች ሲናገሩ፡-
“በመጀመሪያ ደረጃ ማመስገን የምፈልገው፦ እግዚአብሔርን ነው፡፡ ለዚህ ደረጃ አብቅቶኝ በሕይወት ቆይቼ ታሪኬን ለመናገር ስላበቃኝ በጣም አመሰግነዋለሁ፡፡ በመቀጠል የንባብ ችሎታዬ እንዲዳብርና የማንበብ ልምዱ እንዲኖረኝ፣ ከልጅነቴ ጀምሮ መፅሀፍ እያመጣ እያነበበልኝ እየገፋፋኝ የነበረው ወንድሜ ነብሱን ይማር አቶ አብረሀም ክፍሌን በጣም አመሰግናለሁ። በተጨማሪም ሀዋሳ በነበርኩበት ጊዜ የነበሩ ጎረቤቶቼን፣ ጓደኞቼን በችግሬም ሆነ በደስታዬ፤ በማጣቴም ሆነ በማግኘቴ አብረውኝ የነበሩትን ሁሉ እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ፡፡ በመጨረሻም ልጄን በጣም አመሰግናለሁ፤ ምክንያቱም በዚህ በህመሜ ጊዜ ሰብስባ ይዛ እንደልብ እንድኖር ያደረገች እሷ ናት እና አመሰግናታለሁ” በማለት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ሥራ ወዳድ የሆኑት መምህርት ወርቅዓለም ከጡረታ በኋላ ወደ ሥራ የገቡ ቢሆንም፤ በገጠማቸው የጤና እክል ምክንያት መቀጠል አልቻሉም፡፡ አሁን ላይ ብዙ ጊዜያቸውን በማህበራዊ ህይወት ነው የሚያሳልፉት፡፡ በመምህርነት ዓለም የቆየ ሰው ማህበራዊ ኑሮ ውስጥ ቶሎ ለመግባት አይቸገርም፡፡ በሚኖሩበት አካባቢ ጠንካራ ማህበራዊ ህይወት እንዳላቸውም አጫውተውናል፡-
“ወላጆች ልጆቻቸውን በመልካም ሥነ-ምግባር አንፀው ለማሳደግ በመጀመሪያ ደረጃ ስለልጆች አስተዳደግ በቂ ዕውቀት ሊኖራቸው ይገባል። ለልጆቻችን እድገት ስንል ሁል ጊዜ ማንበብ አለብን፡፡ ማንበብ እንኳን ባይችሉ በተገኘው ጊዜ የማይጠቅም ወሬ ከማውራት በመቆጠብ፤ እውቀት የሚያስገኙ ሀሳቦችን አንስተው በመነጋገር እና በመወያየት ብዙ እውቀትን ማግኘት ይቻላል። ስለልጆች አስተዳደግ ያለንን ዕውቀት እና ግንዛቤ በየጊዜው ማደስ መቻል አለብን” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
More Stories
የብዙ ሰዎችን ደጅ ፀንቻለሁ – አቶ አብደላ ላራጎ
“አንባቢ ያደረገኝ አባቴ ነው” – ወይዘሮ ይመኙሻል አየለ
ድርብ ጽናትን ያነገበች!