የባህል ስፖርቶች ለክልሉ ህዝቦች ሠላምና አንድነት ያለው ጠቄሜታ የጎላ በመሆኑ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

የባህል ስፖርቶች ለክልሉ ህዝቦች ሠላምና አንድነት ያለው ጠቄሜታ የጎላ በመሆኑ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

”የባህል ስፖርቶቻችን ለአንድነታችንና ለሠላማችን” በሚል መሪ ቃል 4ኛው ክልል አቀፍ የባህል ስፖርቶችና የባህል ፌስቲቫል እንዲሁም አትሌቲክስ ውድድር በኮንታ ዞን አመያ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በባህል ልብሳቸው ያሸበረቁት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት የባህል ስፖርቶችና የባህል ፌስቲቫል ልዑካን ቡድን የተለያዩ ትርኢቶችን በማቅረብ ውድድሩ ተጀምሯል።

የአመያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ተመስገን ደጀኔ፤ የባህል ስፖርትና የባህል ፌስትቫል ከስፖርት ውድድርነት ባለፈ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እና ትስስር በመፍጠር የማህበረሠቡ ቱባ ባህላዊ እሴቶች እንዲጎለብቱና እንዲታወቁ ከፍተኛ ድርሻ ያለው በመሆኑ በአመያ ከተማ የተሻለ የቆይታ ጊዜ እንዲኖራቸው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኮንታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታከለ ተስፉ፤ የየብሄረሰቡ የማንነት መገለጫዎች የሚተዋወቁበትና ልምድና ዕውቀት የሚለዋወጡበት የአንድነት ማፅኛ መድረክ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በመድረኩ የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ብላቴ፤ የባህል ስፖርቶች ሳይበረዙና ሳይጠፉ ከትውልድ ወደ ትውልድ በማስተላለፍ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸውን ለትውልድ ማስተላለፍ ነው ብለዋል።

በመክፈቻ ሥነስርዓቱ የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡ አብዮት እሸቱ – ከዋካ ጣቢያችን