በክልሉ በ2017 ዓ.ም በግሎባል ፈንድ ድጋፍ የኤች አይ ቪ/ኤድስና ሄፓታይተስ በሽታዎችን ለመከላከልና መቆጣጠር የተከናወኑ ተግባራት አፈጻጸም የግምገማ መድረክ ተካሂዷል።
በክልሉ ጤና ቢሮ በኤች አይ ቪ/ኤድስና የሄፓታይተስ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዘርፍ በግሎባል ፈንድ የገንዘብ ድጋፍ ሲከናወኑ በነበሩ የ2017 ዓ.ም ተግባራት አፈጻጸም የተገመገመበት መድረክ በጂንካ ከተማ ተካሂዷል።
በተመረጡ 8 ታዳጊ ከተሞች የበሽታዎቹን ስርጭት ለመግታትና ለመቆጣጠር በተደረጉ ጥረቶችና የተገኙ ውጤቶችና የተስተዋሉ ውስንነቶች ተፈትሸዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ማቲዮስ ጋርሾ፤ መድረኩ በዋናነት በክልሉ በ8ቱ ከተሞች የተከናወኑ ተግባራት አፈጻጸም የሚገመገምበት መሆኑን አንስተዋል።
ወቅታዊ ሪፖርቶች መነሻ በማድረግ በክልሉ ታዳጊ ከተሞች ኤች አይ ቪ/ኤድስንና የሄፓታይተስ በሽታዎች ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፉ መሆኑን የሚያመላክቱ አሃዞችንም በማሳያነት ያቀርባሉ።
በምርመራ በሽታዎቹ የተገኙባቸው ዜጎችም የህክምና አገልግሎቶ እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ ከ20 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ስለመቻሉም አንስተዋል።
ባለፉት አመታት የድጋፍ ስራዎች መቀዛቀዝ ለስርጭቱ መባባስ መንስኤ መሆኑን በመጥቀስ የመከላከል ስራዎች በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በከተሞች የበሽታዎቹ ስርጭት እየጨመረ መምጣቱን ከመድረኩ መገንዘብ መቻሉን በማንሳት መድረኩ ወቅታዊ ሁኔታን አገናዝቦ የቀጣይ ተግባራትን ለመከወን የሚያስችል መሆኑን የሚጠቅሱት ደግሞ የዲላ ከተማ ኤች አይ ቪ/ኤድስና ሄፓታይተስ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ስራ ሂደት መሪ አቶ ተመስገን ሽፈራው ናቸው።
በመድረኩ የ8ቱ ከተሞች አፈጻጸም ሪፖርቶች ቀርበው ውይይት የተደረገ ሲሆን በዚሁ መነሻ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችም ተመላክተዋል።
ዘጋቢ: ወንድሜነህ አድማሱ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
የማታ 1፡00 ዜና 24፤ ሀዋሳ፡ ጥቅምት 07/2018 ዓ.ም
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀዲያ ዞን ሚሻ ወረዳ በኩታ-ገጠም የለማ የስንዴ ማሳ ምልከታ ተደረገ
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ በሆርቲካልቸር ልማት ዘርፍ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገለጸ