በትምህርት ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችን በቅንጅት መቅረፍ የአገር ብልፅግናን ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥር የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ

በትምህርት ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችን በቅንጅት መቅረፍ የአገር ብልፅግናን ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥር የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ

በክልሉ የመማር ማስተማር ሂደትን ለማሳካት የሚካሄደውን የተማሪዎች የምገባ መርሀ ግብር ትግበራ የአማራና ትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ አመራሮች ጎብኝተዋል።

ለትምህርት ቤቶች መሻሻልና የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በየደረጃው የሚከናወኑ ቅንጅታዊ አሰራሮችን ማጠናከር እንደሚገባም ተመላክቷል።

በየትምህርት ቤቶች የሚደረገው የሥራ ጉብኝት በዋናነት እየተካሄደ ያለው የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም አተገባበርና እየተስተዋለ ያለዉን ተጨባጭ ለዉጥ በመገምገም ተሞክሮዎችን ለማስፋፋት የታለመ መሆኑን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሀላፊ ዶክተር አበባየሁ ታደሰ አስረድተዋል።

በአዲሱ ትምህርት ፍኖተ ካርታ ላይ የተመላከቱና በትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሂደትን ለማሳካት የምገባ ፕሮግራም ያለውን ፋይዳና በተቀናጀ አሰራር የመጣውን ለዉጥ በማበረታታትና ችግሮችን በመለየት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ዶክተር አበባየሁ ገልጸዋል።

በአካባቢው ከሚመረቱ ምርቶች ተማሪዎችን በመመገብ የመማር ማስተማር ሥራን ማሳካት የሚቻልበትን አሰራር ማስፈን ልምድ የሚቀሰምባቸዉ መልካም ተግባራት እንደሆኑም ዶክተሩ አስገንዝበዋል።

አያይዘዉም ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች ለትምህርት ጥራት መስፈንና የትምህርት ቤቶች መሻሻል መርሐ ግብርን ለማሳካት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እየተካሄደ ያለው የተማሪዎች የምገባ መርሀግብር የተቀናጀ አሰራርን የተከተለ ስለመሆኑ በመስክ ባደረጉት ጉብኝት ማረጋገጥ መቻላቸውን የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ አመራርና የምገባ ፕሮግራም ተጠሪ አቶ አፅበሃ ሀይሌእግዚ ገልጸዋል።

ትምህርት ቤቶች የዉስጥ ገቢያቸውን በተለያዩ ተግባራት ለማሻሻል የሚያደርጉት ጥረት ምርጥ ተሞክሮ የሚቀመርባቸዉ እንደሆነም አቶ አፅበሃ አስረድተዋል።

የምገባ መርሐ ግብሩ የተማሪዎች መጠነ ማቋረጥ ከማስቀረቱም ባለፈ ዘርፈብዙ ጠቀሜታ እንዳለው በደቡብ ኦሞ ዞን በማሌ ወረዳ ትምህርት ፅህፈት ቤት የምገባ ፕሮግራም ተጠሪ አቶ ተሰማ ተስፋዬና በወረዳው የኮይቤ ሙሉ መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ኢያሱ ወልዴ ገልጸዋል።

በትምህርት ቤት ደረጃ ከመርሀግብሩ ጋር ተያይዞ በተቀናጀ አግባብ የትምህርት ቤት መሻሻልን ለማረጋገጥና የዉስጥ ገቢን ለማጎልበት በሚያከናዉኗቸዉ በጓሮ አትክልት ልማትና በተለያዩ ተግባራት ዉጤታማ መሆናቸውን ነዉ ርዕሰ መምህሩ የሚናገሩት።

በምገባ መርሐግብር የታቀፉ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እንደሚሉት ተረጋግተው ትምህርታቸውን በመከታተል የተሻለ ዉጤት ማስመዝገብ ችለዋል።

ዘጋቢ፡ ዳኜ ጥላሁን – ከጂንካ ጣቢያችን