በክልሉ ግምታዊ ዋጋቸው ከ450 ሺ በላይ የሆኑ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው የምግብና መጠጥ ምርቶችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ
ማህበረሰቡ በማንኛውም ወቅት ግብይት ሲፈጽም የምርቶችን የመጠቀሚያ ጊዜ በተገቢው ማየት እንዳለበት የክልሉ ጤና ቢሮ አሳስቧል።
ህብረተሰቡ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውና ባዕድ ነገሮች የተቀየጡባቸው ምግቦችን ሲመለከት በ8284 በነጻ መስመር በመደወል ጥቆማ መስጠት እንዳለበት ጥሪ ቀርቧል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ከኢትዮጵያ የምግብና መድሀኒት ባለስልጣን ጂማ ቅርንጫፍ ጋር በመቀናጀት በቤንች ሸኮ እና ሸካ ዞን በምግብና መጠጥ አከፋፋዮችና የችርቻሮ ሱቆች የክትትልና የቁጥጥር ስራ መስራቱን ገልጿል።
በክልሉ ጤና ቢሮ የጤናና ጤና ነክ ጉዳዮች ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አብዱልአዚዝ ፈረጃ እንደተናገሩት፤ እንደ ክልል በቤንች ሸኮ ዞን ሚዛን አማንና በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ ላይ በምግብና መጠጦች ላይ የቁጥጥር ስራ ተሰርቷል።
ተግባሩ ከምግብና መድሀኒት ባለስልጣን ጂማ ቅርንጫፍ፣ ከዞን ጤና መምሪያዎችና ከንግድ ዘርፍ ባለሙያዎች ጋር በጋራ መሰራቱን ገልጸዋል።
በቁጥጥር ስራው ግምታዊ ዋጋቸው ከ450 ሺ በላይ የሆኑ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው የታሸጉ ጁሶች፣ ጨው፣ የንግድ ምልክት የሌላቸው የአልኮል መጠጦች እና በተለይም አፍላ ቶክሲን ሊያስከትሉ የሚችሉ የሻገቱ በርበሬዎች በስፋት መገኘታቸውን ገልጸዋል።
እነዚህ ግብዓቶች በህብረተሰቡ ጤና ሊያስከትሉ የሚችሉት ጉዳት ከባድ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አብዱልአዚዝ፤ የክልሉ ጤና ቢሮም ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተለይም እንደ ማር፣ ቅቤና በመሳሰሉ ምግቦች ላይ ባዕድ ነገሮችን ቀይጠው የሚያቀርቡ አካላት ላይ ከአስተዳደራዊ እርምጃ ባሻገር በህግ የማስጠየቅ ስራም እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ባለስልጣን ጂማ ቅርንጫፍ የምግብ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ዮናስ ሞላ እንደተናገሩት፤ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤታቸው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ጋምቤላና ቤንሻንጉል ክልሎች ላይ የድጋፍ፣ ክትትልና የቁጥጥር ስራ እንደሚሰራም ገልጸዋል።
በቤንች ሸኮ ሚዛን አማንና በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ ከ168 ተቋማት በላይ የቁጥጥር ስራ መሰራቱን አቶ ዮናስ ጠቁመዋል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቤንች ሸኮና ሸካ ዞን በተደረገ ፍተሻ ግምታዊ ዋጋቸው ከ450ሺ ብር በላይ የሆኑ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈ፣ በአቀማመጥ ምክንያት የተበላሹ ምግብና መጠጦች ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
ከቅርብ አመታት ወዲህ ህብረተሰቡ የመጠቀሚያ ጊዜያቸውን በማየት የመግዛት ባህሉ እያደገ መምጣቱን የገለፁት አቶ ዮናስ፤ በተለይም በክልል እንደ ማር፣ ቅቤና በርበሬ ከባዕድ ነገሮች ጋር የመቀየጥ ዕድላቸው ሰፊ በመሆኑ መዋቅሮች የቅርብ ድጋፍና ክትትል ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።
በቤንች ሸኮ ዞን ጤና መምሪያ የጤናና ጤና ነክ ግብዓት ቁጥጥር የቡድን መሪ አቶ ለገሰ ግርማዬ እንደተናገሩት፤ ከቅርንጫፍ መስሪያ ቤትና ከክልሉ ጤና ቢሮ የቁጥጥር ቡድን ጋር ባለፉት 3 ቀናት በሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር 118 ተቋማት ላይ የቁጥጥር ስራ ተሰርቷል።
በዚህም ግምታዊ ዋጋቸው ሩብ ሚሊየን የሚጠጋ የተበላሹ የፋብሪካ ውጤቶችና የአካባቢ ምግቦችን ከገበያ የማስወጣት ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።
ለስራው ስኬት የህብረተሰቡ ጥቆማና ትብብር ከፍተኛ ነበር ያሉት አቶ ለገሰ ይህ ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ፡ ጦያር ይማም – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት የግብርናና ገጠር ልማት ቋሚ ኮሚቴ የሚከታተላቸውን ተቋማት የ6 ወራት እቅድ አፈፃፀም ግምገማ ማካሄድ ጀመረ
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ከ12 ቢሊየን ብር በላይ በጀት 471 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ እየተሰራ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ
የ2017 ዓ.ም የተቀናጀ የተፋሠሰ ልማት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በየም ዞን ፎፋ ወረዳ በአዝጊ ዘምዳ ቀበሌ ተጀመረ