ስፖርታዊ ውድድሮች ተተኪ ስፖርተኞችን ከማፍራት ባሻገር ማህበራዊ መስተጋብር በማጠናከር በአካልና በአዕምሮ የዳበረ ማህበረሰብ ለመፍጠር ከፍተኛ አበርክቶ ያላቸው መሆኑ ተገለፀ

የሀድያ ዞን የ2017 ዓ.ም የልዩ ልዩ ስፖርቶች ሻምፒዮና እና የባህል ስፖርት ወድድር በዞኑ ሆሳዕና ከተማ ተጀምሯል።

በዕለቱ የተገኙት የሀድያ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መመሪያ ኃላፊ አቶ ታምሬ ኤርሚያስ እንደገለጹት፤ ስፖርታዊ ውድድሮች ተተኪ ስፖርተኞችን ከማፍራት ባሻገር ማህበራዊ መስተጋብር በማጠናከር በአካልና በአዕምሮ የዳበረ ማህበረሰብ ለመፍጠር ከፍተኛ አበርክቶ አላቸው።

ስፖርት ከፍተኛ ንቅናቄ ይጠይቃል ያሉት የመምሪያው ኃላፊ፤ የስፖርት ቤተሰብ አርቆ በማሰብና በውድድር ስፍራዎች ጥላቻን በማስወገድ በአንድነት መንፈስ ለስፖርቱ ዕድገት ተቀራርቦ መስራት እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።

የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዳዊት ጡምደዶ በበኩላቸው፤ መሰል ስፖርታዊ ውድድሮች በማህበረሰብ መካከል ወንድማማችነትን በመፍጠር እና በማቀራረብ ለሰላም ዕሴት የላቀ ሚና እንዳላቸው ገልፀው ለውድድሩ መሳካት አስተዳደሩ የበኩሉን ይወጣል ብለዋል።

የሀድያ ዞን ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ምክትል ኃላፊና የስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ንጉሴ ወርቁ እንዳሉት፤ በዓመት ሁለት ጊዜ በሚካሄደው በዚህ ውድድር በዘንድሮው 11 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚሳተፉ ሲሆን እነዚህም በዘመናዊ እና በባህላዊ የስፖርት ዓይነቶች እንደሚሳተፉ አስረድተዋል።

ከውድድሩ ዞኑንና ሀገሪቱን የሚወክሉ ተተኪ ስፖርተኞች አቅማቸውን አሟጠው እንደሚጠቀሙ ተስፋ የሚጣልበት መሆኑን ገልፀው የስፖርቱ ቤተሰብ ጨዋነት በተሞላበት መልኩ የተለመደውን ድጋፍ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

በሆሳዕና አቢዮ ኤርሳሞ መታሰቢያ ስታዲየም የተጀመረው ዞናዊ ልዩ ልዩ እና ባህላዊ ስፖርታዊ ውድድር ከጥር 25/2017 እስከ የካቲት 02/2017 ዓ.ም ለስምንት ቀናት እንደሚቆይ ከውድድር ኮሚቴ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ዘጋቢ: ሄኖስ ካሳ – ከሆሳዕና ጣቢያችን