በየአካባቢው በሚዘወተሩ ስፖርቶች ውጤታማ ለመሆን የበቁ አሰልጣኞችን ማፍራት እንደሚገባ ተገለጸ

በየአካባቢው በሚዘወተሩ ስፖርቶች ውጤታማ ለመሆን የበቁ አሰልጣኞችን ማፍራት እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ጥር 06/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በየአካባቢው በሚዘወተሩ ስፖርቶች ውጤታማ ለመሆን የበቁ አሰልጣኞችን ለማፍራት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ገለፀ።

የአንደኛ ደረጃ የቅርጫት ኳስ የአሰልጣኞች ስልጠና በወልቂጤ ከተማ እየተሰጠ ይገኛል።

በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኙ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የሚዘወተሩ ስፖርቶች ላይ ውጤታማ ለመሆን የበቁ አሰልጣኞችን ለማፍራት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትልና የስፖርት ዘርፍ ሀላፊ አቶ ሰይፈ አለሙ ገልጸዋል።

በክልሉ በስፋት ከሚዘወተሩና በውድድሮችም አመርቂ ውጤት ከሚመዘገብባቸው ስፖርቶች መካከል ቅርጫት ኳስ ቀዳሚ መሆኑን ያነሱት አቶ ሰይፈ ይህንን አቅም በተሻለ ሁኔታ ለመጠቀም ስልጠናው ማስፈለጉን ገልጸዋል።

በአካልና አዕምሮ የበለጸገ ትውልድ ለማፍራት ስፖርት የሚወጣው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ እሸቱ ተሾመ ናቸው።

የቅርጫት ኳስ ስፖርት በክልሉ ቀድሞ ጀምሮ ህብረተሰቡ ይጫወተው እና ይዝናናበት እንደነበር ሲያነሱ ስልጠናው ወልቂጤ ላይ ሲደረግ ከንድፈ ሀሳብ ባለፈ በተግባር ውጤታማ እንዲሆኑና ያለመ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።

ወጣቶች በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች እንዲታቀፉ በማድረግ ውድድሮች ላይ ተሳትፈው አመርቂ ውጤት እንዲያስመዘግቡ እየተሰራ እንደሚገኝ ያነሱት የጉራጌ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ሀላፊ አቶ ሙራድ ረሻድ ሲሆኑ መሰል ስልጠናዎችን በማስተባበር ውጤቱ ዘላቂነት እንዲኖረው እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ታዳጊዎችን በሰለጠኑ አሰልጣኞች ማሰልጠን ልጆች በስነምግባር ታንጸው በስፖርት ክህሎት ዳብረው እንዲያድጉ ፋይዳው የጎላ መሆኑን የገለጹት የስልጠናው አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ዘመዴ በቀለ ናቸው።

አንድ አሰልጣኝ በእውቀትና በቴክኒክ ሲያሰለጥን ቡድኑ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚችል አንስተው፥ ስልጠናው በሁለት ክፍሎች በመክፈል በተግባርና በንድፈ ሀሳብ የታገዝ መሆኑን ኢንስትራክተር ዘመዴ አክለዋል።

መሰል ስልጠናዎች መዘጋጀታቸው የአሰልጠኞችን አቅም ከማሳደግ ባለፈ ለቅርጫት ኳስ ማደግ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ያነጋገርናቸው የስልጠናው ተሳታፊዎች ገልጸዋል።

ሰልጠናው በዛሬው የመክፈቻ ውሎ የወልቂጤ ከተማ ቅርጫት ኳስ ቡድን ልምምድ የመስክ ምልከታ ሲያደርግ ለተከታታይ ቀናት የሚቀጥል መሆኑን ተገልጿል።

ዘጋቢ: ዳዊት ዳበራ – ከወልቂጤ ጣቢያችን