“በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን እና በመድረክ ድራማ ረገድ ከእኔ በኋላ ለመጡ ትውልዶች መሰረታቸው ሆኜ ኖሬአለሁ” – ጸሐፌ ተውኔት ሀይሉ ጸጋዬ
በመሐሪ አድነው
በ1976 ዓ.ም “የዘውገ በሽታ” በሚል የሬዲዮ ድራማ ጅማሮውን ያደረገው የዛሬ እንግዳችን አንጋፋው ደራሲ፣ አዘጋጅና ተዋናይ ሃይሉ ጸጋዬን የበኩር ስራው ሆኖ ከህዝብ ጋር ያስተዋወቀው ቀዳሚ ስራው ነው፡፡ ቅደሚው፣ ኮብላይ፣ ከቤት የወጣ ሰው፣ ጋዜጠኛው፣ የበቀል ጥርሶች፣ ወደ ሃብት ጉዞ፣ የማዕበል ዋናተኞች እና ሌሎች የድርሰት ስራዎችን ለአራት አስርት አመታት ለአድማጭ ተመልካች በማበርከት ይታወቃል፡፡ በእነዚህና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ ከጸሀፊ ተውኔት ሃይሉ ጸጋዬ ጋር ቆይታ አድርገናል መልካም ንባብ፡፡
ንጋት፡- በመጀመሪያ እንግዳችን ለመሆን ስለፈቀድክ በዝግጅት ክፍላችን ስም በጣም አመሰግናለሁ፡፡
ሃይሉ፡- እኔም ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ፡፡
ንጋት፡- ጨዋታችንን ሃይሉ ጸጋዬ ማን ነው ከሚለው እንጀምር፡፡
ሃይሉ፡- ሃይሉ ፀጋዬ እንደሚታወቀው ፀሃፊ ተውኔት ነው፤ ተወልዶ ያደረገው በናዝሬት ከተማ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እስኪያጠናቅቅ የተማረው እዚያው ናዝሬት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ቲያትሪካል አርት ተምሯል። ትያትር ከተማረ በኋላ ለበርካታ አመታት የተውኔት ፅሑፎችን በመፃፍ፣ ድራማዎችን በማዘጋጀትና በመተወን ይታወቃል፡፡ ለአርባ አመታት ያህል በዚያ ሙያ ውስጥ የቆየ ሠው ነው፡፡
ንጋት፡- ለጨዋታችን መነሻ እንዲሆን የሬዲዮ፣ የቴሌቪዥን እና የመድረክ ተውኔቶች ሲፃፉም ሆነ ሲዘጋጁ አንድነታቸው እና ልዩነታቸው ምንድነው? ከሚለው እንደጀምር።
ሃይሉ፡- የሬዲዮ ተውኔት ከቴሌቪዥንና ከመድረክ ተውኔት የሚለይበት የራሱ ባህሪያት አሉት፤ እያንዳንዳቸው የሚያቀራርባቸው ወይም የሚያመሳስላቸው ነገሮች አሉ፡፡ ሁሉም ገፀ ባህሪያት ትረካዎች፣ ዲያሎግ፣ ሰስፔንስ /ልብ ሰቀላ/፣ ክላይማክስ /ጡዘት/ እና ሪዞሊውሽን /መደምደሚያ/ አሏቸው፡፡ ከሚያመሳስሏቸው ነገሮች ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ እነዚህ ናቸው፡፡
የሚለያዩበት ባህሪያትም አሏቸው፡፡ ሬዲዮ አድማጩ በጆሮው የሚያየው ድራማ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ምስኪን እለዋለሁ የሬዲዮ ድራማን ምክንያቱም መረጃ ከምንሰበስብባቸው መንገዶች 82 በመቶውን በአይናችን ነው የምናገኘው፡፡ ሬዲዮ ግን ይህን አይጠቀምም በጆሮ ብቻ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የራሱን ምናባዊ እሳቤ እና ምስል ስለሚፈጥር ለአድማጩ ቦታ ወይም ሠው ሲነግረው ለምሳሌ ማርታ ስለምትባል ልጅ እያንዳንዱ አድማጭ የራሱን ማርታ ነው የሚፈጥረው በቴሌቪዥንና በመድረክ ከሆነ ግን ያውቃታል፥ ያቻት ማርታ ይላል፡፡ ያ ነገር ደግሞ የሬዲዮ ድራማን ጠንካራ ያደርገዋል፡፡
ገፀ ባህሪያትን በተመለከተ በሬዲዮ ሲሆን ቁጥብ መሆን ያስፈልግሃል፡፡ እንደቴሌቪዥንና አልፎ አልፎ እንደመድረክ በተመለተ ማንዛዛት አትችልም፤ ለምን አድማጭህ በጆሮ ብቻ ስለሆነ የሚከታተልህ ድምፆች ሲበዙበት ግራ ሊጋባ ይችላል፡፡ ስለዚህ ገፀ ባህሪያቶችህን መመጠን ግድ ይልሃል ሬዲዮ ላይ፡፡
ቴሌቪዥን ባለሁለት ሚዲየም መልእክት ማስተላለፊያ መንገድ ነው ማለትም ባለሁለት ዳይሜንሽን ሲሆን መድረክ ደግሞ ባለ ሶስት ዳይሜንሽን ነው፡፡ ለምሳሌ በቴሌቪዥን ጠጅ ሲጠጣ ብታይ አይሸትህም ነገር ግን መድረክ ላይ ከሆነ ይሸትሃል፡፡
ሠውየውንም ቁመቱን፣ ጐኑንና ወርዱን ሌላኛውን የሚካሄደውን እንቅስቃሴ ከሶስት አቅጣጫ ታያለህ፡፡ ይህ በመድረክ ሲሆን ነው፡፡ በቴሌቪዥን ግን ቁመትና ጐን ብቻ ነው የሚታየው፡፡
የመድረክ የአፃፃፍ ቴክኒክ ከሬዲዮም ከቴሌቪዥንም የሚለየው ግፋ ቢል ሁለትና ሶስት ቦታ ብቻ ነው የምትቀይረው፥ ማለትም የሶስት ሠዓት ታሪክ አንድ ቦታ ላይ ነው የምትጨርሰው፡፡ ሬዲዮ ግን እንደፈለገው ይጋልባል፤ ሐዋሣ መጣለሁ፣ አሜሪካ እሄዳለሁ፣ ለንደን እገባለሁ፣ አርባምንጭ እመለሳለሁ፥ የፈለኩበት እጓዛለሁ፡፡ ቴሌቪዥንም እንደዚያው ነው፡፡ መድረክ ግን ታሪክ የምትፅፈው አንድ ቦታ ነው፡፡ ገቢር /አክት/ና ትእይንት/ሲን/ መካከል ሊቀያየር ይችላል፡፡ በዚህ መልኩ ነው ተመሳስሎሽ እና ልዩነታቸው የሶስቱ ዘርፎች፡፡
ንጋት፡- አንተ የሬዲዮ፥ የቴሌቪዥን እንዲሁም የመድረክ ተውኔቶችን ትፅፋለህ። ነፍስህ ግን ወደ የትኛው ነው የምታደላው?
ሃይሉ፡- እኔ ለሬዲዮ ብዙ ፍቅር አለኝ፡፡ እኔ በተፈጥሮዬ የሚፈትነኝን ነገር እወዳለሁ። አፃፃፍ ላይ የሬዲዮና የመድረክ ተውኔት በጣም ፈታኝ ናቸው፡፡ ሆኖም ሬዲዮ ግን በድምፅ ብቻ ስለሚተላለፍ አድማጭ በአእምሮው ውስጥ ምስል እንዲስል መትጋት አለብኝ፡፡ ይህ ደግሞ በጣም ፈታኝ ነገር ነው፡፡ በመሆኑም ነፍሴ ያለችው በሬዲዮ ላይ ይመስለኛል፡፡ መተወን የምመርጠውም ከመድረክና ቴሌቪዥን ይልቅ በሬዲዮ ድራማ ላይ ነው፡፡
ንጋት፡- ሃይሉ ፀጋዬ ሲነሳ ብዙዎች የሚያስታውሱት የማዕበል ዋናተኞችንና ወደ ሃብት ጉዞ የተሰኙ የሬዲዮ ተከታታይ ድራማዎችን ነው፡፡ በተለይ የማዕበል ዋናተኞች ድራማ ላይ ዕፁብ የምትባለው ገፀ ባህርይ ስትሞት በርካቶች ጥልቅ ሃዘን ተሰምቷቸዋል፡፡ ከዚህም በላይ ዘፈንም ተዘፍኖላታል፡፡ ለመሆኑ አንተን ከህዝብ ጋር ያስተዋወቀህ የመጀመሪያ ድራማ የትኛው ነው?
ሃይሉ፡- “የዘውገ በሽታ” በሚል የሬዲዮ ተውኔት ነው በ1976 ዓ.ም ሥራዬን የጀመርኩት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው ከፍ ብሎ መብረር የጀመርኩት፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ብዙ አሉ፡፡ ቅዳሜ መዝናኛ ላይ ቅርጫው፣ ኮብላይ፣ ከቤት የወጣ ሠው፣ ጋዜጠኛውና የበቀል ጥርሶች የሚጠቀሱ ሲሆን ከዚያ በኋላ “ወደ ሃብት ጉዞ” የሚለውን የሬዲዮ ድራማ እሁድ ላይ አቀረብኩ፤ ቆይቶ ደግሞ እንዳልከው “የማዕበል ዋናተኞችን” አቀረብኩ፡፡
አሁን ባለው ትውልድ በጣም የሚታወቀው “የማዕበል ዋናተኞች” እና “የደወል ድምፆች” የተሠኙት ተከታታይ የሬዲዮ ድራማዎቼ ናቸው፡፡ ነገር ግን በቅዳሜ መዝናኛ የሠራቸውን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ዛሬም በፍቅር ያነሷቸዋል ያስታውሷቸዋል፡፡
ቀደም ያለው ትውልድ ደግሞ በቅዳሜ መዝናኛ ያቀረብኳቸውን ቅርጫው፣ የልጃገረዶች ሠፈር፣ የበቀል ጥርሶች፣ በቀቀን፣ የሊቅ መሞት እና ከብላይ እንዲሁም የመጨረሻው ሠዓት የመሳሰሉትን ያስታውሳሉ፡፡
ነገር ግን፥ ህዝቡን ዳር እስከ ዳር ያነቃነቀው በ1992 ዓ.ም የፃፍኩት የማዕበል ዋናተኞች ተከታታይ የሬዲዮ ድራማ ሲሆን የድራማው ዋና ገፀ ባህርይ የነበረችው እፁብ ስትሞት ከፍተኛ የህዝብ ቁጣ ነበር የቀሰቀሰው፡፡ ጥቁር የለበሱም አሉ፣ ሊገድሉኝ የሚፈልጉ ሠዎችም ነበሩ፡፡ እራሷን ነው ያጠፋችው እንጂ እኔ መች ገደልኳት የሚል ማስተባበያ እስከመስጠት ደርሼ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ሥራው ምን ያህል በሠው ልብ ውስጥ ገብቶ እንደነበር ነው የሚያሳየው፡፡
እንዲያውም አንዲት ልጅ ከሐዘኗ የተነሳ ከቤት አልወጣ ብላ አስቸግራ እናትየው እፁብን ሆና ወደተጫወተችው አርቲስት መስታወት አራጌ ስልክ ደውላ አንድ ነገር አድርጊልኝ ብላት መስታወት ደውላ ልጅቱን እንዳረጋጋቻት አስታውሳለሁ፡፡
ንጋት፡- ለአራት አሥርት አመታት በሚባል ጊዜ ውስጥ በርካታ ተከታታይ የሬዲዮ ድራማዎች፣ የቴሌቪዥንና የመድረክ ትወናዎች እንዲሁም በቅዳሜ መዝናኛ መጣጥፎች ሲነሱ ሃይሉ ፀጋዬ አብሮ ይነሳል፡፡ በዚህ የረዥም አመታት ልምድህ ሌሎችን አብቅቻለሁ ብለህ ታስባለህ?
ሃይሉ፡- የሬዲዮ፣ የቴሌቪዥንም ሆነ የመድረክ ድራማን ከእኔ በኋላ ለመጡ ትውልዶች መሠረታቸው ሆኜ ኖሬአለሁ፡፡ ቴክኒኩን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ አብዛኛው ከእኔ በኋላ የመጣው ትውልድ የተማረው ከእኔ ነው፡፡ የእኔ ተፅእኖና አሻራ ቀላል እንዳልሆነ እራሴም አውቀዋለሁ። በጣም ብዙ ነው፡፡ በፊልም ስትመጣ እነ ቅድስት ይልማ፣ መሐሙድ ዳውድ የመሳሰሉትን እጃቸውን ይዤ ያስተማርኳቸው ናቸው፡፡ በሬዲዮ ድራማ አፃፃፍ ላይ ደግሞ አሁን በህይወት የሌሉት ሠለሞን ዓለሙ፣ መስፍን ጌታቸው /የሠው ለሠው ድራማ ደራሲ/ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከእኔ ነው የተማሩት፡፡ እነ ቢኒያም ወርቁ፣ ትእግስት ዓለሙ ወዘተ ቁጥር ስፍር የላቸውም፡፡ እኔ ደም ተፍቼ ነው የተማርኩት እውቀቴን ለትውልድ ማስተላለፍና ማውረስ በመቻሌ በጣም እድለኛ ነኝ፡፡
የእኔ ታናሽ ወንድም አዱኒስ ወይም አድነው ወንድይራድ /ገመና የተሠኘ የቴሌቪዥን ድራማ/ ደራሲ በሙያው አርክቴክት ሲሆን ከልጅነቱ ጀምሮ እኔን ሲከተል ያደገ ስለሆነ ሥነ ፅሑፍ ላይ የእኔ አሻራ እና ተፅእኖ አለበት፡፡ ነገር ግን አንዴ መስመሩን ከያዘ በኋላ እኔን የሚፈልግ ሠው አልነበረም፡፡ የራሱን መንገድና የአፃፃፍ ስታይል ተከትሎ የሄደ ሠው ነው፡፡
ንጋት፡- ሐዋሣ ምን እግር ጣለህ?
ሃይሉ፡- ለደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያ ሥራዎቼን ለማቅረብ ወይም ሠዎችን አብቅቼ እቀርባለሁ እያልኩኝ ላለፉት ስምንት ከዚያ በላይ አመታት ተስፋ እያደረኩኝና ቃል ስገባ ቆይቼ ነበር፡፡ የዛሬ አንድ ዓመት አካባቢና ከደራሲ በየነ ፀጋዬ ጋር ለገጣሚ በለው ገበየሁ መፅሐፍ ምርቃት የክብር እንግዳ ሆኜ በመጣሁበት አንዲት ልጅ አገኘሁ፡፡ እፁብ ድንቅ ጫኔ ትባላለች፡፡ በጣም ተሰጥኦ ያላት ልጅ ነበረች ይህችን ልጅ ላስተምር አልኩና ለረጅም ጊዜ ማለትም ከአመት ለሚያልፍ ጊዜ ቁጭ አድርጌ አስተማርኳት። የጀማመረቻቸው ፅሑፎችና የፊልም ስክሪኘቶችን በማየት ተሰጥኦ እንዳላት ስረዳ የአፃፃፍ ቴክኒኩን አስተምሬ ገራኋት፡፡
ከዚያም ተከታታይ የሬዲዮ ድራማ ከሲዳማና ከቀሩት የቀድሞ ደቡብ ክልሎች ሳትወጣ ተውኔት እንድትፅፍ አደረኳት፡፡ ያንን ፅሑፍ ይዛ ደቡብ ሬዲዮ ኤፍ ኤም 100.9 ቀረበች፡፡ አራት ክፍል ያህል አስቀርፃ ኤዲት አስደርጋ ሰጠች፡፡ ወደዱት ውለታ ተዋዋለች። አሁን የራሷን ድርጅት አቋቁማ ድራማውን በሬዲዮ እሁድ እሁድ እያቀረበች ትገኛለች፡፡
ተከታታይ ድራማው ከ6 ወር እስከ አንድ አመት በደቡብ ሬዲዮ ኤፍ ኤም 100.9 ላይ ይሄዳል ብዬ አስባለሁ፡፡ ከደቡብ አንዲት ልጅ አብቅቻለሁ፡፡ እግዚአብሄር ከረዳኝ ሌሎችንም አግዤ ወደ ደህና ቦታ አደርሳቸዋለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡
ንጋት፡- በደቡብ ሬዲዮ ኤፍ ኤም በ100.9 ተከታታይ የሬዲዮ ድራማ ሲቀርብ ፍላጐቱ ላላቸው ወጣቶች ምን አይነት መነሳሳት ይፈጥራል ትላለህ?
ሃይሉ፡- “ይህች ልጅ ቻለች እንዴ?” ብለው ብዙ ወጣቶችና ትልልቅ ሠዎችም እንደሚነሳሱ እርግጠኛ ነኝ፡፡
የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ወይም አራቱም ክልሎች ወጣቶቻችንን አስተምሩ ቢሉን እየመጣን ሥልጠና እንሰጥላቸዋለን፡፡
ጣቢያውም ሆነ ክልሎቹ ፍላጐት ካላቸው እኛ ለማስተማር አቅሙም ፍላጐቱም ስላለን ዝግጁ ነን፡፡ ከሬዲዮም በተጨማሪ የቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማም ይኖራል ብለን እናስባለን፡፡
እኔ አሁን ብዙ ኪሎ ሜትር ለማስተማር መጣሁ፡፡ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያዎቻችሁ ደግሞ መቶ እና አምስት መቶ ሜትር ቀረብ ይበሉ፡፡ ከዚያም ወደሚፈለገው ግብ መድረስ እንችላለን ብዬ አምናለሁ፡፡
ንጋት፡- ለነበረን ጊዜ በዝግጅት ክፍላችን ሥም እጅግ አመሠግናለሁ፡፡
ሃይሉ፡- እኔም አመሠግናለሁ፡፡
More Stories
የብዙ ሰዎችን ደጅ ፀንቻለሁ – አቶ አብደላ ላራጎ
“አንባቢ ያደረገኝ አባቴ ነው” – ወይዘሮ ይመኙሻል አየለ
ድርብ ጽናትን ያነገበች!