የሀዲያ ዞን ፋይናንስ መምሪያ ለ2018 በጀት ዓመት ከ10 ቢልዮን ብር በላይ በጀት ለተለያዩ የልማት ስራዎች እንዲውል በተገቢው እንደሚሠራ ገለፀ

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 20/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሀዲያ ዞን ለ2018 በጀት ዓመት የተመደበ ከ10 ቢልዮን ብር በላይ በጀት ግልጽነት እና ተጠያቂነት ባለው መልኩ የተለያዩ የልማት ስራዎች ላይ እንዲውል በተገቢ እንደሚሠራ የዞኑ ፋይናንስ መምሪያ አስታወቀ።

የየሀዲያ ዞን ፋይናንስ መምሪያ የመንግሥት ፋይናንስ ዘርፍ ኃላፊና የመምሪያው ምክትል ኃላፊ አቶ አማኑኤል ገ/ማርያም ለዞኑ በ2018 በጀት ዓመት ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውል ከ10 ቢልዮን ብር በላይ በጀት መመደቡን አስረድተዋል።

ከበጀቱ ከ6 ቢልዮን ብር በላይ ከዞኑ ገቢ የሚሰበሰብ ሲሆን ቀሪው በመንግሥት በኩል እንደሚሸፈን አቶ አማኑኤል ገልጸዋል።

ከዚህም ውስጥ አብዛኛው በጀት ለመንግሥት መስሪያ ቤት ሠራተኞች የደመወዝ ክፍያና ስራ መስኪያጃ የተያዘ እንደመሆኑ ከደመወዝ ክፍያ ጋር ተያይዞ ክፍተት እንዳይፈጠር ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

አክለውም በዞኑ ባሉ ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች እንዲሳለጡ የዞኑ ፋይናንስ መምሪያ የድርሻውን እንደሚያበረክት ጠቁመዋል።

ከነዚህ ፕሮጀክቶች ውስጥ ለረጅም ጊዜ ግንባታው ተቋርጦ የቆየው የሀዲያ የባህል ማዕከልን ጨምሮ በሆሳዕና ከተማ አስተዳደር የልማት ስራዎች እንዲሁም በወረዳዎች በሚሠሩት በጤና፣ በትምህርት፣ በውሃና በሌሎች ተቋማትም ድርሻ ወስዶ እንደሚሠራ አቶ አማኑኤል አብራርተዋል።

ተቋሙ በበጀቱ ላይ የግልጻኝነትና ተጠያቂነት መሪ ተግባራዊ ማድረጉን የጠቆሙት ምክትል ኃላፊው፥ ማንኛውም ሰው የፋይናንስ አሠራር ደንብ ጠብቆ መስራት እንደለበትና አሠራሩን የጣሰ አካል ቢኖር በህግ ተጠያቂ እንደሚሆን አስገንዝበዋል።

የዞኑ ፋይናንስ መምሪያ፣ በወረዳዎችም ሆኑ በከተማ አስተዳደሮች የፋይናንስ አሠራር ከመዘርጋቱም በሻገር በቅርብ የክትትልና ድጋፍ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑንም ምክትል ኃላፊው አቶ አማኑኤል ገልጸዋል ።

በተገልጋዮች ዘንድ ቅሬታ እንዳይፈጠርና ብልሹ አሠራር እንዳይኖር የፋይናንስን መመሪያ አውቆና ተረድቶ እንዲሁም ተጠያቂነትን ተገንዝቦ ስርዓቱንም ጠብቆ መስራት ውጤታማ ያደርጋል ብለዋል።

ዘጋቢ: መንግሥቱ ፊጣሞ – ከሆሳዕና ጣቢያችን