በማድሪድ ደርቢ ሪያል ማድሪድ ከአትሌቲኮ ማድሪድ ዛሬ ምሽት ይፋለማሉ

በማድሪድ ደርቢ ሪያል ማድሪድ ከአትሌቲኮ ማድሪድ ዛሬ ምሽት ይፋለማሉ

በ23ኛ ሳምንት የስፔን ላሊጋ በማድሪድ ደርቢ ሪያል ማድሪድ ከአትሌቲኮ ማድሪድ ዛሬ ምሽት 5 ሰዓት ላይ የሚያደርጉት ፊልሚያ ይጠበቃል።

ሁለቱ ክለቦች በአንድ ነጥብ ልዩነት ብቻ 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

በአሰልጣኝ ካርሎ አንቼሎቲ የሚመራው ሪያል ማድሪድ በ49 ነጥብ ቀዳሚውን ደረጃ ሲይዝ የከተማ ባላንጣው በበኩሉ በ48 ነጥብ ተከታዩን ደረጃ ይዟል።

ሪያል ማድሪድ በሜዳው በአትሌቲኮ ማድሪድ ላለፉት 9 ዓመታት አልተሸነፈም።

የአሰልጣኝ ዲያጎ ሲሜዮኔው ቡድን በያዝነው የውድድር ዓመት በላሊጋው ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ያለው ክለብ ሆኖ ይገኛል። ሎስ ኮልቾኔሮሶቹ 14 ጎሎችን ብቻ ተቆጥሮባቸው ጥቂት ግቦችን በማስተናገድ በቀዳሚነት ተቀምጠዋል።

ሎስብላንኮዎቹ በአንፃሩ ዘንድሮ ከትልልቅ ክለቦች ጋር ያላቸው ግንኙነት አመርቂ አይደለም።

በያዝነው የውድድር ዓመት በኦፕታ ፓውር ራንኪንግ ከ30ኛ ደረጃ በላይ ካሉ ክለቦች ጋር በሁሉም ውድድሮች 9 ጊዜ ተገናኝተው 2ቱን ብቻ ማሸነፍ ሲችሉ በ7ቱ ተሸንፈዋል።

እነዚህን ሽንፈቶች ያስተናገዱት በባርሴሎና ሁለት ጊዜ፣በሊል፣በኤሲ ሚላን፣ሊቨርፑል እና አትሌቲክ ቢልባኦ ነው።

የዛሬው ምሽት ተጋጣሚ የሆነው አትሌቲኮ ማድሪድም በታላላቅ ክለቦች ተርታ የሚገኝ በመሆኑ ለሪያል ማድሪድ ጨዋታው ከባድ ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም።

በአትሌቲኮ ማድሪድ በኩል አርጄንቲናዊው የፊት መስመር ተጫዋች ጁሊያን አልቫሬዝ ተጠባቂው ተጫዋች ነው።

የቀድሞ የማንቸስተር ሲቲው ተጫዋች በአዲሱ ክለብ የመጀመሪያ ዓመት ቆይታው አትሌቲኮ ማድሪድ በሁሉም ውድድሮች ባከናወናቸው 35ቱም ጨዋታዎች ላይ መሰለፍ ችሏል።

በነዚህ ጨዋታዎችም 16 ጎሎችን ሲያስቆጥር 4 ግብ የሆኑ የመጨረሻ ኳሶችን አቀብሏል።

በሪያል ማድሪድም በኩልም  አዲሱ ፈራሚ ክሊያን ምባፔ በምሽቱ ጨዋታ ትኩረት ሳቢው ተጫዋች ነው።

በመጀመሪያው ዙር የማድሪድ ደርቢ ጨዋታ በጉዳት ምክንያት ያልተሰለፈው ምባፔ በላሊጋው 16 ጎሎች በማስቆጠር እና 2 የመጨረሻ ኳሶችን በማቀበል በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ ይገኛል።

በምሽቱ ተጠባቂ ጨዋታ በሪያል ማድሪድ በኩል ጉዳት ላይ የነበሩት ኤድዋርዶ ካማቪንጋ፣ጁድ ቤሊንግሃም እና ምባፔ ለጨዋታው ዝግጁ መሆናቸው ሲገለፅ አንቶኒ ሩዲገር፣ዳኒ ካርቭሀል እና ኤደር ሚሊታኦ ግን በጉዳት የማይሰለፉ ተጫዋቾች ናቸው።

በአትሌቲኮ ማድሪድ በኩል ደግሞ ተከላካዩ ሮቢን ሌ ኖርማንድ በቅጣት እንዲሁም ሪኬልሜ እና ቶማስ ሌማር በጉዳት ምክንያት በጨዋታው እንደማይሳተፉ ተገልጿል።

በሙሉቀን ባሳ