የመንግስትን ሀብት በአግባቡ በመምራት ከብክነት መታደግ እንደሚገባ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ጥር 07/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የመንግስትን ውስን ሀብት በአግባቡ በመምራት ከብክነት መታደግ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዋና ኦዲተር መ/ቤት አስታወቀ።
ዋና ኦዲተር መ/ቤቱ በፋይናንስ ግዥ እና በውስጥ ኦዲት አሠራር ዙሪያ ለክልሉ መንግስት ከፍተኛ አመራሮችና የኦዲት ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በአርባምንጭ ከተማ እየሰጠ ይገኛል።
በስልጠናው ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር አቶ አባይነህ አቹላ ውስን የመንግስት ሀብትን በአግባቡ በመምራት ከብክነት መታደግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የፖለቲካ ተሿሚዎች የተሻሻሉ የግዥና የንብረት አስተዳደር መመሪያዎችን በአግባቡ ተግባር ላይ በማዋል ከክፍተት የፀዳ አሠራር ማስቀጠል እንዳለባቸው አክለዋል።
በክልሉ መንግስት የግዥ አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 70/2017 ሥርዓቶች ላይ ለክልሉ መንግስት ከፍተኛ አመራሮችና የኦዲት ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛልም ብለዋል።
የስልጠናው ዋና ዓላማ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት የሚመራባቸው የግዥና የንብረት አስተዳደር የህግ ማዕቀፎች ላይ ግንዛቤን ለማሳደግ መሆኑንም ገልፀዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ተሻሽለው በቀረቡ የግዥ አፈጻጸም መመሪያ ሥርዓቶችና አዲስ በተጨመሩ የግዥ አፈጻጸም ሥርዓቶች መሠረት ሥራዎችን ለማቀላጠፍ እንደሚሻ ተገልጿል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት የግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 25/2016 መሠረት የግዥ አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 70/2017፣ የንብረት አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 71/2017 በአግባቡ ተግባር ላይ በማዋል ከክፍተት የፀዳ አሰራርን ማስቀጠል እንደሚገባም ተጠቁሟል።
ስልጠናው የክልሉ መንግስት ለግዥ የሚያውለውን ከፍተኛ ገንዘብ ቁጠባንና ውጤታማነትን ለማረጋገጥ በሚያስችል ሥርዓት ጥቅም ላይ ለማዋል ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑ ታውቋል።
ስልጠናው በተለያዩ ሰነዶች ዙሪያ ለ3 ተከታታይ ቀናት የሚቆይ መሆኑ ታውቋል።
ዘጋቢ፡ ሰለሞን አላሶ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
More Stories
ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ ከተማዋ ፅዱና ውብ እንድትሆን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው – የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በቋሚነት የሚደገፉበት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የቡርጂ ዞን አስተዳደር አስታወቀ
“አንድ ሰው ወደዚህች ምድር ሲመጣ እንዲሰራ የተፈቀደለትና የሚጠበቅበት ነገር አለ” – ታደሰ ገብሬ /ጃክሰን/