የግብርናው ዘርፍ ካለው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅም አንፃር ጥራቱንና ወቅታዊነቱን የጠበቀ መረጃ ማቅረብ እንደሚገባ ተጠቆመ

የግብርናው ዘርፍ ካለው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅም አንፃር ጥራቱንና ወቅታዊነቱን የጠበቀ መረጃ ማቅረብ እንደሚገባ ተጠቆመ

ሀዋሳ፡ ጥር 07/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የግብርናው ዘርፍ ካለው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅም አንፃር ጥራቱንና ወቅታዊነቱን የጠበቀ መረጃ ማቅረብ እንደሚገባ በማእከላዊ ስታስቲክስ አርባምንጭ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ገለፀ።

የኢትዮጵያ ግብርና ናሙና ቆጠራን አስመልክቶ በየደረጃው ለሚገኙ አመራርና ባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በአርባምንጭ ከተማ ተሰጥቷል።

በማእከላዊ ስታስቲክስ አርባምንጭ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ስሜ አንበሴ የምግብ ዋስትናና የኑሮ ደረጃ ከፍ ለማድረግ የግብርና ምርት ጥራትና ስርጭት እንዲሁም የአርሶአደሩን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የናሙና ቆጠራው አይነተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

የግብርናው ዘርፍ ካለው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅም አንፃር ጥራቱንና ወቅቱን የጠበቀ የግብርና ስታስቲክስ መረጃ ማቅረብ፣ በግብርናና በገጠር ልማት ዙሪያ ፖሊሲዎችን ለመንደፍ ብሎም ዕቅዶችን ለማቀድና ለመከታተል ሚና ይኖረዋል ሲሉ አክለዋል ።

የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት ለበርካታ አመታት በአገሪቱ በናሙና በተመረጡ አከባቢዎች የግብርና የናሙና ጥናት በማካሔድ መረጃዎችን ለተጠቃሚዎች እያደረሰ መቆየቱን የጠቆሙት አቶ ስሜ ይህ ታሪካዊ ቆጠራም የተሳካ እንዲሆን በየደረጃው የሚገኙ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል ።

የጋሞ ዞን አስተዳር ተወካይ አቶ በርገኔ በቀለ በበኩላቸው መረጃ ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት መሆኑን አውስተው ሀገሪቱ እየዘመነችና እያደገች ከመሔዷ ጋር የሚመጣጠን ጥራትና ብቃት ያለው መረጃን ማድረስ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ብቁ መረጃን ተደራሽ በማድረግ የሀገሪቱን እድገት ከማገዝ ባሻገር ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ወሳኝ ሚና የሚጫወት በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካል ወቅታዊና የተደራጀ መረጃን ለማድረስ የሚደረገውን ጥረት የናሙና ቆጠራው የሚደግፍ መሆኑንም አብራርተዋል።

በግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው የተገኙ አካላት አስተያየትና ማብራሪያ የሚፈልጉ ሀሳቦችን የሰነዘሩ ሲሆን ከመድረኩም ማብራሪያና ምላሽ ተሰጥቶበታል።

የኢትዮጵያ የግብርና ናሙና ቆጠራ ከ22 አመታት በኋላ የሚደረግ ሲሆን በአርባምንጭ ከተማም ከ 8 ዞኖች የተገኙ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ በሳይንሳዊ ዘዴ በተመረጡ 305 የከተማና 1ሺህ 406 የገጠር አከባቢዎች መረጃዎችን የመሰብሰብ፣ ማጠናቀር፣ መተንተንና ሪፖርቱን ለተጠቃሚዎች የማሰራጨት ተግባር እንደሚያከናውንም ተመልክቷል።

ዘጋቢ ፡ ተመኙህ ገረሱ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን