በጉደሰን ፓርክ ስታዲየም የመጨረሻው የመርሲሳይድ ደርቢ ዛሬ ምሽት ይካሄዳል

በጉደሰን ፓርክ ስታዲየም የመጨረሻው የመርሲሳይድ ደርቢ ዛሬ ምሽት ይካሄዳል

በእንግሊዝ ከሚገኙ የደርቢ ጨዋታዎች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው የመርሲሳይድ ደርቢ በጉዲሰን ፓርክ ስታዲየም ለመጨረሻ ጊዜ ዛሬ ምሽት 5 ሰዓት ላይ ይካሄዳል።

ኤቨርተን ላለፉት 130 ዓመታት ባለሜዳ ሲሆን ሲጫወትበት የቆየውን የጉዲሰን ፓርክ ስታዲየምን ትቶ ከሚቀጥለው የውድድር ዓመት አንስቶ ሌላ አዲስ ስታዲየም መጠቀም የሚጀምር በመሆኑ ነው የመርሲሳይድ ደርቢ ለመጨረሻ ጊዜ በዚሁ ስታዲየም ምሽት ላይ የሚካሄደው።

ከ2025/26 ጀምሮ ኤቨርተን መጠቀም የሚጀምረው አዲሱ ስታዲየም መጠሪያ ስሙ ብራምሌይ ሞር ዶክ የሚሰኝ ሲሆን 52 ሺህ 888 ተመልካች የመያዝ አቅም እንዳለው ተነግሯል።

አስቀደሞ የአንፊልድ ስታዲየምን ይጠቀም የነበረው ኤቨርተን የሊቨርፑል እግርኳስ ክለብ መመስረቱን ተከትሎ እንደ አውሮፓዊያኑ ከ1894 አንስቶ በጉዲሰን ፓርክ ስታዲየም መገልገል መጀመሩን የታሪክ ድርሳናት ያመላክታሉ።

ኤቨርተን በዚሁ ስታዲየም የመጀመሪያ ጨዋታውን ከቦልተን ዎንደረርስ ጋር ሲጫወት 4ለ2 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

በጉዲሰን ፓርክ የመጀመሪያው የመርሲሳይድ ደርቢ እንደ አውሮፓውያኑ ጥቅምት 13 ቀን 1894 የተገናኙ ሲሆን ጨዋታውም በኤቨርተን 3ለ0 አሸናፊነት ነው የተጠናቀቀው።

ዛሬ ምሽት በዚህ ዕድሜ ጠገብ ስታዲየም በሁሉም ውድድሮች ለ120ኛ ጊዜ በአጠቃላይ ደግሞ ለ245ኛ ጊዜ የሚገናኙ ይሆናል።ከዚህ ቀደም በጉዲሰን ፓርክ በተከናወኑ ጨዋታዎች እያንዳንዳቸው 41 ጊዜ ሲሸናነፉ 37 ጊዜ ደግሞ ሳይሸናነፉ ተለያይተዋል።

ኤቨርተን ላለመውረድ እንዲሁም ሊቨርፑል የፕሪሚዬርሊጉ የዋንጫ አሸናፊ ለመሆን ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ሆነው የሚያደርጉት የምሽቱ ጨዋታ በጉደሰን ፓርክ ስታዲየም ማን የበላይ ሆኖ ያጠናቅቃል የሚለውን ለመለየትም የሚደረግ ትልቅ ፊልሚያ ይሆናል ተብሎ ተጠብቋል።

በሙሉቀን ባሳ