ስፖርት ለሀገራዊ አንድነት፣ ለሰላም ግንባታና ለወንድማማችነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለዉ ተገለፀ
ሀዋሳ፡ የካቲት 10/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ስፖርት ለሀገራዊ አንድነት፣ ለሰላም ግንባታና ለወንድማማችነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለዉ የአሪ ዞን አስተዳደር ገለጸ
ሁለተኛዉ መላዉ የአሪ ዞን ልዩ ልዩ ስፖርታዊ ሻምፒዮናና የባህል ስፖርቶች ውድድር ተጠናቋል ፡፡
በውድድሩ ማጠቃለያ ላይ የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም አታ ባስተላለፉት መልዕክት ስፖርት ለሀገራዊ አንድነት ለሰላም ግንባታና ለወንድማማችነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ተናግረው ወጣቱ በስፖርት የዳበረና በስነምግባር የታነጸ እንዲሆን ላመድረግ ስፖርታዊ ዉድድሩ እንደሚያግዝ ገልፀው አስተዋጽኦ ያበረከቱ አካላትን አመስግነዋል፡፡
የአሪ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምርያ ኃላፊ አቶ ይሄነዉ ተስፋዬ በበኩላቸዉ፥ ለአንድ ሣምንት በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ሲካሄድ የቆየዉ ስፖርታዊ ውድድር ፍፃሜዉን ማግኘቱን ገልፀው በውድድሩ ዞኑን የሚወክሉ ተተኪ ስፖርተኞች መመልመላቸዉንም አስረድተዋል፡፡
የሰሜን አሪ ወረዳ ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት የወጣቶችና ስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ በየነ በለጠ ዉድድሩ ከአምናዉ የተሻለና ልምድ የተወሰደበት አስደሳች ውድድር እንደነበ ተናግረዋል፡፡
የሰሜን አሪ ወረዳ በባህላዊ ስፖርት የተወዳደሩት አቶ ማቲዎስ ኤራ ኩርቦ የተሰኘው ባህላዊ ዉድድሩ አሪ ማህበረሰብ ባህላዊ መገለጫ ከመሆኑም በላይ አዝናኝ ስፖርት ነዉ ብለዋል፡፡
የደቡብ አሪ ወረዳ የወንዶች እግር ኳስ ቡድን አንበል ዮናስ ሺቺ እና ግብ ጠባቂው እያሱ አድማሱ በጋራ እንደገለፁት ጠንክረዉ በመስራታቸዉ የወርቅ ሜዳልያ ተሸላሚ ከመሆናቸዉም በላይ ዞኑን ወክለዉ ክልል ላይ የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንደሚተጉ ገልፀዋል ፡፡
በሴቶች እና በወንዶች ቦክስና ቴኳንዶ ተወዳድረዉ የወርቅ ሜዳልያ ሽልማት ያገኙት ወጣት ባንቻየሁ ዳዊት እና አሰማኃኝ ዘለቀ በጋራ እንደተናገሩት በዉድድሩ ሠላም አንድነትንና ወንድማማችነትን እንዳዳበሩ ገልፀዉ ለስፖርቱ ዘርፍ ትኩረት ሊሰጠዉ ይገባል ብለዋል ፡፡
በወንዶች እግር ኳስ ደቡብ አሪ ወረዳ ሲያሸንፍ በሴቶች ደግሞ የባካዳዉላ አሪ ወረዳ አሸንፈው የተዘጋጀላቸውን ዋንጫ ተቀብለዋል፡፡
More Stories
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በህግና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበለትን ደንብ መርምሮ አጸደቀ
ሀዋሳ ከተማ ሙሉጌታ ምህረትን የክለቡ አሰልጣኝ አድርጎ ሾመ
የአካባቢን ሰላም ለማስጠበቅ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ትልቅ ሐላፊነት መዉሰድ እንዳለባቸዉ ተጠቆመ