የቱሪዝም ዘርፉ ስኬቶች
በደረሰ አስፋው
የሰው ዘር መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ በቱሪዝም ሀብታቸው ከሚታወቁ የዓለም ሀገሮች አንዷ ናት። ሁሉም ዓይነት የቱሪዝም ሀብቶች ያሉባት በመባልም ትታወቃለች። በአያሌ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መስህቦቿ፣ ብሔራዊ ፓርኮቿ፣ ደማቅ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ሥርዓቶቿ ትታወቃለች።
የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የጎንደር አብያተ መንግሥት፣ የአክሱም ሀውልት፣ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ የጥያ ትክል ድንጋይ፣ የጀጎል ግንብ፣ የመስቀል ደመራ እንዲሁም የጥምቀት በዓላት፣ የገዳ ሥርዓት፣ ፍቼ ጫምባላላ፣ የኮንሶ መልክአ ምድር፣ የታችኛው አዋሽ ሸለቆና የታችኛው የኦሞ ሸለቆ፣ የጌዴኦ መልክዓ ምድር እና የባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ፣ እንዲሁም የሀረሪ ብሔረሰብ የሸዋሊድ በዓል በዩኔስኮ ተመዝግበዋል።
በዩኔስኮ የተመዘገቡ የሀገሪቱ ቅርሶች ቁጥር ከ13 ወደ 16 አድገዋል። እነዚህ በዩኔስኮ የተመዘገቡ ቅርሶች የዓለምም ቅርስ በመሆን ሀገሪቱን የቅርሶች ባለጸጋ አድርጓታል። በዓለም በርዝመቱ ትልቁ የሆነው የዓባይ ወንዝ /ናይል/ መነሻም ኢትዮጵያ፣ የበርካታ ሐይቆች፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች መገኛም ናት፤ በዚህም የውሃ ማማ በመባል ትታወቃለች።
ብርቅዬ አእዋፋትና አራዊቶችን በማቀፍ በዓለም ደረጃ በከፍታውና በቅዝቃዜው የሚታወቀው ራስ ዳሸን ተራራ፣ በዓለም ዝቅተኛው ስፍራ በመባል የሚታወቀው የዳንክል ሞቃታማ ስፍራ እና ሌሎች በቱሪስት መዳረሻነታቸው የሚታወቁ ስፍራዎች ናቸው።
ናሽናል ጂኦግራፊ ዩኬ በጥር ወር ጉዞ ሊደረግባቸው ከሚገቡ አምስት ሀገሮች መካከል ኢትዮጵያን በግንባር ቀደምትነት ጠቅሷል፡፡ በተጠቀሰው ወር በላሊበላና ጎንደር የገናና ጥምቀት በዓላት በድምቀት የሚከበሩ መሆናቸውንም ጠቁሟል።
የቱሪዝም ዘርፉ ይህ ሁሉ እምቅ አቅም እንዳለው የተገነዘበው መንግሥትም በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የአስር ዓመቱ መሪ እቅድ ዘርፉን የምጣኔ ሀብቱ ምሰሶ ካላቸው አምስት ዘርፎች አንዱ ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ለቱሪስት መዳረሻ ሊሆኑ የሚችሉ የተለያዩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተገንብተው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ በገበታ ለሸገር ፕሮጀክት በአዲስ አበባ ከተማ የተገነቡት የአንድነት፣ የወዳጅነትና የእንጦጦ ፓርኮች የከተማዋና የሀገሪቱ የቱሪስት መስህብ መሆን ችለዋል።
ገበታ ለሸገር ወደ ገበታ ለሀገር ተሸጋግሮ በወንጪ፣ በጎርጎራ እና በኮይሻ ልማቱ ተስፋፍቷል። የኮይሻ አካል የሆነው የሀላላ ኬላ ሪዞርት ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል። ሀላላ ኬላ ሪዞርት የዳውሮ ንጉስ ያስጀመረውና ለ300 ዓመታት የዳውሮ ነገሥታት እየተቀባበሉ እንደገነቡት የሚነገርለት ግንብ፣ የጊቤ ሶስት ግድብ በሚገኝበት ውብ የተፈጥሮ ሀብት ባለበት አካባቢ የተገነባ ነው።
በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት ደግሞ ወደ ስምንት በሚደርሱ አካባቢዎች ላይ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ግንባታዎች እየተካሄዱ ይገኛል። እነዚህ የቱሪስት መዳረሻዎች የቱሪዝም ዘርፉን በእጅጉ የሚያነቃቁና ለበርካታ ዜጎችም የሥራ እድል የፈጠሩ ናቸው።
ኢትዮጵያ ምንም እንኳ በተፈጥሮ፣ ሰው ሰራሽ እና ባህላዊ መስህቦቿ በአለም ብትታወቅም፣ በርካታ መስህቦችንም በዩኔስኮ ብታስመዘግብም፣ በዘርፉም ቢሆን ከአፍሪካ ቀዳሚ ስፍራ ላይ ብትሆንም፣ ከዚህ ሁሉ ጸጋዋ ግን የሚገባትን ያህል ጥቅም እያገኘች አይደለችም። ሀገሪቱ ከዚህ ቁጭት በመውጣት ይህን ሁኔታ የሚቀይር ከቱሪዝም ዘርፍ ተገቢውን ተጠቃሚነት የሚያመጣ ተግባር እያከናወነች ትገኛለች።
ለዚህም ዘንድሮ ለአንድ ወር የዘለቀና ስኬታማ ሆኖ የተጠናቀቀ የቱሪዝም ኤግዚቢሽንና ሆስፒታለቲ አውደ ርዕይም አጋዥ ነው። ይህ አውደ ርዕይ ክልሎች ጭምር የቱሪስት መስህቦቻቸውን ያስተዋወቁበት፣ የሸጡበት፣ እርስ በርስ ልምድ የተለዋወጡበት መሆኑ ተነግሮለታል።
በቱሪዝም ሀብቱ እና ልማቱ እንዲሁም ተግዳሮቶቹና መፍትሔዎች ላይ ምክክር አድርገውበታል። በአውደ ርዕዩ ከ160 ሺህ በላይ ሰዎች በአካል ተገኝተው እንደጎበኙት፣ ከዘጠኝ ሚሊየን በላይ በሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በተለያዩ የዲጂታል አማራጮችና በመገናኛ ብዙሃን ስለመጎብኘቱም የቱሪዝም ሚኒስቴርን ዋቢ ካደረጉ መገናኛ ብዙሃን የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
ከጥቂት ዓመታት በፊት የወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ቱሪዝም በየዓመቱ በአራት በመቶ እያደገ ይገኛል። በዓለም ከሚፈጠሩ አስር የሥራ እድሎች አንዱ በቱሪዝም ዘርፍ የሚፈጠር ነው፤ ዘርፉ ለዓለም አጠቃላይ እድገትም 10 በመቶ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው። ቱሪዝም የገቢ ምንጭ ከመሆኑም ባለፈ ሀገርን ከሌሎች የዓለም አገሮች ጋር ለማስተዋወቅና የሀገርን በጎ ገጽታ ለማሳየት ይረዳል፡፡
ክልሎችም በተመሳሳይ ያሉ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ጸጋዎችን በማልማትና በማስተዋወቅ ረገድ የማይናቅ ተግባር እያከናወኑ ነው፡፡ በዚህ ጽሁፍም ለመዳሰስ የሞከርነው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልን ነው፡፡
ክልሉ በቅርቡ የተቋቋመ አዲስ ክልል ነው፡፡ ይሁን እንጂ የቱሪስት መዳረሻ የሆኑ ጸጋዎችን በማልማት የሀብት ምንጭ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ነው ከክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
እንደ መረጃ ምንጫችን ከሆነ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ከክልሉ ዲዛይንና ግንባታ ቁጥጥር ድርጅት ጋር የቱሪዝም ስፍራዎችን ማልማት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ የመግባቢያ የግብ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡ በዚህም ክልሉን የቱሪዝም መዳረሻ ተምሳሌት ለማድረግ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል አንዱ ነው፡፡
በክልሉ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ ከ305 ሺህ በላይ ጎብኚዎች ጉብኝት በማድረግ በቱሪዝም ዘርፉ ከ488 ሚሊዮን ብር በላይ ቀጥተኛ ያልሆነ ገንዘብ ተንቀሳቅሷል፡፡ የክልሉ ከተፈጥሮ ጸጋዎቹ መካከል ፓርኮች፣ ወንዞች፣ ፏፏቴዎች እና ሀይቆች ይጠቀሳሉ። ፓርኮቹ የአያሌ የዱር እንስሳትና አእዋፋት እንዲሁም እጽዋት መገኛ በመሆናቸው ለቱሪስት መስህብ ሊውሉ የሚችሉ ተራራዎች፣ ዋሻዎች በብዛት ይገኙበታል።
ክልሉ ካለው አንጻራዊ ሰላም እንዲሁም ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት መገኘቱ ለቱሪዝም ልማት አመቺ ነው፡፡ በዚህም መስህቦችን በተገቢው በማልማት የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ በማራዘም የገቢ አቅምን ማሳደግ ይቻላል። በመዳረሻ ልማት ስራዎች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በጥናት በመለየት ማልማት ይገባል።
ከሀገሪቱ ብሔራዊ ፓርኮች አንዱ የሆነው የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ በክልሉ ከሚገኙ ፓርኮች አንዱ ነው። በፓርኩ አጥቢ የዱር እንስሳትና ልዩ ልዩ አእዋፋት ይገኛሉ፤ ፓርኩም፣ ሸለቆውም፣ እነዚህ አእዋፋቱም የዱር እንስሳትም ለቱሪስት መስህብ መሆን የሚችሉ ናቸው።
ይህ ፓርክ የሚገኘውም በጉራጌ ዞን ነው። በአካባቢው ሳሮ ቢራ የሚባል መስህብ እንደሚገኝም ነው የተገለጸው። ይህ ቦታ ቢለማ ለቱሪስቶች ተመራጭ ከመሆኑ ባሻገር ለሀገሪቱም ትልቅ የቱሪዝም መስህብ ሊሆን ይችላል።
ክልሉ በሰው ሠራሽ የቱሪዝም ሀብቶቹም ይታወቃል። እ.አ.አ በ1980 በዩኔስኮ የተመዘገበውና በጉራጌ ዞን የሚገኘው የጢያ ትክል ድንጋይ በቱሪስቶች በእጅጉ የሚታወቅ ቅርስ ነው። በምስራቅ ጉራጌ ዞን ከሚገኘው ትክል ድንጋይ በተጨማሪ በዩኔስኮ ያልተመዘገቡ ትክል ድንጋዮች በስልጤ ዞን፣ በየም ዞንና በሌሎችም እንዳሉ ይነገራል።
በከምባታ ዞን የሚገኘው የአምበሪቾ ተራራ የኮሙኒቲ ቱሪዝም መስህብ ሌላው የክልሉ መስህብ ነው። የአምበሪቾ ተራራ አናት ላይ መቶ ሺህ ሰው ማስተናገድ የሚችል ሰፊ ሜዳ ይገኛል። ሜዳው አውሮፕላን ማሳረፍ እንደሚችልም ይገለጻል፡፡
ይህ መስህብ በዞኑ አስተዳደርና ተወላጆች ተገንብቶ የቱሪስት መዳረሻ መሆን ችሏል። በዚህ የቱሪስት መስህብ ተራራ አናት ላይ ለመድረስ የሚያስችሉ 777 ደረጃዎች ተሰርተዋል፤ ተራራው ከባህር ወለል በላይ ያለው ከፍታም ወደ 3 ሺህ 80 ሜትር ነው። በጣም ያምራል፤ ጉም ይመላለስባታል፡፡ “ገና ተራራው ግርጌ ላይ ስትደርስ በእድሜህ ላይ አምስት ዓመት፤ ስታጋምስ ሌላ አምስት ዓመት፣ ደረጃውን ስትጨርስ ሌላ አምስት ዓመት ትጨምራለህ” ይባልለታል፡፡
777 የሚለው ትርጉም እንዳለውም መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ሰባት ቁጥር በብሔረሰቡ ብዙ ትርጉም አለው፤ ከሶስቱ አንዱ ሰባት ወንዞችን ያመለክታል፤ ሌላው ሰባት በአካባቢው ያሉ ሰባት ተራራዎችን፣ እንዲሁም ሌላው ሰባት ጥንት የከምባታ ማህበረሰብ ሰባት ጎሳ ሆኖ ወደ አካባቢው በመምጣት እዚህ ተራራ ሥር መኖር እንደጀመረ ያመለክታል በመባልም ይገለጻል።
ሐይቆች ሌሎች በክልሉ የሚገኙ የቱሪስት መስህቦች ናቸው። በርካታ ትንንሽ ሐይቆች በክልሉ የሚገኙ ሲሆን፣ በሀዲያ ጭፍራ መሀሉ ደሴት ያለበት በርካታ ወፎች የሚታዩበት ሐይቅ አለ፡፡ በዚሁ ዞን ጉማሬ በስፋት የሚታይበት ቡዳ ማዶ በሚባል አካባቢ ጉዮ የሚባሉ ሐይቆች አሉ፡፡ ሌላው በሀዲያ ለጋብቻ ቃል ኪዳን ሲታሰርና እርቅ ሲፈጸም በጋራ ወተትና የመሳሰሉት የሚጎነጩበት ሁለት አፍ ያለው ቁስ /ገንቦ/ አለ።
በሀዲያ ብሔረሰብ ዘንድ በዚህ ሥነ ሥርዓት የተጋቡ ጥንዶች ተፋትተው አያውቁም ተብሎ ይነገራል። በነፍስ የሚፈላለጉ ጠበኞች ከእርቅ በኋላ በዚህ ቁስ ከጠጡ ሁሉም ነገር እንደ ቀድሞው መሆን አለበት ተብሎ ይታሰባል።
በስልጤ ዞን ላይ ቀለሙን የሚቀያይር ‹‹ሀረ ሼጣን›› የሚባል ሐይቅ አለ። በተመሳሳይ ትንሹ አባያ የሚባል ሀይቅም በስልጤ ዞን የሚገኘው የመስህብ ስፍራ ነው፡፡ በሀላባ የአልቶ ፍልውሃ፣ ሌሎችም ለቱሪስት መስህብነት ሊውሉ የሚችሉ በርካታ ፍል ውሃዎች በክልሉ ይገኛሉ። በክልሉ ሁሉም ዞኖች ዋሻዎችም ይገኛሉ፡፡ ከምባታ ዞን ላይ አንድ ሺህ ሰዎችን መያዝ የሚችል “ሶኪቾ” የሚባል ዋሻ እንዳለም የመረጃ ምንጫችን ያመለክታል።
በክልሉ በዓመት አንዴ ለባህላዊ መድኃኒት የሚውሉ እጽዋት ለቀማ የሚካሄደበት አካባቢ አለ፡፡ ይህ በየም ብሔረሰብ ዘንድ የሚካሄደው ዓመታዊ ባህላዊ ሥነ ሥርዓት የቱሪዝም መስህብ ሊሆን የሚችል ነው።
በየም ብሔረሰብ በየዓመቱ ጥቅምት 17 የሚፈጸመው ይህ ሥነ ሥርዓት ከኢትዮጵያ ውጭ በየትኛውም የዓለም ክፍል አይፈጸምም። ማኅበረሰቡ መድኃኒቱን ለእንስሳትም ለሰውም ህመም መፈወሻነት ይገለገልበታል፤ በዓመት አንዴ የሚሰበሰበውን ይህ ባህላዊ መድኃኒት ማህበረሰቡ ዓመቱን ሙሉ ይጠቀምበታል። ክልሉ ባለፈው ጥቅምት ወር በሳይንስ ሙዚየም በተካሄደው የቱሪዝም ሆስፒታሊቲ አውደ ርዕይ የቱሪስት መዳራሻዎቹንና መስህቦቹን አስጎብኝቷል።
More Stories
ህብረተሰቡ የቁጥጥሩ ባለቤት ካልሆነ ችግሩን ለመቅረፍ ያስቸግራል – አቶ ቡሪሶ ቡላሾ
የኢትዮጵያ ሚና በአፍሪካ
አንድ ነገር ቢጎድልህም ሌላ ነገር ተሰጥቶሀል – ወጣት ቢኒያም በሪሶ