ፒኤስጂ ከሊቨርፑል እንዲሁም ባየርንሙኒክ ከባየርሊቨርኩሰን ዛሬ ምሽት የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል

ፒኤስጂ ከሊቨርፑል እንዲሁም ባየርንሙኒክ ከባየርሊቨርኩሰን ዛሬ ምሽት የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል

የአውሮፓ ሻምፒዮንስሊግ የመጀመሪያው ዙር የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ዛሬ ምሽትም መካሄዳቸውን ሲቀጥሉ ፒኤስጂ ከሊቨርፑል እንዲሁም ባየርሙኒክ ከባየርሊቨርኩሰን ጋር ዛሬ ምሽት 5 ሰዓት ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

በፈረንሳይ ርዕሰ መዲና ፓሪስ ላይ በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኙት ፒኤስጂ እና ሊቨርፑል በፓርክ ዴ ፒሪንስ ይፋለማሉ።

በአሰልጣኝ ሊውስ ኤንሪኬ የሚመራው ፒኤስጂ በፍሬንች ሊግ በ24 ጨዋታ ምንም ሳይሸነፍ በ13 ነጥብ ልዩነት መሪ ሆኖ ይገኛል።

በሻምፒዮንሊጉ ምንም እንኳን እንደ ዛሬው ተጋጣሚው በቀጥታ ወደ 16 ውስጥ ማለፍ ባይችልም በሌላ ጥሎ ማለፍ የሀገሩን ክለብ ብረስትን 10ለ0 በሆነ በድምር ውጤት ረቶ እዚህኛው ዙር ላይ መድረሱ ይታወቃል።

በአሰልጣኝ አርኔ ስሎት የሚመራው ሊቨርፑል እንደ ፒኤስጂ ሁሉ ሊጉን በ13 ነጥብ ከመምራቱ በተጨማሪ የሻምፒዮንስሊጉን የምድብ ማጣሪያ በአንደኝነት አጠናቆ ወደ ጥሎ ማለፉ በቀጥታ መሻገሩ የሚታወስ ነው።

ሁለቱም ክለቦች በዘንድሮው ዓመት በሁሉም ውድድሮች በተመሳሳይ 101 ግቦችን በተጋጣሚያቸው መረብ ላይ አሳርፈዋል።

በሊቨርፑል በኩል ሞሐመድ ሳላህ በፒኤስጂ በኩል ኦስማን በምሽቱ ጨዋታ የበርካቶች አይን ማረፊያ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ግብፃዊው አጥቂ በያዝነው ዓመት በሁሉም ውድድሮች ለመርሲሳይዱ ክለብ 52 የጎል ተሳትፎ አድርጓል።

የ33 ዓመቱ ተጫዋች 30 ጎሎችን አስቆጥሮ 22 የመጨረሻ ኳሶችን በማቀበል ከክለቡ ጋር ምርጥ የውድድር ዓመትን በማሳለፍ ላይ ነው።

በፈረንሳዩ ክለብ በኩል ደግሞ በአንድ ወቅት የዓለማችን ውድ ፈራሚዎች መካከል አንዱ የነበረው ኦስማን በእግር ኳስ ተጫዋችነት ዘመኑ አስደናቂ ብቃቱ ላይ ይገኛል።

የ27 ዓመቱ ተጫዋች ዘንድሮ ለክለቡ እስካሁን 26 ጎሎችን አስቆጥሮ 6 የመጨረሻ ኳሶችን ማቀበል ችሏል።

ሁለቱ ክለቦች በሻምፒዮንስ ሊጉ ለ3ኛ ጊዜ ይገናኛሉ።

ከ6 ዓመታት በፊት በምድብ ማጣሪያው ተገናኝተው ሁለቱም በየሜዳዎቻቸው አሸናፊ እንደነበሩ ይታወሳል።

በሌላ የምሽቱ ተጠባቂ መርሃ-ግብር የጀርመን ክለቦች ባየርን ሙኒክ እና ባየርሊቨርኩሰን በተመሳሳይ ሰዓት በአሊያንዝ አሬና ስታዲየም ወደ ሩብ ፍፃሜው ለማለፍ ይፋጠጣሉ።

ሁለቱ ክለቦች ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ የሚገናኙ ይሆናል።

በቡንደስሊጋው ሁለቴ ተገናኝተው በአቻ ውጤት ሲለያዩ በዲኤፍቢ ፖካል ካፑ ሌቨርኩዝን የ1 ለ ዐ አሸናፊ ሆኗል።

በተጨማሪም በተመሳሳይ 5 ሰዓት ላይ በስታዲዮ ዳሉዥ ቤኔፊካ ከባርሴሎና ይጫወታሉ።

በያዝነው ዓመት ሁለቱ ክለቦች በምድብ ማጣሪያው እዚሁ ስታዲየም ላይ ተገናኝተው አዝናኝ በነበረው ጨዋታ ባርሴሎና 5ለ4 ማሸነፉ ይታወሳል።

ከነዚህ 3 ጨዋታዎች ቀደም ብሎ ምሽት 2 ከ 45 ሰዓት ላይ በዴ ኩፕ ስታዲየም ፌዬኖርድ ከኢንተር ሚላን ይፋለማሉ።

በሮተርዳሙ ክለብ በኩል አሰልጣኝ ሮበን ቫንፔርሲ የልጅነት ክለቡን እየመራ በአሰልጣኝነት የመጀመሪያውን የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታውን ያከናውናል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ