በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀዲያ ዞን ሚሻ ወረዳ በኩታ-ገጠም የለማ የስንዴ ማሳ ምልከታ ተደረገ

በ2017/18 ምርት ዘመን ላይ የተሻለ የሰብል አጠባበቅ እንዳለ ተገልጿል።

አርሶ አደር ጌታሁን ከበደ፣ አበራ ተሰማ እና ፍቅሬ ፎኮሮ በዞኑ የሚሻ ወረዳ የቡኡማ፣ የሌንችቾ እና የሰሜን ዋስገበታ ቀበሌ አርሶ አደሮች ሲሆኑ በግብርና ባለሙያዎች ክትትልና ድጋፍ በተደረገላቸው ድጋፍ በመስራታቸው የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

አርሶ አደሮቹ አክለውም በምርት አሰባሰብ ወቅት በዘመናዊ ማሽኖች ምርቱን ለመሰብሰብ እንዲቻል ከወዲሁ ትኩረት እንዲደረግ ጠይቀዋል።

የሚሻ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ዘርሁን ጋዶሬ፤ በወረዳው በምርት ዘመኑ አርሶ አደሮች የሙያ ግንዛቤ ማግኘታቸውን አብራርተዋል።

እስካሁን የሚታይ የሰብል በሽታ ባይኖርም ከአየር ንብረቱ ጋር ተያይዞ የዋግ በሽታ ስጋት እንዳለባቸው የጠቆሙት አቶ ዘርሁን፤ ለዚህም የመከላከያ መድኃኒት እና የአረም ማጥፊያ መድኃኒት እንደተረጨ ገልጸዋል።

የሀዲያ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ ዶክተር ሀብታሙ ታደሰ በበኩላቸው፤ በዞኑ ከ1 መቶ 56 ሺህ ሄክታር ማሳ 8 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ከማዳበሪያ አቅርቦት ጀምሮ ከወረዳ ግብርና ሃላፊዎች ጋር በጋራ እየሰራን ነው ያሉት ዶክተር ሃብታሙ ይህም በ2017/18 ምርት ዘመን የተሻለ ምርት ለማግኘት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

በምርት ዘመኑ በቂ ምርት እንዲገኝ አርሶ አደሩ የማሳ ክትትል ማድረግ እንዳለበት ያሳሰቡት ዶክተር ሃብታሙ፤ የሚከሰቱ የሰብል በሽታዎች ካሉም በፍጥነት ለወረዳው ማሳወቅ እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

በመስክ ምልከታው የሃዲያ ዞን ግብርና መምሪያ ሃላፊ ዶክተር ሃብታሙ ታደሰን ጨምሮ የዘርፉ አመራሮች፣ የሚሽ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ዘርይሁን ጋዶሬ፣ የዘርፉ ባለሙያዎች እና የአካባቢው አርሶ አደሮች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ: ሳምራዊት ያዕቆብ – ከሆሳዕና ጣቢያችን