የጎፋ ዞን ልዩ ልዩ ስፖርቶች ሻምፒዮናና ባህላዊ ስፖርት ፌስቲቫል ውድድር መካሔድ ጀመረ

የጎፋ ዞን ልዩ ልዩ ስፖርቶች ሻምፒዮናና ባህላዊ ስፖርት ፌስቲቫል ውድድር መካሔድ ጀመረ

ሀዋሳ: የካቲት 05/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የጎፋ ዞን የ2017 ልዩ ልዩ ስፖርቶች ሻምፒዮና እና ባህላዊ ስፖርት ፌስቲቫል ውድድር በዛላ ወረዳ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች መካሔድ ጀምሯል።

ከዞኑ 11 መዋቅሮች የተውጣጡ የስፖርት ቡድኖች በ12 አይነት የውድድር ዘርፎች ይሳተፋሉ።

በጎፋ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ አዘጋጅነት እና በዛላ ወረዳ አስተናጋጅነት የሚካሄደው የዘንድሮ 3ኛው ልዩ ልዩ ስፖርት ሻምፒዮና እና 5ኛው የባህል ስፖርቶች ፌስቲባል የመክፈቻ ስነ-ስርዓት በጋልማ ከተማ ተካሂዷል።

በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የጎፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና ከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ ወሰኔ ዞናዊ ልዩ ልዩ የስፖርት ሻምፒዮናና የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል ውድድር ጠንካራና ተወዳዳሪ ስፖርተኞችን ለማፍራትና የህዝቡን የእርስበርሰ ግንኙነትና አንድነት ለማጠናከር አይነተኛ ሚና የሚያበረክት መሆኑን አስገንዝበዋል።

የዛላ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ያዕቆብ ዘካሪያስ ባስተላለፉት መልዕክት ስፖርታዊ ውድድሩ ያለምንም የፀጥታ ችግር በሠላም እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ የስፖርት ዘርፍ ኋላፊ አቶ ጠንክር ግዛቸው 11 መዋቅሮች የተውጣጡ የስፖርት ቡድኖች በ12 አይነት የውድድር ዘርፎች የሚሳተፉ መሆናቸው ጠቁመዋል።

በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ላይ በአዘጋጇ ዛላ ወረዳ እና መሎ ኮዛ ወረዳ የወንዶች እግር ኳስ ቡድን መካከል በተደረገ ጫወታ 1 ለ 0 በሆነ ውጤት መለያየት ችለዋል።

ዘጋቢ:- አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን