ባህልን ለማስተዋወቅ የቆረጠች እንስት
ባህል ማለት አንድ ሠው በማህበረሠብ አባልነቱ የሚያገኘው እውቀት፣ እምነት፣ ልምድ እና ግብረ-ገብነትን ሲያጠቃልል የአንድ ማህበረሠብ የማንነቱ አሻራ ያረፈበት መገለጫም ነው፡፡ ይህን የተረዳችው የዛሬዋ እቱ መለኛችን ወግ፣ ልማድ፣ አመጋገብና አለባበስ ለማስተዋወቅ ትመኝ የነበረውን ሀሳብ ለማሳካት የተጋች ነች፡፡
ይህን ህልሟን ለማሳካት ብዙ ውጣ ውረጆችን መሻገር ነበረባት፡፡ ይህንንም በፅናት አልፋ ዛሬ ላይ ባህሏን ማስተዋወቅ በምትችልበት የሥራ መስክ ተሠማርታለች፡፡ ዓላማዋ ረጅም ቢሆንም መንገዱን ጀምራለችና ጥሩ ተስፋ እየተመለከተች ነው፡፡ እኛም ከዚህች ጠንካራ ወጣት መልካም ልምድና ተሞክሮዎች እንደሚገኝ በማመን የሕይወት ታሪኳን ልናስቃኛችሁ ወደድን፡፡
ሴሳ ታደለ ትባላለች፡፡ ተወልዳ ያደገችው በሲዳማ ክልል በቀድሞ አወቃቀር በአሮሬሳ ወረዳ ጭሪ ከተማ በአሁኑ ምስራቃዊ ሲዳማ ጭሪ ወረዳ ነው፡፡ ትምህርቷን የተከታተለችው ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል በቦና ወረዳ ሲሆን ከ7ኛ ክፍል እስከ ኮሌጅ ድረስ ያለውን በሐዋሣ ከተማ ነው የተከታተለችው፡፡ ከኮሌጅ በጤና ባለሙያነት ከተመረቀች በኋላ ትዳር መስርታ ኑሮዋንም ሥራዋንም በአዲስ አበባ አደረገች፡፡ ሆኖም ግን በመንግሥት ሥራ የቆየችው ለአጭር ጊዜ ነበር፡፡ ምክንያቱም ዝንባሌዋ ወደ ንግድ ሥራ ስላዘነበለ፡፡
በመሆኑም ኑሮዋን ከአዲስ አበባ ሳትለቅ ወንዶገነት ላይ የልብስ ሱቅ ከፍታ ሠራተኛ በመቅጠር ከመርካቶ አልባሳት እያመጣች መሥራት ጀመረች፡፡ በዚህ መልኩ ለሁለት አመታት ያህል ከሠራች በኋላ መመላለሱ አዋጭ እንደማይሆን ስትገነዘብ እዚያው አዲስ አበባ በመንግሥት ቢሮዎች ላይ አልባሳትን በመሸጥ ክፍያው በወር ደመወዝ የሚከፈልበትን ሁኔታ በማመቻቸት በብድር እየሰጠች ሥራዋን ቀጠለች፡፡
የቀድሞው ደቡብ ክልል በነበረበት ጊዜ እንደ አጋጣሚ ሆኖ የደቡብ ሴቶች ተሰብሰቡ የሚል ጥሪ ቀረበላቸው፡፡ ጥሪውን ተቀብላና የደቡብ ሴቶች አስተባባሪ ሆና ወደ ሥፍራው ሄደች፡፡ በሲዳማ ባህላዊ አልባሳትና የፀጉር አሠራር ተውባ ከቦታው ደረሰች፡፡ የሁሉም ባህል ሲተዋወቅ ሴሳ ታደለ ቁጭትና እልህ ያደርባት ጀመር፡፡
አዲስ አበባ ላይ ሥራውን ለመጀመር ከፍ ያለ ካፒታል ስለሚጠይቅ ባላት አቅም ጀምራ በማስፋት አቅም ስትፈጥር እስከ አለም ዳርቻ የተወለደችበትን ማህብረሠብ ባህል ለማስተዋወቅ በማሰብ ወደ ሐዋሣ ተመልሳ የሲዳማ ባህላዊ ምግብ ቤት በመክፈት ሥራ ጀመረች፡፡ ነገር ግን በርካታ ተግዳሮቶች ይፈትኗት ጀመር፡፡
ቤት ተከራይታ፣ ቤቱን በብዙ ወጭ አሳድሳ እና በባህላዊ ቁሳቁሶች አስማምራ ሥራ ልትጀምር ተዘጋጀች፡፡ ይሁን እንጂ አከራዮቿ ራሳችን ልንሠራበት ነው ቤቱን ልቀቂ ሲሏት፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ እንደዚሁ ተከራይታ ሥራ ስትጀምር ቤቱን በላይዋ ላይ ሲሸጡባት በበርካታ ፈተናዎች የታጀቡ ጊዜያት ለማሳለፍ ተገደደች፡፡ አሁን ላይ በተወሰነ ደረጃ በተረጋጋ መልኩ የሲዳማ ባህላዊ ምግብ ቤት ከፍታ ሥራዋን አሟሙቃ እየሠራች ትገኛለች፡፡
ቡርሳሜ፣ ጩካሜ፣ ኦሞልቾ፣ ጣጣሜ፣ ቲማ፣ ዱዋሜ፣ ቄቃሎ እንዲሁም የቤቱ ስፔሻል የሆነውን የገና ምግብ የተሰኘ እና ሌሎች ወደ አርባ የሚጠጉ የሲዳማ ባህላዊ የምግብ አይነቶችን አዘጋጅታ ለገበያ በማቅረብ ነው ሴሳ ታደለ እውቅና እያገኘች የመጣችው።
የተለያዩ ፌስቲቫሎች ሲኖሩ የሲዳማ ባህላዊ ምግብ በማቅረብ ከሚታወቁት መካከል ሴሳ አንደኛዋ ናት፡፡ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ይዘው ይሄዳሉ፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የውጭ ሀገር ዜጐች ሳይቀሩ በተለይ ሳይበላሽ ለረዥም ጊዜ መቆየት የሚችለውን ቡርሳሜ ወደ ውጭ ሀገር ይዘው እስከመሄድ ድረስ የተለመደ ምግብ መሆኑን ሴሳ አጫውታኛለች፡፡
ለወደፊት ባህሏን በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት በመውሰድ የማስተዋወቅ ፍላጐት እንዳላትም ነግራኛለች፡፡
ሴሳ ታደለ ከባህላዊ ምግብ በተጨማሪ የተለያዩ የማስዋብ ሥራዎችንም (ዲኮሮችንም) በመሥራት ትታወቃለች፡፡ በባህላዊውም ሆነ ዘመናዊ ዲኮር በማድረግ የተለያዩ ዝግጅቶችን ታደምቃለች፡፡
በፊቼ ጫምባላላ፣ በአፊኒ ፊልም ሥራ ላይ እና የተለያዩ አመታዊ ዝግጅቶችና ጉባኤዎች ሲኖሩ የተለያዩ ቢሮዎችን የማስዋብ ሥራ እንደምትሠራም ትናገራለች፡፡ የተለያዩ ባህላዊ አልባሳቶችን መሥራትና ማከራየት ተጨማሪ ሥራዎቿ ናቸው፡፡ በእነዚህም መካከል ባለቶና ቢሊቄ የሚባሉትንና መሠል የፀጉር ጌጣጌጦችንም በመሥራት ትታወቃለች፡፡
የሴሳ እናትና አባት ሴሳ ዛሬ ላለችበት ደረጃ ከፍተኛ ሚና ነበራቸው፡፡ ወላጅ እናቷ አሁን ድረስ በምግብ ዝግጅት ረገድ ግብአት በማቅረብ በግንባር ቀደምትነት እየደገፏት ይገኛሉ፡፡ ፌስቲቫል ሲኖርና ሥራዎች ሲበዙባትም ከቦና ድረስ በመምጣት ምግብ በማዘጋጀት ይረዷታል፡፡
ሴሳ እንደምትገልፀው በይፋ የሚታወቁት የሲዳማ ባህላዊ ምግቦች ውስን ናቸው፡፡ የእርሷ ፍላጐት ደግሞ ሁሉንም አይነት ምግቦች ማስተዋወቅ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በራሷ ፈጠራ ካለው ነገር ተነስታ የምታዘጋጃቸው የምግብ አይነቶችም ተጨማምረው ወደ አርባ አይነት ይደርሳሉ፡፡
“በቅርቡ አዲስ አበባ በነበረው ፌስቲቫል ሲዳማ በባህል ዘርፍ አንደኛ እንዲወጣ የእኛ አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነበር፡፡ በዚህም የሲዳማ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በተለያዩ ጊዜያት የእውቅና ሽልማትና የምስክር ወረቀት ሰጥቶኛል” ትላለች ሴሳ፡፡
“የሲዳማን ባህል በማስተዋወቅ ረገድ አሁንም ሠርቻለሁ ብዬ አላስብም” የምትለው ሴሳ ለወደፊት እያንዳንዱን ባህል በስፋት የማስተዋወቅ ጉጉት ነው ያለኝ ብላለች፡፡
ሴሳ ታደለ አሁን ላይ ለሠላሳ ዘጠኝ ዜጐች የሥራ እድል የፈጠረች ሲሆን በአጠቃላይ ሠባ የሚጠጉ ጊዜያዊ ሠራተኞችን በስሯ እያሠራች ትገኛለች፡፡
ከትንሽ ካፒታል ተነስታ በትጋትና ጥረቷ ዛሬ ላይ ከራሷ አልፋ ለዜጐች የሥራ እድል የፈጠረች ጠንካራ ሴት ናት፡፡ አሁን ድረስ በኪራይ ቤት እየሠራች ያለች በመሆኑ ሥራዋን አስፋፍታ ለመስራት እንዲያስችላት የክልሉ መንግስት የተሻለ የራሷን መስሪያ ቦታ ቢሠጣት ባህሏን ይበልጥ ለማስተዋወቅ እንደሚረዳት አንስታለች፡፡ ከዚህም ባለፈ ለዜጐችም የበለጠ የሥራ እድል መፍጠር ስለሚያስችላት የከተማ አስተዳደሩም ሆነ የክልሉ መንግሥት ድጋፍ ቢያደርግልኝ ጥሩ ነው ስትል ጠይቃለች፡፡
More Stories
ሀገር በያየህይራድ ብዕር
“የማቀርባቸው እቅዶች ህብረተሰቡን ያሳትፉ ነበሩ” – አቶ ግዛው በላቸው
የልጅነት ገናን በትዝታ፣ የአሁኑን በትዝብት