የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት ገለፀ
እስካሁን በተሰራው ተግባር ከ11 ሺህ በላይ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎችን ማፍራት መቻሉንም ጠቁሟል፡፡
የቀቤና ልዩ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አብድልኸይ ኑርሀሰን እንደገለፁት፤ በልዩ ወረዳው የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡
12 ሺህ 8 መቶ 88 አባዎራዎች አገልግሎቱን እንዲያገኙ ታቅዶ አስካሁን በተሰራው ስራ 11 ሺህ 51 አባላትን ማፍራት መቻሉን የተናገሩት አቶ አብድልኸይ፤ ይህም የዕቅዱ 80 በመቶ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ለዚህም በጤና ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና የመድሃኒት አቅርቦት ማሻሻል ወሳኝ ነው ያሉት አቶ አብድልኸይ፤ በበጀት አመቱ በሁለት ነጥብ አምስት ሚልየን ብር የመድሃኒት ግዢ ተፈፅሞ ለጤና ተቋማት መሰራጨቱን ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ አሁንም የመድኃኒት አቅርቦቱ ከማህበረሰቡና ከጤና ተቋማት ፍላጎት ጋር የተጣጣመ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡
በሃገር አቀፍ ደረጃ የታለመውን ሁለንተናዊ ለውጥ እውን ለማድረግ ከተፈለገ የጤና አገልግሎትን ለሁሉም በማዳረስ ጤናው የተጠበቀ አምራች ዜጋ መፍጠር እንደሚገባ የገለፁት ሃላፊው፤ በልዩ ወረዳው እየተገነባ የሚገኘው የማህበረሰብ አቀፍ የፋርማሲ ግንባታ 70 በመቶ መድረሱን ገልፀዋል፡፡
በተለይም አገልግሎቱ ሁሉም ማህበረሰብ በፍታሃዊነት የጤና አግልግሎት እንዲያገኝ ምቹ እድል የሚፈጥር ነው ያሉት አቶ አብድልኸይ፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ችግሮችን የማረም እንዲሁም በአጎራባች ወረዳዎችና ዞኖች ከሚገኙ የጤና ተቋማት ውል በመግባት አገልግሎቱን ይበልጥ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በጽ/ቤቱ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሀምዲሳ አህመድ፤ ማህበረሰቡ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆን በተሰራው ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል ብለዋል፡፡
በልዩ ወረዳው የአልቢር ሀሰን ኡንጃሞ ጤና ጣቢያ ሃላፊ የሆኑት አቶ ደገፈ ኢማሙ፤ በጤና ጣቢያው የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥር እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
አልፎ አልፎ የሚስተዋለውን የመድሃኒት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል ያሉት አቶ ደገፈ፤ ማህበረሰቡ ፍትሃዊና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኝ ለማስቻል እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በልዩ ወረዳው በጤና ተቋማት አግኝተን ያነጋገርናቸው የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ተጠቃሚዎች በሰጡት አስተያየት፤ በአመት አንድ ጊዜ በከፈሉት መዋጮ የህክምና አገለግሎት አመቱን ሙሉ እንዲያገኙ ያስቻላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በጤና ተቋማቱ የሚስተዋሉ የመድኃኒት አቅርቦት ችግሮችን ለመቅረፍ እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ገልፀዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ጅላሉ ፈድሉ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
128 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የተለያዩ የህክምና መሣሪያዎች ለ53 የክልል ደም ባንኮች ድጋፍ ተደረገ
የጥንቃቄ መልዕክት-ዶክተር ደግነት አማዶ (የድንገተኛ እና ጽኑ ህሙማን ስፔሻሊስት )
የኤችአይቪ/ኤድስ ስርጭትን ለመከላከልና የተጣሉ ግቦችን ለማሳካት ትኩረት እንደሚያስፈልግ ተገለፀ