የስኬት ቁልፉ የጠፋበት ዩናይትድ ገናናነቱን መመለስ ተስኖታል
በኢያሱ ታዴዎስ
ሰር አሌክሳንደር ቻፕማን ፈርጉሰን፣ የማንችስተር ዩናይትድን የስኬት በር ቁልፍ አግኝተው ስኬትን እንዳሻቸው ካጣጣሙ በኃላ መልሰው ዳግመኛ እንዳይገኝ አድርገው የጠረቀሙት ነው የሚመስለው።
የቀድሞው የላንክሻየሩ ክለብ አለቃ፣ ኦልድትራፎርድን ከረገጡበት ከአውሮፓዊያኑ 1986 ጀምሮ እስከ 2013 ድረስ ስኬት ማለት ምን ማለት እንደሆነ አሳይተው ነበር በጡረታ የተገለሉት።
በእርግጥ ዩናይትድ፣ ከሰር አሌክስ ዘመን በፊትም ቢሆን በአውሮፓ ገናና ክለብ ነበር። በእንግሊዝ ምድር የነበሩትን ዋንጫዎች ዓይነት በዓይነታቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኦልድትራፎርድ ያመጡትና ከ1903 እስከ 1912 ድረስ በክለቡ ቆይታ ያደረጉት ኧርነስት ማንግኖል የዩናይትድን የእንግሊዝ ከፍታ አስጀመሩ።
ኧርነስት ማንግኖል 2 የመጀመሪያ ዲቪዚዮን (የአሁኑ ፕሪሚየር ሊግ)፣ 1 የኤፍኤ ካፕ እና 2 የቻሪቲ ሺልድ (የአሁኑ ኮሚዩኒቲ ሺልድ) ዋንጫዎችን በማሳካት የክለቡ የስኬት ማህደር ላይ የሰፈሩ አሰልጣኝ ናቸው።
ከእሳቸው በኋላ በርካታ አሰልጣኞች ቢፈራረቁም የተለየ ታሪክ መስራት የቻሉት ግን ጀብደኛው ስኮትላንዳዊው ሰር አሌክሳንደር ማቲው በዝቢ ናቸው። ማት በዝቢ ከ1945 እስከ 1969 በክለቡ ባደረጉት ቆይታ 5 የፕሪሚየር ሊግ (የመጀመሪያ ዲቪዚዮን)፣ 2 የኤፍኤ ካፕ እና 5 የቻሪቲሺልድ ዋንጫዎችን ከማስገኘታቸውም በላይ በአውሮፓ መድረክ ትልቁ የሆነውን የቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን 1 ጊዜ በማሳካት ከእንግሊዝ አልፎ በአህጉሪቱ ደረጃ ገናና አድርገውታል።
ይህ የማት በዝቢ ስኬት በማንችስተር ከተማው ክለብ ብቻ ሳይሆን በመላው አውሮፓ ከታዩ የምን ጊዜም ምርጥ አሰልጣኝ ተርታ አሰልፏቸዋል።
ዩናይትድ ከእኚሁ ውጤታማ አሰልጣኝ በኋላ፣ የሊጉን ዋንጫ ዳግም እስኪያነሳ ድረስ የግድ 4 አሰልጣኞች መፈራረቅ ነበረባቸው። ከዚያ ወዲህ ግን እንደ ሰር ማት በዝቢ የስኮትላንድ ዜግነት ያላቸው ቆፍጣና አሰልጣኝ መዳረሻቸውን ኦልድትራፎርድ አደረጉ፤ አሌክስ ፈርጉሰን።
ጨዋታ ሲመሩ ማስቲካ ያለ እረፍት የሚያመነዥጉት እኚህ ሰው፣ ክለቡን ሲረከቡ በጎልማሳነት ዕድሜ ላይ ቢገኙም በደጋፊዎች ዘንድ ብዙም ስለማይታወቁ እምነት አላገኙም ነበር። አስቀድሞ ያሰለጥኑበት ለነበረው የስኮትላንዱ አበርዲን ክለብ የሀገሪቱን ዋንጫዎችን ሁሉ ጠራርገው ከማስረከባቸውም በላይ የአውሮፓ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ጭምር በማከል ትልቅ ውለታ ውለው ነበር።
ወደ እንግሊዙ ገናና ክለብ ሲያመሩ ግን እንደ ስኮትላንድ ቀላል ፉክክር እንደማይገጥማቸው በማሰብ ነበር በርካቶች ትኩረት የነፈጓቸው። በዚያ ላይ ክለቡን ሲረከቡ ያገኟቸው እንደነ ኖርማን ዋይትሳይድ፣ ፖል ማግራዝ እና ብራያን ሮብሰን የመሳሰሉ የቡድኑ ከዋክብቶች በመጠጥ ሱስ ተይዘው ለያዥ ገናዥ ማስቸገራቸው ሥራቸውን ይበልጥ አከበደባቸው።
ክለቡን በተቀላቀሉ በሶስተኛው ሳምንት ደግሞ ወላጅ እናታቸውን በካንሰር ህመም ማጣታቸው የኦልድትራፎርድ ሕይወታቸውን ለሲኦል የቀረበ አደረገባቸው። በዚህ ሁሉ ግን ተስፋ አልቆረጡም። የሚያዩትን እያንዳንዱ ቀዳዳ ለመድፈን መላ መፈየድ ጀመሩ።
የስነምግባር ችግር የሚታይባቸውን ተጫዋቾች መረር ባለ ትዕዛዝ እና ጥብቅ መመሪያ አደብ እንዲገዙ አደረጉ። በአበርዲን አብረዋቸው የሚሰሩትን ምክትል አሰልጣኝም አስመጥተው በሥራቸው አደረጉ። ቀጣይ የለውጥ ምዕራፍ ያደረጉት እንደ ስቲቭ ብሩስ፣ ቪቭ አንደርሰን እና ብራያን ማክሌር ያሉ ድንቅ ተጫዋቾችን ማዘዋወር ነበር።
በዚህ ሁሉ ለውጥ ውስጥ የክለቡ ውጤት በሊጉ ደረጃዎችን ከማሻሻል በዘለለ ጠብ ያለ ሌላ ነገር አልነበረም። ይህ ሳያንስ ክለቡ ለ3 ዓመታት ያህል ያለ ዋንጫ አሳለፈ። ያን ጊዜ የመውጣታቸው ዜና መናፈቅ ጀመረ።
ከአሁን አሁን ተባረሩ ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት በ1989/90 የውድድር ዓመት መጠናቀቂያ የመጨረሻ ሰከንድ ላይ ለክለቡ የመጀመሪያ ዋንጫቸው የሆነውን የኤፍኤ ካፕ ዋንጫን በስጦታነት አበረከቱ።
ከዋንጫው ስኬት በኋላ ሁለተኛ ዕድል ተሰጣቸው። የኮሚዩኒቲሺልድ፣ የአውሮፓ አሸናፊዎች አሸናፊ እና ሊግ ካፕ (የአሁኑ ካራባዎ ካፕ) ዋንጫዎችን አከታትለው አሸነፉ። ይህን ጊዜ የኦልድትራፎርድ ዙፋናቸው ጸና። ከተቃውሞም ነጻ ሆነው ተረጋግተው ማሰልጠን ጀመሩ። የፕሪሚየር ሊጉ ጉዳይ ግን ከጥያቄ አልዘለለም።
1992/93 የውድድር ዘመን ተከተለ። ኤሪክ ካንቶና፣ ማርክ ሂውዝ፣ ፒተር ሽማይክል፣ ስቲቭ ብሩስ እና ወጣቱ ራያን ጊግስን የቀላቀለው ስብስብ ይዘው ተፋለሙ። ይህ የውድድር ዓመት ግን አዲስ ብስራት ይዞላቸው ከተፍ አለ። የፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮንነት።
ከዚህ ጊዜ በኋላ ፈርጉሰንን ማን ያቁማቸው። የእንግሊዙ ፈርጥ የነበረው ሊቨርፑል እንኳን በቀላሉ እጁን ሰጠ። እሳቸው ግን ደግመው ደጋግመው የዋንጫን ጣዕም አጣጣሙ። አኪሩ ሙሉ በሙሉ ወደ እሳቸው ተገለበጠ። መላውን እንግሊዝ በአንድ እግራቸው አቆሙ።
በሀገሪቱ ደረጃ የሚካሄዱ የክለብ ዋንጫዎችን ሁሉ ወስደው የኦልድትራፎርድን መደርደሪያዎች በዋንጫ ሞሉዋቸው። በ1998/99 ደግሞ የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን አሳክተው ሰራዊታቸው መላው አህጉሪቱን በበላይነት ተቆጣጠረ።
እንዲህ እንዲያ እያለ የሰር አሌክስ ፈርጉሰን ስኬት ለ27 ዓመታት ዘለቀ። ይሄ ስኬታቸው ደግሞ በማንም ሊደፈር በማይችል መልኩ ለዘመናት ሊቆይ የሚችል ሆኖ ነው የተጠናቀቀው። ጀብደኛው አሰልጣኝ በዩናይትድ በአጠቃላይ ከ49 በላይ ዋንጫዎችን አሳክተዋል። ይህን ያሳካ አሰልጣኝ በእግር ኳስ ታሪክ እስካሁን አልተፈጠረም።
13 የፕሪሚየር ሊግ፣ 10 ኮሚዩኒቲሺልድ፣ 5 ኤፍኤ ካፕ፣ 4 ሊግ ካፕ (ካራባዎ)፣ 2 አውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ፣ 1 የአውሮፓ የአሸናፊዎች አሸናፊ እና 1 የዓለም የክለቦች ዋንጫዎች ካሳኳቸው ስኬቶች መካከል ይገኙባቸዋል። ፈርጉሰን ይህንን ሊደገም የማይችል ጀብዱ ከሰሩ በኋላ ከነክብራቸው የእኔ አልጋ ወራሽ ይሆናል ብለው ላመኑት ሌላኛው ስኮትላንዳዊ አሰልጣኝ ዴቪድ ሞይስ አስረከቡና ዳግመኛ ላይመለሱ በጡረታ ተሰናበቱ።
ይሄ ነበር የማንችስተር ዩናይትድ ትክክለኛ ፈተና የጀመረው። በእርግጥ በዋንጫ አጀብ ክለቡ ተሟሙቆ ስለነበር ዴቪድ ሞይስ ስኬቱን አያስቀጥሉም ተብሎ አልታሰበም ነበር። ሞይስ አብዛኞቹን ከፈርጉሰን ጋር የነበሩትን ተጫዋቾች ይዘው ነበርና። ክለቡም በእሳቸው ላይ እምነት እንደነበረው የሚያሳብቀው የ6 ዓመታት ውል ማስፈረሙ ነበር።
ደጋፊዎች ደግሞ ለአሰልጣኙ ያላቸውን ድጋፍ ለመግለጽ በኦልድትራፎርድ “የተመረጠው ሰው” የሚል መልዕክት ያለው ጽሁፍ ይዘው ይታዩ ነበር። አሰልጣኙ የመጀመሪያ የውድድር ዘመናቸውን የኮሚዩኒቲ ሺልድ ዋንጫን ዊጋን አትሌቲክን 2ለ0 በማሸነፍ አሳኩ።
ይህ የበኩር ዋንጫ በሊጉና በሌሎች የአውሮፓ መድረክ ስኬቶች ሊከተል እንደሚችል የብዙዎች እምነት ነበር። ሊጉ እንደተጀመረም ዩናይትድ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ከውጤት ጋር ማሳየት ቻለ። በጨዋታ ሂደት ግን ቀስ በቀስ እየተንሸራተተ በመጨረሻ ውጤት ራቀው።
በኤፍኤ ካፕ በሶስተኛው ዙር ሲሰናበት በሊግ ካፕ (ካራባዎ ካፕ) በግማሽ ፍጻሜ በሰንደርላንድ ተሸንፎ ከውድድሩ ውጭ ሆነ። በፕሪሚየር ሊጉም በፈርጉሰን ዘመን ታይቶ የማይታወቅ የውጤት ቀውስ ውስጥ ሲገባ “የተመረጠው ሰው” ብለው ሞይስን ሲያቆለጳጵሱ የነበሩት ደጋፊዎች “የተሳሳተው ሰው፣ ሞይስ ውጣ” የሚል መልዕክት ይዘው በስቴዲየም መታየት ጀመሩ።
በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግም ወደ ግማሽ ፍጻሜ ቢደርሱም በደርሶ መልስ በባየር ሙኒክ ተሸንፈው የስንብት ዕጣ ደረሳቸው። በሊጉ ደግሞ በክለቡ የ10ኛ ወር ቆይታ እንዳደረጉ በኤቨርተን በመሸነፋቸው ከሁለት ቀናት በኋላ የስንብት ደብዳቤ ደረሳቸው።
ዴቪድ ሞይስ መሰናበታቸውን ተከትሎ 5 ሚሊየን ፓውንድ ካሳ ተከፈላቸው። ከእሳቸው በኋላ የክለቡ ጀብደኛ ራያን ጊግስ በጊዜያዊነት ቢረከብም የክለቡን የሊጉን ደረጃ ከሰባተኛነት ከፍ ሊያደርገው አልቻለም። ይሄኔ ሞይስ ክለቡን የኋሊት እንዲጓዝ ያደረጉት ትልቅ ክለብ የማሰልጠን ልምድ ስላልነበራቸው ነው ተባለ።
የኦልድትራፎርድ የአሰልጣኞች ድራማ ቀጠለ። የዩናይትድ ባለስልጣናት በ2014ቱ የዓለም ዋንጫ ከኔዘርላንድስ ብሄራዊ ቡድን ጋር ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ የነበረውን ልዊስ ቫንሃል ውድድሩን ሳያስጨርሱት እንዲፈርም ካስማሙት በኋላ ውድድሩ እንደተጠናቀቀ የ3 ዓመት ውል አስፈረሙት።
በአያክስ፣ በባርሴሎና እና በባየር ሙኒክ መልካም ስም የገነባው ቫንሃል ለዩናይትድ ትክክለኛው አሰልጣኝ እንደሆነ በዜማ ጭምር ይነገርለት ጀመር። አንደር ሄሬራ፣ ሉክ ሾው፣ አንሄል ዲማሪያ፣ ዴሊ ብሊንድ እና ራዳሜል ፋልካዎ የመሳሰሉ ከዋክብቶችን አስፈርሞም አዲሱን የውድድር ዘመን ጀመረ።
ቫንሃል ከጨዋታ ጨዋታ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ የሚያሳይ ቡድን ቢገነባም ውጤት ግን እሱንም ራቀችው። በሊጉ 4ኛ ደረጃን ሲያጠናቅቅ ያለምንም ዋንጫ የውድድር ዘመኑን ጨረሰ። ቀጣዩ ዓመት ተከተለ። አሁንም ከ1 የኤፍኤካፕ ዋንጫ ስኬት ውጪ ዩናይትድን የሚመጥን ስኬት ላይ መድረስ ተራራ የመግፋት ያህል ከበደው።
በፕሪሚየር ሊጉ አስከፊ ውጤት በማምጣቱና 5ኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቁ ለ3 ዓመታት የተፈረመው ውል ቀረና በ2ኛው ዓመቱ ተሰናበተ። ቫንሃልም የዩናይትድ ትክክለኛው አሰልጣኝ መሆን ሳይችል ቀረ።
ግንቦት 27/ 2017 ፖርቱጋላዊው ውጤታማ አሰልጣኝ ሆዜ ሞሪንሆ የማንችስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ የመሆናቸው ዜና ተሰማ። አሰልጣኙ የ3 ዓመታት ውል በመፈረም ነበር ክለቡን የተቀላቀሉት። የእሳቸው መምጣት የዩናይትድን ታላቅነት እንደሚመልስ የተጠራጠረ አልነበረም።
በአዲሱ የውድድር ዘመን ማማሟቂያቸውም የኮሚዩኒቲሺልድ ዋንጫን ሌስተር ሲቲን በማሸነፍ አሳኩ። ሊጉ እና ሌሎች ውድድሮች እየተጧጧፉ ሲመጡ ብዙም የማያስተች ውጤት ቢያስመዘግቡም ፕሪሚየር ሊጉን ያጠናቀቁት 6ኛ ደረጃን በመቆናጠጥ ነበር። በኤፍኤ ካፑ እና በኢውሮፓ ሊግ ግን ድል በመቀዳጀት የሁለትዮሽ ዋንጫ አሳኩ።
በቀጣዩ የውድድር ዘመን እንደነሮሜሉ ሉካኩ እና ቪክቶር ሊንድሎፍ የመሳሰሉ ተጫዋቾችን በማከል ጠንክረው ቢቀርቡም እያንዳንዱ ውድድር ቀላል ሆኖ አልጠበቃቸውም።
በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ገና ከ16ቱ የጥሎ ማለፍ ውድድር ተሰናበቱ። ኤፍኤ ካፕ እና ካራባዎ ካፕ ዋንጫዎችን ማሳካት ተሳናቸው። በሊጉ ደግሞ በተቀናቃኛቸው ማንችስተር ሲቲ በ19 ነጥብ ተበልጠው በሁለተኝነት አጠናቀቁ።
ከማንችስተር ጋር በሶስተኛው የውድድር ዘመናቸው ሞሪንሆ ይበልጥ አሽቆልቁለው ተገኙ። ቀስ በቀስ ውጤት እየራቃቸው መጣ። ይባስ ብሎ ከክለቡ ወሳኝ ተጫዋቾች ጋር በመልበሻ ክፍል መጋጨት አዘወተሩ።
ይህም በሂደት ለስንብት አበቃቸው። በ2018/19 የውድድር ዘመን በሊጉ ባደረጉት 17 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ሰባቱን ብቻ ነበር ማሸነፍ የቻሉት። የፈረንጆቹ ገና ሲቃረብም ኦልድትራፎርድን ለቅቀው ወጡ።
የእሳቸውን ስንብት ተከትሎ የቀድሞ የክለቡ ጀግና ኦሌጉናር ሶልሻየር ጊዜያዊ አሰልጣኝ ሆኖ ተሾመ። ሶልሻየር ከጨዋታ ጨዋታ አስደናቂ ብቃት እያሳየ በማሸነፉ የ3 ዓመት ውል እንዲፈርም ተደረገ። የውድድር ዘመኑን ግን ያለምንም ዋንጫ አጠናቀቀ።
ሶልሻየር ውጤት ያመጣበታል ተብሎ በታመነበት በቀጣዩ የውድድር ዘመንም ስኬታማ ሳይሆን ቀረ። 2020/21 የውድድር ዘመን ተከተለ። በቻምፒየንስ ሊጉ የምድብ ማጣሪያውን ማለፍ ተስኖት ወደ ኢውሮፓ ሊግ ወረደ። በኢውሮፓ ሊግ ደግሞ በፍጻሜው በስፔኑ ቪያሪያል በመለያ ምት ተሸንፎ ዋንጫውን ተነጠቀ። በፕሪሚየር ሊጉም ሆነ በሌሎች ውድድሮችም ድል ሳይቀናው ቀረ።
ቀጣዩ የውድድር ዘመንን ተጨማሪ 3 ዓመታት ውል አራዝሞ ቢቀጥልም ሊጉ በጀመረ በ4 ወራት ውስጥ በውጤት ማጣት ምክንያት ለስንብት በቃ። ከሶልሻየር ስንብት በኋላ ሌላኛው የዩናይትድ ጀግና ማይክል ካሪክ በጊዜያዊ ሞግዚትነት ተረከበ። ብዙም ሳይቆይ ጀርመናዊው ራፍ ራኚክ ለ6 ወራት ክለቡን አሰለጠኑ። በዚህ ሁሉ ውጤት ጠፋ።
ዩናይትድ 2022/23 የውድድር ዘመንን ከአያክሱ ውጤታማ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ጋር ብቅ አለ። ቴን ሃግ ከአያክስ ጋር ስኬታማ ጊዜ በማሳለፋቸው ለዩናይትድ ትክክለኛው አሰልጣኝ ተደርገው ተወሰዱ።
በተደራጀ የቡድን መዋቅር እና የሚፈልጓቸውን ተጫዋቾች በማስመጣት የኦልድትራፎርድን ሕይወት የጀመሩት ቴን ሃግ፣ በመጀመሪያው የውድድር ዘመናቸው ጠንክረው ቢቀርቡም በሊጉ ሶስተኛ ደረጃን ይዘው ነበር ያጠናቀቁት። በአንጻሩ የካራባዎ ካፕ ዋንጫን ማሳካታቸው እንደ ትልቅ ድል ተቆጠረላቸው።
በ2023/24 የውድድር ዘመን ደግሞ በሊጉ ዋንጫ ባያሳኩ እንኳን ተፎካካሪ ሆነው እንደሚቀርቡ ተጠብቆ ነበር። የታሰበው ሳይሆን ቀረና 8ኛ ደረጃን ከማጠናቀቃቸውም በላይ ከቻምፒየንስ ሊጉ ሳይቀር በጊዜ ተሰናበቱ። ብቸኛ መጽናኛቸው የነበረው የኤፍኤ ካፕ ዋንጫን ተቀናቃኛቸውን ማንችስተር ሲቲ አሸንፈው ማሳካታቸው ነበር። ይህም ከመባረር ለጥቂት አዳናቸው።
ኤሪክ ቴን ሃግ 2024/25 የውድድር ዘመንን የተሻለ የውጤት ተስፋ ሰንቀው ነበር የጀመሩት። ይሁን እንጂ ጥሩ ብስራት ይዞላቸው አልመጣም። በተለይም በሊጉ ከጨዋታ ጨዋታ በመሸነፍ መጥፎ ታሪክ ማስመዝገባቸውን ቀጠሉ። ቡድናቸው በ7 ጨዋታዎች 8 ነጥብ ብቻ በመሰብሰብ 14ኛ ደረጃ ላይ መገኘቱ ለስንብት አበቃቸው። እሳቸውም የውጤት እርግማን ተጠቂ ሆነው ከኦልድትራፎርድ በውርደት ተሸኙ።
ከቴንሃግ በኋላ የእሳቸው ምክትል የነበረው የቀድሞው የክለቡ ጀብደኛ ሩድ ቫንኒስትልሮይ በጊዜያዊነት ተተካ። የኒልስትልሮይ ቆይታም በጣት ከሚቆጠሩ ጨዋታዎች አልዘለለም።
በአዲሱ ፖርቱጋላዊው ወጣት አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም ተተካ። ወጣቱ አሰልጣኝ ከሚከተለው ውብ የእግር ኳስ አጨዋወት ፍልስፍና እና ለአሸናፊነት የሚያበቃ ታክቲክ በመነሳት ዩናይትድ በስተመጨረሻ የአሌክስ ፈርጉሰንን ተተኪ ማግኘቱ ታምኖበት ነበር።
እምነት እንዲያገኝ ያስቻለው የቀድሞው ክለቡን ስፖርቲንግ ሊዝበን ከሀገሪቱ ትላልቅ ክለቦች ፖርቶ እና ቤነፊካ መንጋጋ ነጥቆ ሁሉንም የሀገር ውስጥ ዋንጫዎች እንዲያነሳ ማድረጉ ነበር። ትንሹን ነገር ማግዘፍ የሚቀናቸው የእንግሊዝ ሚዲያዎችም ያለ መታከት ስለታላቅነቱ አወሩ።
ብዙም ሳይቆይ አሞሪ በሜዳ ውስጥ እንቅስቃሴ መፈተን ጀመረ። አጀማመሩ መልካም ቢመስልም ጨዋታዎች እየበዙ ሲሄዱ የእሱም ስም በሽንፈት ምክንያት ማደፍ ጀመረ። ዩናይትድም ከሚያሸንፈው በላይ የሚሸነፋቸው ጨዋታዎች በእጅጉ በዙ።
ከጨዋታ ጨዋታ ሽንፈት የዩናይትድ መለያ እስኪመስል ድረስ ተከታተለ። በዚህም ምክንያት አሞሪም የአሰልጣኝነት ሕይወቴ መጥፎ ጊዜ ይሄ ነው ሲል ስሜቱን ሳይደብቅ በአደባባይ ተናገረ።
አሁንም የተለወጠ ነገር የለም። ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ አሞሪም በዩናይትድ በፕሪሚየር ሊጉ 16 ጨዋታዎችን አድርጎ ማሸነፍ የቻለው 5 ጨዋታዎችን ብቻ ነው። በ8ቱ ተሸንፏል። 5ቱን ደግሞ በአቻ ውጤት አጠናቅቋል። በሊጉ 14ኛ ደረጃ ላይ ተገኝቷል።
አሞሪም በክለቡ በአጠቃላይ ካደረጋቸው ጨዋታዎች፣ የማሸነፍ ንጻሬው 43.48 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ይህም አሰልጣኙ በተጠበቀው ልክ እንዳልሆነ ያመላከተ ነው፡፡
የእንግሊዙ ገናና ክለብ፣ አሁንም ከውጤት ጋር ሆድና ጀርባ ሆኗል፡፡ ከሰር አሌክስ ፈርጉሰን በኋላ 6 ቋሚና 4 ጊዜያዊ አሰልጣኞችን ቢቀጥርም የቀድሞ ገናናነቱን መልሶ ማግኘት አልቻለም፡፡
ታዲያ የስኬት ቁልፉን ሰር አሌክስ እንዳይገኝ አድርገው ይዘውት ጠፍተው ይሆን? እስካሁን ምላሽ ያልተገኘለት ጥያቄ ነው፡፡
More Stories
አማራጭ የኢነርጂ ልማት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል
የብዙ ሰዎችን ደጅ ፀንቻለሁ – አቶ አብደላ ላራጎ
“አንባቢ ያደረገኝ አባቴ ነው” – ወይዘሮ ይመኙሻል አየለ