128 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የተለያዩ የህክምና መሣሪያዎች ለ53 የክልል ደም ባንኮች ድጋፍ ተደረገ
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በርክክቡ ወቅት እንዳሉት፤ የደምና ሕብረ ህዋስ አገልግሎቱ፤ በ2015 ዓ.ም ከአይን ባንክ ጋር ከተዋሃደ እንዲሁም በአዲሱ በጸደቀው የጤና አገልግሎት አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1362/2017 መሠረት የተልዕኮና የአደረጃጀት ለውጥ በማድረግ፣ የአገልግሎት አድማሱን ይበልጥ በማስፋቱ፣ ተቋሙን በደም፣ በህብረ ህዋስ እና በአካል የማስተላለፍ ህክምናዎች ለማዘመን ስራዎችን እየሠራን እንገኛለን።
የጤና ሚኒስቴር በሁሉም አቅጣጫ የኢትዮጵያ ደምና ሕብረህዋስ ባንክ አገልግሎትን እየደገፈ እንደሚገኝ እና የዛሬውም ድጋፍ የቀጣይ ድጋፍ አንዱ ማሣያ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ ድጋፉ 12 ዓይነት የህክምና መሣሪያዎችን ያካተተ እንደሆነና በገንዘብም 128 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት እንደሆነ ጠቁመዋል።
አንድም እናት በወሊድ ወቅት በደም እጥረት ህይወቷ እንዳያልፍ፤ በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች አስተማማኝ እና ቀጣይነት ያለው የደም አቅርቦትን ለማረጋገጥ የህብረተሰቡ የበጎ ፍቃድ የደም ልገሣ ተሣትፎ ወሣኝ እንደሆነ የገለፁት ሚኒስትሯ በግልም ይሁን በማህበር ተደራጀተው ለደም ልገሳው ዘወትር ከፊት ለሚሰለፉ የበጎ ፍቃድ ደም ለጋሾች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አሸናፊ ታዘበው በበኩላቸው፤ በደም አቅርቦት ሥርዓት ውስጥ የህክምና መሣሪያዎች ሚናቸው ወሣኝ ቢሆንም በሃገር ውስጥ የማይገኙ፣ በግዢ ሂደትም ውስብስብ የጥራት ጉዳይ የሚታይባቸውና ከፍተኛ ሃብት የፈሰሰባቸው በመሆናቸው፤ መሣሪያዎችን በአግባቡና በጥንቃቄ ተጠቅመን አጠቃላይ የደም ሥርዓታችንን ለማሻሻል ሁሉም በትኩረት ሊሠራ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
አሁን የተደረገው ድጋፍ የመጀመሪያ ዙር ሲሆን በቀጣይ ፍሪጆች እና ሌሎች የህክምና መሳሪያዎች ግዥ ሂደት ላይ በመሆናቸው ሀገር ውስጥ እንደደረሱ የሚሰራጩ መሆኑን ተናግረው፤ አገልግሎቱ አጠቃላይ የደምና ህብረ ህዋስ ስርአቱን ለማዘመን የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።
ድጋፎቹን የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ያስረከቡ ሲሆን ከክልሎች የመጡ የጤና ቢሮ ሀላፊዎች እና ምክትል ሀላፊዎችም በድጋፉ መደሰታቸውን እና ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
ምንጭ፡ የጤና ሚኒስቴር
More Stories
የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት ገለፀ
የጥንቃቄ መልዕክት-ዶክተር ደግነት አማዶ (የድንገተኛ እና ጽኑ ህሙማን ስፔሻሊስት )
የኤችአይቪ/ኤድስ ስርጭትን ለመከላከልና የተጣሉ ግቦችን ለማሳካት ትኩረት እንደሚያስፈልግ ተገለፀ