በ6 ወራት ውስጥ ሊመዘበር የነበረ ከ156 ሚሊየን 560ሺህ ብር በላይ ማዳን መቻሉ ተገለጸ

በ6 ወራት ውስጥ ሊመዘበር የነበረ ከ156 ሚሊየን 560ሺህ ብር በላይ ማዳን መቻሉ ተገለጸ

ሀዋሳ: ጥር 30/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባለፉት በ6 ወራት ውስጥ ሊመዘበር የነበረ ከ156 ሚሊየን 560ሺህ 356.55 ብር በላይ ማዳን መቻሉን የክልሉ ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ለክልሉ ምክር ቤት የህግና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርት አመላከተ።

ሙስናና ብልሹ አሰራር የሀገርም ሆነ የክልሉ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እድገት ጠንቅ መሆኑን የገለፁት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ ተካልኝ ጋሎ፥ የልማት፣ የዲሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ግንባታ ጥረታችንን የሚያደናቅፍ ተግባር በመሆኑ የክልሉ መንግስት የጸረ-ሙስና ትግሉን ይበልጥ በማጠናከር እየሰራ ነው ብለዋል።

ለሙስና የሚያጋልጡ ሁኔታዎችን በጥናት በመለየት ቀድሞ መከላከልና የተሿሚዎችና የመንግስት ሰራተኞችን ሀብት ምዝገባ በማካሄድ የግልፅኝነትና ተጠያቂነት አሠራርን ማረጋገጥ መሆኑን በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን ለሙስና ተጋላጭ የሆኑ ዘርፎችና አካባቢዎች ማለትም የግብር አሰባሰብ፣ የመንግስት ግዥ እና በጀት አስተዳደር፣ የመሬት አስተዳደርና አቅርቦት፣ የኢንቨስትመንት መሬት አሰጣጥ፣ የኮንስትራክሽን ዘርፍ በኢንዱስትሪ ዘርፍ በተለይም በሥራ እድል ፈጠራ፣ ፕሮግራሞች፣ በመሳሰሉት ላይ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡

የክልሉ ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ተካልኝ ጋሎ፥ ለክልሉ ምክር ቤት የህግና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡት የ6 ወራት እቅድ አፈፃፀም፥ በአስቸኳይ ሙስና መከላከል 104 ሚሊየን 934ሺህ 520.93 ብር ማዳን መቻሉን ተናግረዋል።

ተመዝብሮ የነበረ የመንግሥትን ሀብት ለማስመል በተደረገ ጥረት (በሠነድ የተረጋገጠ) 51 ሚሊየን 625ሺህ 835.62 ብርተመላሽ መሆኑን አመላክተው፥ በዓይነት 45ሺ 108 ካሬ የከተማ መሬት 630 ካሬ ሜትር የከተማ የገበያ ንግድ ቦታዎች 10ሺህ 000 ካ.ሜትር የገጠርእርሻ መሬት ፤ 215 ያልተወራረሱ የገቢ እስሊፖች 6 ጥራዝ ደረሰኝ፤ 1 ታብሌት ፤960 ሊትር ናፍጣ በአጠቃላይ በ2018 ግማሽ አመት በሙስና መከላከል የዳነና የተመለሰ ሀብት በድምሩ በገንዘብ 156ሚሊየን 560ሺህ 356.55 ብር ማዳኑን ለቋሚ ኮሚቴው አስረድተዋል።

ከዚህ በተጓዳኝ በአስቸኳይ ሙስና መከላከል ስራ በጎፋ ዞን በከንቾ ቀበሌ በተፈትሮ አደጋ /መሬት ናዳ / ለተፈናቀሉ ወገኖች ከተሰበሰበዉ ሀብት 60 ሚሊዮን ብር ቼክ በማጭበርበር ጉዳይ የህግ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ኮሚሽነሩ አመላክተዋል።

በአርባምንጭ አካል ጉዳተኞች ተሀድሶ ማዕከል ከግንባታ ጨረታ እና ክንዉን ጋር ተያያዞ ከ10 ሚሊየን ብር በላይ የተመዘበረ እና ብልሹ አሠራር እየተፈፀመበት ያለ ስለመሆኑ ለኮሚሽኑ ጥቆማ ቀርቦ እገዳ በመስጠት ተጨማሪ መረጃ የማሰባሰብ ሂደት በመከናወን ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴ አባላት በበኩላቸው በክልሉ በሙስናና ተያያዥ ጉዳዮች የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከል የተጀመረው ተስፋ ሰጪ ተግባራት ተጠናክሮ ሊቀጥሉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት የህግና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዱንጋ ናኩዋ በበኩላቸው ሙስናን የሚፀየፍ ትልውድ ለመፍጠር ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበው፥ ሀብት የማያስመዘግቡ አካላት ጋር ተያይዞ ያለውን ውስንነት በመፍታት በስፋት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

ዘጋቢ: ዘላለም ተስፋዬ