ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመግባት ዕድል ያገኙ ተማሪዎች የበለጠ ውጤታማ ለመሆን ትምህርታቸው ላይ ብቻ ሊያተኩሩ እንደሚገባ መልዕክት ተላለፈ

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 21/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመግባት ዕድል ያገኙ ተማሪዎች የበለጠ ውጤታማ ለመሆን ከአላስፈላጊ ውሎና ተግባር ተቆጥበው የየዕለት ተግባራቸው መማር ሊሆን እንደሚገባ የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ አሳሰበ።

ዩኒቨርስቲው ለ2018 የትምህርት ዘመን በዋና ግቢ ከ880 በላይ እንዲሁም በዱራሜ ካምፓስ ከ600 በላይ አዲስ ገቢ የተማሪዎች አቀባበል እያደረገ ይገኛል።

የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ በዋናው እና ዱራሜ ካምፓስ በተለያዩ የትምህርት መርሀ ግብር ከ22ሺ በላይ ነባር ተማሪዎችን በማስተማር ላይ እንደሚገኝም ከዩኒቨርስቲው የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ የአስተዳደር እና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ኤርሚያስ ሞሊቶ በአዲስ ገቢ ተማሪዎች አቀባበል ወቅት እንደገለጹት፥ የሰላም አምባሳደር ወደ ሆነው ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ እንኳን በሰላም መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፥ ዩኒቨርስቲው የሰላም አምባሳደር እንዲሆን የግቢ እና የአከባቢው ማህበረሰብ እንዲሁም የጸጥታ አካላት በቅንጅት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት አዲስ ገቢ ተማሪዎች አቀባበል በማድረግ የአከባቢው እና የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብና የጸጥታ አካላት የተለመደውን ትብብር እያደረጉ መሆኑን ዶክተር ኤርሚያስ ተናግረዋል።

ዩኒቨርስቲው በዋና ግቢ ከ880 በላይ በዱራሜ ካምፓስ ከ600 በላይ ተማሪዎችን በ2018 የትምህርት ዘመን አዲስ ተማሪዎችን መቀበሉን ጠቁመዋል።

ወደ ዩኒቨርሲቲዎች የመግባት ዕድል ያገኙ ተማሪዎች የበለጠ ውጤታማ ለመሆን ከአላስፈላጊ ውሎና ተግባር ተቆጥበው የየዕለት ተግባራቸው መማር ሊሆን እንደሚገባ ዶክተር ኤርሚያስ አሳስበዋል።

ዩንቨርስቲው የግቢውንና የአከባቢውን የአገልግሎት ማዕከላት ምቹ እና ሰላማዊ ከማድረግም ባሻገር የህክምና መስጫ ክሊኒክ እና ሌሎች የመማር ማስተማር ሂደትን ውጤታማ የሚያደርጉ የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል በቂ ዝግጅት ማድረጉንም ዶክተር ኤርሚያስ ጠቁመዋል።

በዕለቱ ልጆቻቸውን ለመሸኘት የመጡ አንዳንድ ወላጆችና አዲስ ገቢ ተማሪዎች በሰጡት አስተያየት ዩኒቨርስቲው ያደረገው አቀባበል ወላጆችንና ተማሪዎችን ከስጋት ነጻ የሚያደርግና ተማሪዎች የስነልቦና ጉዳት ሳይደርስ ሙሉ ትኩረታቸውን ትምህርት ላይ እንዲያደርጉ የሚያስችል ነው ብለዋል።

ዘጋቢ: ሳሙኤል መንታሞ – ከሆሳዕና ጣቢያችን