ክቪቻ ክቫራትስኬሊያ ለስድስት ወራት ከሜዳ ይርቃል
የፈረንሳይ እግር ኳስ ግዙፍ ክለብ ፓሪሰን ዠርማን በከባድ የጉዳት ቀውስ ውስጥ መውደቁን አስታውቋል።
ክለቡ ትናንት ምሽት ከባርሴሎና ጋር ባደረገው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ አሸናፊ ቢሆንም፣ ዋነኞቹን ቁልፍ ተጫዋቾቹን በጉዳት ማጣቱ ለቀጣዮቹ የውድድር መርሃ ግብሮች ትልቅ ስጋት ፈጥሯል።
ትናንት ማታ ከባርሴሎና ጋር በተደረገው እና 4 ለ 2 በሆነ ውጤት በተጠናቀቀው ጨዋታ ላይ በጉዳት ከሜዳ እንዲወጣ የተገደደው የፊት መስመር ተጫዋቹ ክቪቻ ክቫራትስኬሊያ፤ በቀኝ ጉልበቱ ላይ የፊት ለፊት የጅማት መበጠስ (ACL) ጉዳት እንዳጋጠመው ይፋ ሆኗል።
የቀድሞው የናፖሊ ኮከብ በጨዋታው ላይ ከባርሴሎናው ተከላካይ ዣቪ ኤስፓር ጋር ከተጋጨ በኋላ ተቀይሮ ከሜዳ መውጣቱ ይታወሳል።
የክለቡ የሕክምና ቡድን ዛሬ ጠዋት ባከናወነው የኤምአርአይ (MRI) ምርመራ ጉዳቱ የከፋ መሆኑን አረጋግጧል።
ተጫዋቹ በቀጣዮቹ ቀናት የቀዶ ጥገና ሕክምና የሚደረግለት ሲሆን፣ ቢያንስ ለቀጣዮቹ ስድስት ወራት ከእግር ኳስ ሜዳ እንደሚርቅ ፓሪሰን ዠርማን በሰጠው መግለጫ አሳውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በምሽቱ ጨዋታ ጉዳት አስተናግደው በተመሳሳይ ተቀይረው ከሜዳ የወጡት የፊት መስመር አጥቂው ኡስማን ደምቤሌ እና የቡድኑ አምበል ማርክሂንዮስ እንዲሁ ለቀጣዮቹ ሳምንታት በሕክምና ቆይታ ላይ እንደሚቆዩ ክለቡ አረጋግጧል።
በውድድር ዘመኑ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ የሚገኘው የሉዊስ ኤንሪኬ ስብስብ፣ እነዚህን ቁልፍ ተጫዋቾች በጉዳት ማጣቱ በቻምፒዮንስ ሊግ እና በሊጉ ጉዞው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ተጠቁሟል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
“በአጨዋወታችን ላይ የሚሰነዘረው ሂስ ጥቂቶችን ብቻ የሚወክል ነው” – ሚኬል አርቴታ
ማንችስተር ዩናይትድ ከሊድስ ዩናይትድ ጋር ሲፋለም አርሰናል ከሜዳው ውጪ ወሳኝ ጨዋታ ይጠብቀዋል
የቀድሞው የማንችስተር ሲቲ እና የሌስተር ሲቲ ኮከብ ሪያድ ማህሬዝ አዲስ ክለብ አግኝቷል።