“የማቀርባቸው እቅዶች ህብረተሰቡን ያሳትፉ ነበሩ” – አቶ ግዛው በላቸው

“የማቀርባቸው እቅዶች ህብረተሰቡን ያሳትፉ ነበሩ” – አቶ ግዛው በላቸው

በአብርሃም ማጋ

አንድ እቅድ የህብረተሰቡን ፍላጐት ወደጎን የሚያደርግ ከሆነ አፈፃፀሙ ውጤታማ እንደማይሆን ሳይታለም የተፈታ ሃቅ ነው። ለዕቅዱ አፈፃፀምና ስኬት የህዝቡ ተሳትፎና ርብርብ ወሳኝ ሚና አለው፡፡ ለዚህም ነው የህብረተሰቡን ችግሮች በማቃለል ላይ ያላተኮረ እቅድ የግለሰብ እንጂ የማህበረሰቡ አይደለም የሚባለው፡፡ ህብረተሰቡ ደግሞ በማይመለከተው ጉዳይ ተሳትፎ ለማድረግ ተነሳሽነቱ አነስተኛ ስለሚሆን ውጤት መጠበቅ የማይታሰብ ይሆናልም።

የዛሬው ባለታሪካችን ለ41 ዓመታት ያህል በሃላፊነት በሰሩባቸው ቦታዎች ጥሩ ሥራ መሥራት የቻሉት ህብረተሰቡን የሚያሳትፍ እቅድ አውጥተው በመተግበራቸው እንደሆነ ያነሳሉ፡፡ ባለታሪካችን አቶ ግዛው በላቸው በቀድሞው አጠራር በአርሲ ጠቅላይ ግዛት፣ በከምባታ አውራጃ በሆሳዕና ከተማ ጊዮርጊስ ተብሎ በሚጠራ ሰፈር በ1938 ዓ.ም ነው የተወለዱት። የልጅነት ጊዜያቸውን በወቅቱ የቄስ ትምህርት ቤት ገብቶ መማሩ ቅድሚያ የሚሰጥ በመሆኑ አለቃ ጥዑመ ልሳን የቄስ ትምህርት ቤት ገብተው ለሁለት ዓመት ተምረው ጥሩ የማንበብና የመፃፍ ችሎታ በማዳበር አሳልፈዋል፡፡

በመቀጠልም በ1950 ዓ.ም ላይ ፊታቸውን ወደ ዘመናዊ ትምህርት አዙረው በሆሳዕና ራስ አባተ ቦዋ ያላው 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብተው በ6 ዓመት ውስጥ (ከ1950-1956) የ8ኛ ክፍል ትምህርታቸውን አጠናቀቁ፡፡ ይህንን ሊፈጽሙ የቻሉት በወቅቱ ለጐበዝ ተማሪዎች በዓመት ሁለት ክፍሎችን /ደብል ኘሮሞሽን/ የመማር እድል ስለሚሰጣቸው እየዘለሉ በመማራቸው ነበር፡፡

አቶ ግዛው በወቅቱ ከጐበዝ ተማሪዎች አንዱ በመሆናቸው በ1956 ዓ.ም ላይ የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈትነው ጥሩ ውጤት በማምጣት ነበር ወደ 9ኛ ክፍል የተዛወሩት፡፡ በወቅቱ 75 ከመቶ በላይ የሚያመጡ ተማሪዎች በወር 15 ብር እየተከፈላቸው የነፃ ትምህርት እድል የሚሰጣቸው በመሆኑ እሳቸውም የእድሉ ተጠቃሚ መሆን ቻሉ፡፡ ከጉብዝና ባለፈ የእድሉ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስፈልገውን ማስረጃ ካሟሉ በኋላ ወደ ወሊሶ ከተማ ራስ ጐበና ዳጨው ትምህርት ቤት ተልከው መማር ጀመሩ፡፡ ይሁን እንጂ ወደ ትምህርት ቤቱ ሲሄዱ ከተሰጣቸው 15 ብር ውጭ በቀጣዮቹ 4 ወራት ብሩ ሳይሰጣቸው ይቀራል፡፡ በዚህም ከፍተኛ ችግር ውስጥ ይወድቃሉ፡፡

መጀመሪያ አካባቢ ስለብሩ ሲጠይቁ በጀቱ ስላልፀደቀ ነው በቅርቡ ይፈፀምላችኋል የሚል ምላሽ ይሰጣቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ አንድ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃና ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ጉብኝት በሚያደርግበት ወቅት ተማሪዎች አመፅ አንስተው ግምባሩን በድንጋይ ወርውረው በመፈንከታቸው የመንግስት ቁጣ ብርቱ ሆነባቸው፡፡

በዚህም የሚሰጠው ገንዘብ እንዲቆም መንግስት ውሳኔ ሲያስተላልፍ እሳቸው ትምህርታቸውን ለመማር ባለመቻላቸው ወደ ሆሳዕና ከተማ ለመመላለስ ተገደዱ፡፡ 1957 ዓ.ም ተገባዶ በ1958 አዲስ ዓመት በሆሳዕና ከተማ የ9ኛና 1ዐኛ ክፍል ትምህርታቸውን መከታተል የሚያስችላቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲከፈት ያቋረጡትን ትምህርታቸውን የመማር እድል አግኝተው በመማር በ1959 ዓ.ም የ1ዐኛ ክፍልን አጠናቀቁ፡፡ በወቅቱ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የሚጠናቀቀው 10ኛ ክፍል በመሆኑ ብሔራዊ ፈተና ከተፈተኑ 26 ተማሪዎች ሁለቱ ብቻ ነበሩ የማለፍ ዕድል ያላጋጠማቸው፡፡

እሳቸው ለዲኘሎማ ፕሮግራም የሚያበቃቸውን ውጤት በማምጣት ደብረብርሃን መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ገብተው በመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ማስተማርና መምራት የሚያስችላቸውን ሥልጠና ለሁለት ዓመት በመከታተል (ከ1960-1961) ተመረቁ፡፡ የሥራ ዓለምን ለመቀላቀል በወጣ ዕጣ ሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት፣ ጀምጀም አውራጃ፤ አዶላ ወረዳ፣ ዘምባባ ውሃ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ደርሷቸው በርዕሰ መምህርነት ተመድበው መሥራት ጀመሩ።

በትምህርት ቤቱም በርዕሰ መምህርነት እስከ 68 ዓ.ም ድረስ ለ7 ዓመታት ያህል አገልግለዋል፡፡ በወቅቱ በአካባቢው ለትምህርት ይሰጥ የነበረው ትኩረት አነስተኛ ስለነበረ ጥቂት ተማሪዎች ብቻ ይማሩ እንደነበረ ይገልፃሉ፡፡

በወቅቱ የነበረውን የግንዛቤ እጥረት ለማስወገድ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን ሳይናገሩት አላለፉም፡፡ በየቤቱና በየገበያው እየዞሩ ለአካባቢው ህበረተሰብ ትምህርት በመስጠት ግንዛቤ በማስጨበጥ ረገድ ከፍተኛ ሥራ በመሥራታቸው የተማሪምች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በጥሩ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱንም አንሥተዋል፡፡ አሉ የሚባሉ ምሁራኖች ከትምህርት ቤቱ ፈልቀው እስከ ሳይንቲስት ድረስ የደረሱ ስለመኖራቸውም አውስተዋል፡፡ በትምህርት ቤቱ ለሰባት ዓመት ያህል ካገለገሉ በኋላ በ1969 ዓ.ም ወደ ወላይታ አውራጃ፣ ቦሎሶ ሶሬ ወረዳ፣ አረካ ከተማ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተዛውረው በርዕሰ መምህርነት ተመድበው መሥራት ጀመሩ፡፡

በርዕሰ መምህርነት አንድ አመት እንደሠሩ በወቅቱ በነበራችው የአመራር ብስለት ተመዝነው በ197ዐ ዓ.ም የአረካ ከተማ ከንቲባ ሆነው ተሾሙ። በከንቲባነት ለሁለት ዓመታት ያህል ሲሰሩ የርዕሰ መምህርነቱን ቦታ ውክልና ስጥተው ነበር፡፡

በወቅቱ በከተማዋ በከንቲባነት በሠሩባቸው ጊዜያት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡ ለአብነት ያህል ከተማዋን በማካለል የህግ ሰውነት እንዲኖረው ማድረግ፣ ከኢትዮ-ከካናዳ መንግሥት ጋር በመጻጻፍ በተገኘው ፈንድ ለመጀመሪያ ጊዜ በከተማዋ የቧምቧ ዝርጋታ በማከናወን ህብረተሰቡን የንፁህ ውሃ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ችለዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ከዋዱ ድርጅት ጋር በመነጋገር በ12ዐ ሺህ ብር ጀነሬቴር ገዝተው ነዋሪው የማብራት ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረጋቸው ዋና ዋና ተግባራት እንደሆኑ አብራርተዋል፡፡ ጀነሬተሩ በጣም ትልቅና የነዋሪውን ህዝብ ሙሉ ለሙሉ ተጠቃሚ ያደረገ በመሆኑ በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትና ተወዳጅነትን እንዲያተርፉ አስችሏቸዋል፡፡

ከዚያም በ1973 ዓ.ም ወደ ሲዳማ አውራጃ ተዛውረው ሀዋሳ ታቦር 1ኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት በርዕሰ መምህርነት ተመድበው መሥራት ጀመሩ፡፡ በዚህም ዓመት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጀመሩትን የክረምት ትምህርት ጨርሰው በትምህርት አስተዳደር በዲኘሎማ ተመርቀዋል፡፡ በመቀጠልም በሐዋሣ ታቦር 1ኛና መለስተኛ ሁለኛ ደረጃ ትምህርት በርዕሰ መምህርነት ለአንድ አመት ተኩል ካገለገሉ በኋላ፤ በ74 ዓ.ም በየካቲት ወር የሲዳማ ክፍለ ሀገር ትምህርት ቤቶች ጽ/ቤት ኘላንና ኘሮግራም ክፍል ሃላፊ ሆነው አመርቂ ውጤት በማስገኘት እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ ለ1ዐ ዓመት ሠርተዋል፡፡ በዚህን ወቅት ከ1974-1983 ዓ.ም ድረስ በሐዋሣ ከተማ ከ1-ዐ4 ቀበሌ በሊቀመንበርነት ተመርጠው ጥሩ ተግባር ፈጽመዋል፡፡ ለአብነት ያህል የሲዳማ ባህል አዳራሽ ሲሰራ ሚናቸው ከፍተኛ ነበር፡፡

በዚህ መሃል በ1976 ዓ.ም በጀርመን ሀገር የትምህርት ዕድል አግኝተው ለስድስት ወራት ተከታትለው በኘላንና ስታስቲክስ ትምህርት በዲኘሎማ ተመርቀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር ሆነው በደቡብ አፍሪካ፣ በዛምቢያና በሞዛምቢክ የተለያዩ የሙያ ጉብኝት አድርገው ተመልሰዋል፡፡ በ1986 ዓ.ም የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ሲቋቋም በፕላንና ስታስቲክስ ክፍል የስታስቲክስ ክፍል ኃላፊ ሆነው እስከ 1994 ዓ.ም ድረስ አመርቂ ሥራ ሠርተዋል፡፡

በ1995 ዓ.ም የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ወደ ሃላባ ልዩ ወረዳ ትምህርት ቤቶች አዛውሯቸው የጽ/ቤቱ የትምህርት ኘሮግራም ኃላፊ ሆነው ለ7 ዓመታት ያህል ካገለገሉ በኋላ በ2ዐዐ2 ዓ.ም የጡረታ መብታቸውን አስከብረዋል፡፡ በአጠቃላይ በመንግሥት ሥራ ላይ 41 ዓመት ማገልገላቸውንም መረጃዎቻቸው ያመላክታሉ፡፡

ባለታሪካችን የሲዳማ ክፍለ ሀገር ትምህርት ቤቶች ጽ/ቤት የፕላንና የኘሮግራም ሃላፊ ሆነው በሠሩባቸው ወቅት በትምህርት ማሰፋፊያ ሥራዎች ላይ ትልቅ ተግባር ፈጽመዋል፡፡ ትምህርት በማስፋፋት ረገድ በፕላንና በፕሮግራም አመራር ሥራቸው ብዙ የ1ኛ፣ የመለስተኛ እና ከፍተኛ የሁለተ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን እንዲከፈቱ አድርገዋል፡፡

ለአብነት ያህል የኮምቦኒ፣ የለኩ፣ የአለታ ወንዶ፣ የሀገረ ሰላም፣ የቦሬ፣ የዋደራ፣ የነጌሌ ቦረና፣ የሞያሌ፣ የያቤሎ፣ የሀገረ ማሪያም፣ የአረካ፣ የበዴሳ፣ የጋቼኖና የመሳሰሉትን ሁለተኛ ከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን እንዲሠሩ አቅደው ተግባራዊ ሆነዋል፡፡ በመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃም የአረካ፣ የበዴሳ፣ የጋቼኖ፣ የአለታ ወንዶ፣ የቦሬ፣ የዋደራ፣ የሻኪሶ፣ የሀገረማሪያም፣ የገራማ፣ የቀርጫ፣ የሜጋ የመሳሰሉት ትምህርት ቤቶች የተሠሩት እሳቸው ባወጡት ዕቅድ /ኘሮግራም ነበር፡፡ በአጠቃላይ ከመምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ጀምረው በሰሩባቸው 41 ዓመታት፤ 23 የሚደርሱ ሽልማቶችንና የዕውቅና የምስክር ወረቀቶችን አግኝተዋል፡፡

ለአብነት ያህል በደብረብርሃን ከተማ የዲኘሎማ ትምህርታቸው በሚማሩበት ወቅት ጐን ለጐን በሰሩት የጐልማሶች ትምህርት የማስተባበር ሥራ ገና በጅምሩ በ196ዐ ዓ.ም የምስክር ወረቀት አግኝተዋል፡፡ በ1961 ዓ.ም ዕጩ መምህር ሆነው የኢትዮጵያ ዕጩ መምህራን ማህበር አባልና የኘሮግራሙ ተከታታይ ሆነው በማገልገላቸውና በተለይም ማህበሩ የደብረብርሃንን ህዝብ ለማስተማር ባቋቋመው የማታ ትምህርት ቤት በማስተማር አገልግሎታቸው በተፈለገ ጊዜ በዚሁ ሥራ ባለማቋረጥ ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል፡፡

በ1982 ዓ.ም በሀዋሣ ከተማ በተካሄደው የመምህራን ትምህርት ባለሙያዎች የተሃድሶ ሴሜናር ላይ ተሳትፈው የምስክር ወረቀት አግኝተዋል፡፡ በ1985 ዓ.ም በትምህርት ሚኒስቴር የባለሙያዎች ማሰልጠኛ ማዕከል የተሰጠውን የፕላንና የፕሮጀክት ዝግጅት ስልጠና ስላጠናቀቁ የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ልዩ ባህሪያቸውን ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፡- “ልዩ ባህሪዬ ህብረተሰቡን ማዕከል ያደረገ አገልግሎት መሰጠት ነው፡፡ ሥራዬን ከሌሎች ነገሮች አብልጩ እወደዋለሁ” በማለት ገልፀዋል፡፡

በማከልም ከሥራቸው ያሉትን ሠራተኞቻቸውንና ከጐናቸው ያለውን ህብረተሰብ አማክለው ሰለሚያሠሩና ስለሚያሳትፉ ሁሌ ውጤታማ እንደነበሩ አንስተዋል፡፡ ከሠራተኞቻቸው ጋርም ጥሩ የሥራ ግንኙነት ነበራቸው፡፡ ከአድሎዓዊነትና ከጥቅማጥቅም ተገዥነት የፀዱና ሀቅንና እውነትን ተከትለው የሚጓዙ አባታዊ መሪ እንደነበሩም ያብራራሉ፡፡ በተጨማሪም ጥፋት ሲገኝ ለቅጣት የማይቸኩሉና በምክር የሚያስተምሩ እንደነበሩም አብረዋቸው የሰሩ ወዳጆቻቸው ይመሰክራሉ፡፡

የመግቢያና መውጫ ሠዓታቸውን የሚያከብሩና ከሥራቸው ያሉ ሠራተኞች የእሳቸውን ፈለግ እንዲከተሉ በጣም የሚጥሩ ናቸው፡፡ ከራሳቸው ጥቅም ይልቅ ለህዝብ ተጠቃሚነት ከፍተኛ ቦታ ሰጥተው የሚንቀሳቀሱ በመሆናቸው በሁሉም ዘንድ ተወዳጅነታቸውና አክብሮታቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ከማህበረሰቡ ጋር የነበራቸው ግንኙነት ምን እንደሚመስል ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፡- “እኔ የማቀርባቸው ዕቅዶች ህብረተሰቡን የሚያቅፉ ናቸው፡፡ ይህ በመሆኑም ህብረተሰቡ በሙሉ ሃይሉ በጉልበትም በገንዘብም ይተባበረኛል” በማለት ገልፀዋል፡፡

አቶ ግዛው በላቸው ወደ ትዳር ዓለም ያገቡት በ1964 ዓ.ም ሲሆን 2 ወንዶችና 3 ሴቶች በድምሩ የ5 ልጆችና የ10 የልጅ ልጆች አባት ናቸው፡፡ የመጀመሪያ ወንድ ልጃቸው በአካውንቲንግ ትምህርት ተመርቆ፤ በአሁኑ ጊዜ አውስትራሊያ ሄዶ በግል ሥራ ላይ ተሠማርቶ እየሠራ ይገኛል፡፡ ሁለተኛ ሴት ልጃቸው በኮምፒውተር ሳይንስ ተመርቃ የመንግሥት ሠራተኛ ነች፡፡ ሁለተኛው ወንድ ልጃቸው ኢንተርናሽናል የእግር ኳስ ዳኛ ነው፡፡ አንዲት ሴት ልጃቸው በህግ ትምህርት ከሐዋሣ ዩኒቨርስቲ በሁለተኛ ድግሪ ተመርቃ በአሁኑ ጊዜ በአሜሪካን ሀገር የግል ሥራ ትሠራለች፡፡ የመጨረሻ ሴት ልጃቸው ደግሞ አውስትራሊያ ትኖራለች፡፡

ይህ የባለታሪኩ ምርጥ ተሞክሮ በሌሎችም ዘንድ መለመድ እንዳለበት እየጠቆምን የዛሬን በዚሁ ቋጨን ሠላም፡፡