ሀገር በያየህይራድ ብዕር

ሀገር በያየህይራድ ብዕር

በይበልጣል ጫኔ

ቁጥብ ነው። ሲበዛ ዝምተኛ። የሰራቸው ስራዎች እንጂ÷ እርሱ እምብዛም አይታወቅም። ከጀርባ ሆኖ ብዙዎችን ፊት ለፊት አቁሟል። በልቡ ውስጥ የሚንቀለቀል ስሜቱን በብዕሩ ጫፍ ከትቦ÷ ብዙዎች በስሜት እንዲደመጡ አድርጓል። እሱስ ቢሉ÷ እሱ ፊት ለፊት አይታይም። ስሙም ሆነ ግብሩ እንዲህ ወይም እንዲያ ተብሎ አይነገርለትም።

ሰሞኑን የእረፍቱ ዜና ሲሰማ ነው÷ ድንገት ስሙ አየሩን የሞላው። ያየህይራድ አላምረው÷ እንደ ስራው ያልተወራለት እንደ አበርክቶው ያልተነገረለት ጉምቱ ብዕረኛ።

ከቀዳሚዎቹ እና ዘመን ተሻጋሪ የጥበብ አሻራቸውን ማሳርፍ ከቻሉ የሙዚቃ ግጥም ፀሐፊዎች አንዱ ነው÷ ያየህይራድ አላምረው።

ይኼ ታላቅ የጥበብ ሰው ከ1970ዎቹ ጅማሬ አንስቶ የሙዚቃ ግጥም መፃፍ የጀመረ ቢሆንም÷ እያበበ፣ እያሸተ እና እየጎመራ የየዘመናቸውን መልክ መግለጥ የሚችሉ ድርሰቶችን እያበረከተ ከትውልድ ጋር ዘልቋል። ከነ ኩኩ ሰብስቤ፣ ፀሐዬ ዮሐንስ፣ ዳምጠው አየለ፣ ክቡር ዶክተር ጥላሁን ገሠሠ እስከ ወጣቱ ከያኒ ዳዊት ፅጌ ድረስ በሰላ ብዕሩ ዘመን አይሽሬ ሥራዎችን እየከተበ ተሻግሯል።

በተለይ ደግሞ ፍቅርን እና ናፍቆትን የሚገልጥበት መንገድ÷ ግዘፍ ነስቶ በሰዎች ልብ ውስጥ የሚመላለስ እንጂ እንዲሁ በዋዛ ተሰምቶ የሚረሳ አይደለም። ለዚህ ሃሳብ አስረጂ ይሆነን ዘንድ ሁለት ስራዎቹን ብቻ እንጠቅሳለን። ቀዳሚ የምናደርገው የአስቴር አወቀን “የሠርጌ ትዝታ” ነው።

“የሠርጌ ትዝታ” የተሰኘው የያየህይራድ ድርሰት÷ የተሰራበትን ዘመን ተሻግሮ ዛሬም ድረስ ይደመጣል። ሠርግ ሠርጎ ላገባ እና ተሞሽሮ ለተዳረ ሁሉ የወል ትዝታ ነውና÷ ምናልባት ወደፊትም የሚያረጅ ዓይነት አይደለም። እነሆ የሙዚቃው መንደርደሪያ ግጥም፦
“እኔ ያንተ ሙሽሪት አምሮብኝ ተውቤ
አማረብሽ ሲሉኝ መላው ቤተሰቤ
ዛሬም ባይንህ ባይኔ ይመጣል ትዝታው
እንዴት እንደነበር የሠርጌ ሁኔታው”

ሌላኛው ፍቅር እና ናፍቆት የተሰናኘበት የያየህይራድ ድርሰት÷ ፀሐዬ ዮሐንስ ነፍስ የዘራበት “ነፍሴ” የተሰኘ ሙዚቃ ነው። ብዙዎች አብሮነታቸውን ያጀቡበት÷ ከአንደበታቸው ቃል ሳያወጡ ልብ ለልብ የተግባቡበት ይህ ሙዚቃ÷ እንዲህ ውብ ሆኖ ለመሰራቱ የተጫወተው ሙዚቀኛ ሚና ከፍ ያለ መሆኑ ባይታበልም÷ የደራሲው ረቂቅ ስሜትን ስሜት መያዝ በሚችል መንገድ መግለጥ መቻሉ የታየበት ከፍ ያለ ሥራ ነው፦
ነፍሴ በምድር ያፀደቅሽኝ
“ልቤ በፍቅር ያጠመቅሽኝ
ዓለም በእጄ ምን ይጎድልብኛል
ፍቅር ንግስት አንቺን አድሎኛል
መርጦኛል”
ያየህይራድ አላምረው ከምንም ነገር በላይ ሀገሩን ይወዳል። ስለ ሀገሩ አብዝቶ ያስባል። ይብሰለሰላል። እንደሌሎቹ የሙዚቃ ድርሰቶቹ ሁሉ÷ ስለ ሀገሩ ኢትዮጵያ የከተባቸው የሙዚቃ ግጥሞች ሲበዛ ጉልበታም ናቸው።

ስለ ኢትዮጵያ አስቦ ከፃፋቸው የሙዚቃ ግጥሞች ቀዳሚው በ1970ዎቹ አጋማሽ ኩኩ ሰብስቤ የተጫወተችው “ይህቺ ናት ሀገሬ” የተሰኘው ግጥም ነው። ይኼ የሙዚቃ ግጥም ከፍ ባለ ትጋት እና ጥልቅ በሆነ የሀገር ፍቅር ተሰርቷል። የዚያ ዘመኗን ኢትዮጵያም እንደተወለወለ መስታወት ጥርት አድርጎ ያሳያል፦
“ይህቺ ነች ይህቺ ነች ሀገሬ
ፍልቅልቅ መንደሬ”
ሙዚቃው ከላይ የሰፈሩትን አዝማች ስንኞች ከፊት አስቀድሞ ወደ ታች ሲወርድ “ይህቺ ነች” ተብላ በተገለፀችው ሀገር ውስጥ ያለን የዕለት ተዕለት ክዋኔ እና የህይወት መስተጋብር ወደ መዘርዘሩ ይሸጋገራል።

ከጎታ ቀንሳ ያወጣችውን ሽንብራ መጅ እየገፋች የምትፈጭ እናት፣ ማልዶ በሬዎቹን የጠመደ እና እየፎከረ መሬት የሚሰነጥቅ ገበሬ፣ የሚቦርቅ እንቦሳ፣ የሚያገሳ በሬ፣ ገሳ ለብሶ ከብቶቹን የሚያግድ እረኛ፣ መቀነቷን ታጥቃ ጭራሮ የምትለቅም ጉብል የሀገር መልክ ሆነው ተስለዋል÷ በ “ይህቺ ነች ሀገሬ” የሙዚቃ ግጥም ውስጥ።

ደግሞ በሌላ የሀገርን መልክ በሚኩሉ ስንኞቹ ያዘረዘረ ስንዴ፣ ያሸተ ባቄላ፣ መዓዛው የሚያውድ ማሳ በአዕምሮዋችን ላይ ይስልብናል። በዚህ አረንጓዴ ስጋጃ በለበሰ ለምለም መስክ ላይ÷ እንስራ አዝለው ወደ ምንጭ የሚወርዱን እንስቶች በአካል የምናውቃቸው ያክል እንዲሰማን ያደርጋል÷ ግጥሙ።

ሌላኛው የዚህ የሙዚቃ ግጥም ሰበዝ÷ የእሳት ዳር ጨዋታ ነው። የእሳት ዳር ጨዋታ ትርጉሙ ብዙ ነው። ታሪክ ይነገርበታል። ምክር እና ተግሳፅ ይሰጥበታል። ቤተሰባዊ አብሮነት ይፀናበታል። የልጆች ዝንባሌ እና ተሰጥኦ ይለይበታል÷ያድግበታል። የማዳመጥ እና የመናገር ክህሎት ይዳብርበታል። ምክያቱም በእሳት ዳር ጨዋታ ሽማግሌዎችም፣ ወጣቶችም፣ ልጆችም፣ ሴቶችም፣ ወንዶችም … ይታደሙበታል። ገጣሚው ይኼንን የሀገር መልክ በኩኩ አንደበት እንዲህ ሲል ገልጦታል፦
“ሥራው ተጠናቆ ሁሉም ተሰብስቦ
እሳት እየሞቀ ዙሪያ ክብ ከቦ
እረኛው በዋሽንት እኔ በእንጉርጉሮ
አጅቦን ይዘፍናል ጎረቤቱም አብሮ”
ሀገራችን ይህቺ ነች። ይህቺም ነበረች። ዘመኗን የምትመስል ውብ ስዕል። ገጣሚው ቃላትን እንደ ካሜራ ዓይን ሰድሮ ነገሮችን የቀረጸበት እና የገለፀበት መንገድ ግን ይገርማል።

ያየህይራድ አላምረው ለኩኩ ሰብስቤ የሰጣት÷ ስለ ኢትዮጵያ የተብሰለሰለበት ሌላም ስራ አለው። “ኢትዮጵያ” ይሰኛል ርዕሱ። በዚህኛው ዘፈን ደግሞ የሀገራችንን ቀዳሚ ባለታሪክነት እና የትናንት ገናናነት በሚገባ ተናግሮበታል። የትናንት ታሪካችንን በኩራት ከመናገር ተሻግሮም÷ ነገ ዳግም ከፍ እንድትል ያለውን መሻትም ከትቧል። ይኼ የሀገራችን ዳግም መነሳት በአብራኳ ክፋዮች÷ በገዛ ልጆቿ እንደሚበሰር ተልሞ÷ በተከታዮቹ ስንኞች የልብ መሻቱን ገልጧል፦
“የአብራክሽ ክፋይ የማህፀን ፍሬሽ
በሃዘን በተድላሽ ልኑር አብሬሽ
ላፈራን ማህፀን ላዘለን ጀርባሽ
እንሆንሻለን ውለታ መላሽ”
ይኼ ዘፈን የሀገር ምንነት ላልገባቸው÷ ድህነቷ ለሚያሳፍራቸው÷ ተባብረው እንባዋን ከማበስ እና አንገቷን ከማቅናት ይልቅ ዘወትር ዕድፋቸውን ለሚያራግፉባት÷ የእናታቸውን ሆድ መርገጥ ለሚሹ የሙቀጫ ልጆች ዛሬም ድረስ ህያው ማስተማሪያ ነው።

ሌላኛው አብዝቼ የምገረምበት የያየህይራድ ድርሰት÷ የክቡር ዶክተር ጥላሁን ገሠሠ “ቆሜ ልመርቅሽ” ሙዚቃ ነው። “ኢትዮጵያ” ብሎ የማይጠግበው የሙዚቃ ግጥም ደራሲ በዚህ ስራው “እማ” ብሎ የጠራትን ሀገሩን “ዕድሜ ላንቺ” እያለ ስለውለታዋ ያመሰግናታል። “ራስሽን ችለሽ ባየሁሽ ማግስት ብሞትም አይቆጨኝም” ይላታል። ለሀገሩ ያለውን የፍቅር ጥግ ባሳየበት ግሩም ድረሰቱ፦
“ቆሜ ልመርቅሽ ተቀበይኝ እማ
ህይወትን መርቀሽ ሰጥተሽኝ እኔማ
ይህ ቀረኝ የምለው የሚቆጨኝ ባ’ለም
ኢትዮጵያ ዕድሜ ላንቺ ያላየሁት የለም፤
አንገትሽ ራስሽን ችሎ ልየውና
ማግስቱን ይውሰደኝ አሥር ሞት ይምጣና”
የሀገሩን ሠላም እና ጥጋብ÷ የሰንደቁን ከፍታ አብዝቶ መፈለጉን በሚገልፅበት በዚህ የሙዚቃ ግጥም÷ ለሀገሩ መልካሙን ሁሉ ከመመኘት ተሻግሮ÷ ጠላቶቿን ሲረግም ይደመጣል። “እማማ” እያለ በፍቅር ቃል እየጠራ እንዲህ ይላታል፦
“ሴራው ይክሸፍበት የመታብሽ አድማ
እጁን ሳር ያድርገው ጉልበቱን ቄጤማ
ካቀባበለብሽ ብረት ከደገነ
አምላክ ያግዝልሽ ላንቺ እየወገነ”
ይኼ ጉልበታም ብዕር የጨበጠ ጥበበኛ÷ ቃላት እንደልቡ የሚታዘዙለት ገጣሚ ስለ ሀገሩ ብዙ ቢልም÷ ሀገሩ ስለሱ ጥቂቱን እንኳን አላለችለትም። በእርግጥ የእርሱም መሻት በሱ በኩል ሀገሩን ማሳየት እንጂ በእሷ በኩል መታየት አይደለም። ይኼንን እውነታም ክትት ደብቅ ብሎ ኖሮ አሳይቶናል።

ምንም ቢሆን የሀገር ውድ ልጇ ነውና÷ ከሰሞኑ የተሰማው ድንገተኛ ህልፈቱ የሚያውቁትን ሁሉ አሳዝኗል። የህልፈቱ ዜና ከተሰማ ጀምሮ ሃዘናቸውን ሲገልፁ እና ሃሳብ ሲለዋወጡ የታዩት ግን ጥቂቶች ናቸው። ብዙሃኑ የሀገር ሰው ይኼንን ባለውለታውን አያውቀውም። በእርግጥ ዘንድሮ የሚታወቁት አዋቂዎቹ ሳይሆኑ ሌሎች ናቸው።