የሥራ ሥነምግባርን መጠበቅ ግንባር ቀደም ተግባሬ ነው – አቶ ለገሠ ኃይለማሪያም

የሥራ ሥነምግባርን መጠበቅ ግንባር ቀደም ተግባሬ ነው – አቶ ለገሠ ኃይለማሪያም

በአብርሃም ማጋ

የዛሬው ባለታሪካችን አቶ ለገሠ ኃይለማሪያም ናቸው፡፡ በርዕሱ ላይ የገለፁትን ሐሳብ ለማንኛውም ሥራ የሥራ ሥነምግባርን መጠበቅ መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን በመግለፅ ያጠናክራሉ፡፡

የሥራ ሥነምግባሮችን ሲያብራሩ የሥራ ሰዓትን ማክበር፣ ጤናማ የሥራ ግንኙነቶችን መፍጠር፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን ተከትሎ መሥራት፣ ሐላፊነትን በአግባቡና በተገቢው ሁኔታ መወጣት፣ ከአድሎአዊነት የፀዳና ሁሉንም ያማከለ አሠራርን መከተል ተሳትፏዊነትን ማጐልበት እና ሌሎችም ዋንኞቹ እንደሆኑ ያብራራሉ፡፡

በመሆኑም አቶ ለገሠ የሥራ ሰዓታቸውን ለሥራ ብቻ ሲያውሉት ማርፈድ፣ ሰዓት ሳይደርስ መውጣት እና ያለ ምክንያት ከሥራ መቅረት የመሳሰሉት ጉዳዮች እንደማይወክላቸው በመግለፅ ነበር ሃሳባቸውን አክለው የተናገሩት፡፡

በትልቅ ሐላፊነት በሠሩባቸው ጊዜያት ቅድሚያ የሚሰጡት ምቹ የሥራ ቦታ መፍጠር ላይ ነበር፡፡ ለሠራተኞቻቸው ምቹ የሥራ ድባብ መፍጠራቸው ደግሞ ሰራተኞቻቸው ሳይሸማቀቁ በነፃነት ተደስተው ሥራቸውን በተገቢው ሁኔታ በመሥራት ለሥራው ስኬት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ ሳይገልፁ አላለፉም፡

አቶ ለገሠ ኃይለማሪያም በቀድሞው አስተዳደራዊ መዋቅር በሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት፣ በሲዳማ አውራጃ ሸበዲኖ ወረዳ፣ በሞሮቾ ነጋሻ ቀበሌ በ1958 ዓ.ም ተወለዱ፡፡እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ገና በአምስት ዓመታቸው የመማር እድል ገጠማቸው፡፡

በመሆኑም በለኩ ከተማ ልእልት ተናኘ ወርቅ ት/ቤት ገብተው ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ተምረዋል፡፡ በወቅቱ በትምህርታቸው በጣም ጐበዝ ተማሪ በመሆናቸው ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ተምሮ ለማጠናቀቅ 6 ዓመት ብቻ ፈጅቶባቸዋል፡፡

በወቅቱ ጐበዝ ተማሪዎችን በዓመት ሁለቴ ማሳለፍ /ደብል ፕሮሞሽን/ ስለሚፈቅድ 2ኛ እና 3ኛ ክፍሎችን በአንድ ዓመት ተምረዋል። በመቀጠልም 4ኛ እና 5ኛ ክፍሎችን በአንድ ዓመት ውስጥ ተምረው በአጠቃላይ 8ኛ ክፍልን የጠናቀቁት በ6 ዓመት ብቻ ነበር፡፡

በ1972 ዓ.ም ላይ በ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ላይ 99 ነጥብ 8 ከመቶ በማምጣት ነበር ወደ 9ኛ ክፍል የተዛወሩት፡፡

ከ9ኛ ክፍል 12ኛ ክፍል የተማሩት በይርጋዓለም አጠቃላይ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ሲሆን ከክፍልና ከአጠቃላይ 1ኛ ደረጃ መውጣት ችለዋል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ካሉት 2ዐ ጐበዝ ተማሪዎች ሲመለመሉ ከ20ዎቹም እሳቸው በአብዛኛው በ2ኛ ደረጃ ይመሩ ነበር፡፡

በዚሁም በ1976 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና 3 ነጥብ 2 በማምጣት አዲስ አበባ 6 ኪሎ ዩኒቨርሲቲ መግባታቸውን መረጃቸው ያመለክታል፡፡

በ1977 ዓ.ም በአዲስ አበባ 6 ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በሶሻል ሳይንስ ተመድበው የ1ኛ ዓመት ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በሁለተኛ ዓመት ላይ የትምህርት ክፍል መረጣ አድርገዋል፡፡

በዚሁም የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ፅሑፍ /አማርኛ/ ትምህርት ክፍል ደርሷቸው ከተማሩ በኋላ በ1980 ዓ.ም በመጀመሪያ ዲግሪ በከፍተኛ ውጤት ተመርቀዋል፡፡

በመሆኑም የኢኮኖሚ ፕላን ኮሚሽን ውስጥ እጣ ሲያወጡ ትምህርት ሚኒስቴር ደርሷቸው፣እንደገና ትምህርት ሚኒስቴር ሄደው እጣ ሲያወጡ ወሎ ክፍለ ሃገር ዋግ አውራጃ የሰቆጣ ወረዳ አጠቃላይ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአማርኛ መምህርነት ተመደቡ፡፡

ይሁን እንጂ በወቅቱ ከተማዋ በኢህአዴግተይዛስለነበር ሌላ ትምህርት ቤት ቅያሪ ተደርጐላቸው ሰሜን ወሎ አውራጃ ኮረም አጠቃላይ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተመድበው በቋንቋ መምህርነት ከ1981 ዓ.ም እስከ 1982 ዓ.ም ድረስ ለሁለት ዓመታት የ11ኛ እና የ12ኛ ክፍል መምህር ሆነው ሠርተዋል፡፡

በ1983 ዓ.ም አሁንም ከተማዋ በኢህአዴግ ጦር ቁጥጥር ስር ስትሆን ወደ አዲስ አበባ ተዛውረው ሰበታ አጠቃላይ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመድበው ለአንድ ዓመት አስተምረዋል። ወቅቱ የኢህአዴግ መንግስት ደርግን አሸንፎ ስልጣን የያዘበት ሲሆን እሳቸውም በክረምት ወቅት ትምህርት ቤቱ ሲዘጋ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ወደ ሸበዲኖ ወረዳ ተመለሱ፡፡

እንደተመለሱ በኢህአዴግ ፖለቲካ ውስጥ በመሳተፍ በፖለቲካ አደረጃጀት ውስጥ ገብተው በሸበዲኖ ወረዳ አስተባባሪ ኮሚቴ ሆነው ተመድበው ለ5 ወራት ከሠሩ በኋላ የሲዳሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት /ሲህዴድ/ ተመሠረተ፡፡በዚሁም እሳቸው የድርጅቱማዕከላዊ ኮሚቴ ሆነው ተመረጡ፡፡

በ1984 ዓ.ም ደቡብ በአምስት ክልሎች ሲከፋፈል እሳቸው በክልል 8 ውስጥ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሆነው ተመረጡ፡፡
በተመረጡት ሃላፊነት አንድ ዓመት ከሠሩ በኋላ 5ቱ ክልሎች በደቡብ ክልል ሲጠቃለሉ በ1985 ዓ.ም እሳቸው የደቡብ ክልል ማስታወቂያ ቢሮ ሐላፊ ሆነው ተሾሙ፡፡ በቢሮው የመጀመሪያ ተሿሚ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከ1985 ዓ.ም እስከ 1987 ዓ.ም ድረስ ለ3 ዓመታት ያህል በቢሮ ሃላፊነት ከሠሩ በኋላ በ1987 ዓ.ም በሰኔ ወር ላይ ወደ ሲዳማ ዞን ተዛውረው የኢኮኖሚ ጉዳይ ተጠሪ ሆነው ተሹመው ለአንድ ዓመት አገልግለዋል፡፡

የማስታወቂያ ቢሮ ኃላፊ ሆነው በሠሩባቸው ጊዜያት በርካታ ሥራዎችን አከናውነዋል፡፡ለአብነት ያህል የሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች የማስታወቂያ መምሪያዎችና ጽህፈት ቤቶች እንዲቋቋሙ መዋቅር ዘርግተዋል፡፡

የክልሉ ማስታወቂያ ቢሮ እንዲደራጅ ከማስታወቂያ ሚኒስቴር ጋር ጥሩ ግንኙነት በመፍጠር ለቢሮው፣ ለመምሪያዎችና ለጽህፈት ቤቶች የሎጅስቲክ ድጋፍ እንዲገኝ አድርገዋል፡፡ጽህፈት ቤቶችና መምሪያዎች የሚዲያ ሽፋን እንዲያገኙ በማድረግ ረገድም ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡

ለእሳቸው የተሰጣቸውን ተሽከርካሪ ለሪፖርተሮችና ለካሜራ ባለሙያዎች በመስጠት በክልሉሁሉም አካባቢዎች ተዘዋውረው መረጃ በመሰብሰብ በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን እንዲሰራጩ በማድረግ ረገድ ላቅ ያለ ሚና ተጫውተዋል፡፡

አቶ ለገሠ ከራሳቸው ምቾት ይልቅ ቅድሚያ ለሥራው በመስጠታቸው ተሽከርካሪያቸውን ለመስክ ሥራ ሰጥተው እሳቸው በብስክሌት ይሄዱም ነበር፡፡ አሊያም በእግራቸው ሁሉ እንደሚሄዱ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በወቅቱ በቢሮው ከአራት መምሪያዎች አንዱ የሆነውን የፕሬስ መምሪያ የህትመት ውጤት እንዲያዘጋጅ ማለትም የደቡብ ንጋት በሚሰኝ ስያሜ እንዲታተም ንድፍ በማበጀት መሠረት የጣሉት እሳቸው ነበሩ፡፡ በሌላ አነጋገር ጋዜጣው ህጋዊ እውቅና አግኝቶ ለመታተም የበቃው እሳቸው ባስቀመጡት እቅድ መሠረት ነበር፡፡

እንደ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነታቸው ደግሞ ከሌሎች የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን የሲዳማ ህዝብ በወቅቱ በፖለቲካ አደረጃጀት ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆን የበኩላቸውን ድርሻ ተወጥተዋል፡፡

የሲዳማ ህዝብ በ1987 ዓ.ም የፀደቀው የሃገሪቷን ህገ መንግስት ተጋሪና ተጠቃሚ እንዲሆን የማንቃትና የማሳተፍ ሥራ ሠርተዋል፡፡

አቶ ለገሠ ኃ/ማሪያም ከላይ የተጠቀሱትን ተግባር ካከናወኑ በኋላ ከ1988 ዓ.ም እስከ 1992 ዓ.ም ድረስ የሲዳማን ህዝብ በመወከል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነው ለ5 ዓመታት በማገልገል የተሰጣቸውን ሃላፊነት በብቃት ተወጥተዋል፡፡

ከ5 ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ ክልላቸው ተመልሰው በ1993 ዓ.ም በፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ በኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ኤክስፐርት በመሆን ተመድበው እስከ 2010 ዓ.ም ለ17 ዓመታት ያህል አገልግለዋል፡፡

በ2011 ዓ.ም የትምህርት ደረጃቸውን ለማሻሻል በወጣው ማስታወቂያ መሠረት ተወዳድረው በማለፍ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ገብተው ለሁለት ዓመታት ተከታትለው በዲፕሎማሲና አለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት በሁለተኛ ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡

ከዚያም በ2015 ዓ.ም የደቡብ ክልል በተለያዩ አደረጃጀቶች ከመከፋፈሉ ሁለት ወር አስቀድሞ በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ውስጥ በገቢዎች ባለስልጣን በኮሙኒኬሽን ጉዳዮች የህዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ በመሆን ተቀላቅለዋል፡፡ እስከ አሁንም ድረስ በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡

በቀድሞው በደቡብ ክልል ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኤክስፐርት ሆነው በሠሩባቸው ጊዜያት ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን በርካታ ሥራዎችን ማከናወናቸውን ያወሳሉ፡፡

ለአብነት ያህል በ1995 ዓ.ም ላይ የመጀመሪያውን ፋይናንስና ልማት የሚል መጽሔት መሥርተዋል፡፡ በዲጂታልም ሆነ በፕሬስ ሚዲያ አርቲክሎችን፣ ዜናዎችንና የተለያዩ ሙያዊ የሆኑ ምስሎች /ፎቶዎች/ እንዲወጡ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡

በቢሮው በኮሙኒኬሽን ጉዳዩች ላይ የተመሠረቱ ፖሊሲ፣ መመሪያና ደንብ በሚዲያ እንዲተላለፍ ከደቡብ ሚዲያ ጋር በማቀናጀት የተሳካ ሥራ ሠርተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በረጅም ዓመታት ያበረከቱትን ልምድ ይዘው የክልሉን በተለይም የገቢዎች ባለስልጣን ተግባራት ለሚዲያና ለኮሙኒኬሽን እንዲበቃ በማድረግ ሙያዊ ግዴታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ፡፡

በሃላፊነትና በሙያተኛነት በሠሩባቸው ጊዜያት ከሠራተኞቻቸውና ከሃላፊዎቻቸው ጋር ጥሩ የሥራ ግንኙነት ነበራቸው፡፡ በሃላፊነት በሠሩባቸው ጊዜያት ከሁሉም ነገር በላይ ለባለሙያዎች ቅድሚያ ይሰጣሉ፡፡

ምክንያቱም የቢሮውን ዓላማ የሚያስፈጽሙት በዋናነት ባለሙያዎች መሆናቸውን ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ሪፖርተሮች የሚዲያ ሽፋን እንዲሰጡ ወደተለያዩ አቅጣጫዎች ይላካሉ፡፡ ሰብስበው ያመጡትን መረጃ በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን እንዲተላለፍ እንዲያደርሱ ይልካሉ፡፡ የቢሮው ሥራ ማስኬጃ ገንዘብ በአብዛኛው ለሪፖርተሮቻቸው በአበል መልክ ይሰጣሉ፡፡ ለራሳቸው የተሰጣቸውን አንዲት ተሽከርካሪ ለሪፖርተሮቹ አቀናጅተው ይሰጣሉ፡፡

ሪፖርተሮቹ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ሄደው የሚዘግቡ ከሆነ ከሌሎች ቢሮዎች በውሰት መኪና ወስደው ያሰማራሉ፡፡ ሪፖርተሮች በቢሮ ውስጥ እንዲያሳልፉ በጭራሽ አይፈልጉም፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ በዋናነት ይከተሉ የነበረው “ጋዜጠኛ ሥራ ፍለጋ ይሄዳል እንጂ ሥራ ጋዜጠኛን እየፈለገ አይመጣም” የሚል መርህ ይዘው ነው፡፡

ሁሉንም ሠራተኛ ያማከለና ከአድሏዊነት የፀዳ አሠራር ይከተላሉ፡፡ ሠራተኛን ከሠራተኛ ማበላለጥና ማሳነስ በፍፁም አይታይባቸውም። ሠራተኞቻቸውን በአባታዊ መርህ ይመራሉ። በቁጣ ከማሸማቀቅ ይልቅ ጥፋት የሚፈጽሙ ሠራተኞችን አባታዊ ምክር ሰጥተው ያስተምራሉ፡፡

ሰውን ማስቀየምና ማስቆጣት በፍፁም አይወዱም፡፡ ሰራተኞቻቸውን ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ሰው ላይ በደል መፈጸም አይወዱም። ለዚህም ይመስላል “አንድም ቀን ከሰው ጋር ተጣልቼና ተጋጭቼ አላውቅም” ያሉት። አቶ ለገሠ ጋ ሁሌ ከሰዎች ጋር መጫወትና መሳቅ ብቻ ይታይባቸዋል፡፡ ክፋት የሚባል ነገር በፍፁም የተቸራቸው ሰው አይደሉም፡፡

ሰውን ማፍቀር፣ ጓደኛን ማብዛት፣ ትህትና፣ መግባባት፣ መተባበር፣ የዋህነት እና የተቸገረውን በተቻላቸው መጠን መርዳት ልዩ ባህሪያቸው እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በሙያቸው ያካበቱትን እውቀት ለሌሎች የማካፈልና የማብቃት ሥራም ልዩ ባህሪያቸው እንደሆነም ሳይገልፁ አላለፉም፡፡

ለሥራ ያላቸውን ፍቅር ተጠይቀው የሰጡት ምላሽ ቢኖር፡- “የሥራ ሥነምግባርን ጠብቆ የመንግስት ሥራን በማክበር እሠራለሁ” ይላሉ፡፡