ሀዋሳ ከተማ፣ሲዳማ ቡና እና ሃድያ ሆሳዕና ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፉ የመጀመሪያዎቹ ክለቦች ሆኑ

ሀዋሳ ከተማ፣ሲዳማ ቡና እና ሃድያ ሆሳዕና ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፉ የመጀመሪያዎቹ ክለቦች ሆኑ

በኢትዮጵያ ዋንጫ ሶስተኛ ዙር ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ፣ሲዳማ ቡና እና ሀድያ ሆሳዕና ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ ወደሚቀጥለው ዙር ያለፉ የመጀመሪያዎቹ ክለቦች ሆነዋል።

ወደ ሩብ ፍፃሜ ለማለፍ የሚከናወኑ መርሐግብሮች በዛሬው ዕለት መከናወን ሲጀምር ነው ሦስቱ ክለቦች ማለፋቸውን ያረጋገጡት።

ቀን 9 ሰዓት ከ30 ላይ በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ስታዲየም ከነገሌ አሪሲ ጋር የተጫወተው ሀዋሳ ከተማ 2ለ0 በማሸነፍ ቀጣዩን ዙር ተቀላቅሏል።

ከቀናት በፊት የቀድሞ ተጫዋቹን እና አሰልጣኙ ሙሉጌታ ምህረትን ለሾመው ሀዋሳ ከተማ የማሸነፊያ ግቦችን ተባረክ ሄፋሞ እና ብሩክ ታደሰ ከመረብ አሳርፈዋል።

በተመሳሳይ ሰዓት በሰበታ ስታዲየም ከስሑል ሽረ ጋር የተጫወተው ሲዳማ ቡና 1ለ0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍፃሜው አልፏል።

ለሲዳማ ቡና ወሳኟን የማሸነፊያ ግብ ሀብታሙ ታደሰ ከመረብ ጋር አገናኝቷል።

ቀደም ብሎ በዚሁ ስታዲየም በተካሄደ ጨዋታ ሀድያ ሆሳዕና ሀረር ከተማን በተመሳሳይ 1ለ0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉን አረጋግጧል።

ተመስገን ብርሃኑ መደበኛው 90 ደቂቃ ተጠናቆ በጭማሪው ሰዓት የሀድያን የማሸነፊያ ግብ አስቆጥሯል።

ወደ ሩብ ፍፃሜ ለማለፍ የሚደረጉት የ3ኛው ዙር የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታዎች ነገ እና ከነገ በስቲያ መከናወናቸውን የሚቀጥሉ ይሆናል።

በሙሉቀን ባሳ