የከብቶቻቸውን ዝርያ በማዳቀል ከወተትና ሥጋ ምርት ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን በኣሪ ዞን የሚገኙ አርሶ አደሮች ገለፁ

የከብቶቻቸውን ዝርያ በማዳቀል ከወተትና ሥጋ ምርት ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን በኣሪ ዞን የሚገኙ አርሶ አደሮች ገለፁ

የከብቶቻቸውን ዝርያ በማዳቀልና በማሻሻል ከወተትና ሥጋ ምርት ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን በኣሪ ዞን ጋዘር ከተማ የሚገኙ አርሶአደሮች ተናግረዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ግብርና ዩኒት በበኩሉ፤ የከብቶችን ዝርያ ለማሻሻል የማዳቀል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፆ፤ የአርሶአደሩ ግንዛቤ ከጊዜ ወደጊዜ እየተሻሻለ በመምጣቱ በማዳቀል ተጠቃሚ የሚያደርጋቸውን የከብት ዝርያ የመጠቀም ሁኔታ እያደገ መሆኑን አስታውቋል፡፡

አርሶ አደር ተካ አስቶ፣ ጩቢ ማሎ፣ ማቴዎስ ኤዳልቆና ሌሉች አርሶአደሮች እንደገለፁት፤  ከሀገር ቤት ዝርያ ከብቶች ከሚገኘው ምርት ይልቅ የተዳቀሉ ከብቶች በወተቱም ሆነ በስጋ ምርት የተሻሉ በመሆናቸው መጠቀም መጀመራቸውን ገልፀዋል።

‎

‎የሀገር ውስጥ ዝርያ ላሞች የወተት ምርት በቀን በአማካይ ከአንድ ሊትር በላይ እንደማያልፍ የጠቆሙት አሰተያየት ሰጪዎቹ፤ ከተዳቀሉ ዝርያዎች ግን በቀን በአማካይ እስከ 7 ሊትር እንደሚያገኙ ተናግረዋል፡፡

አርሶአደሮቹ አክለውም የተዳቀሉት ከብቶች ከወተት ምርታማነታቸው ባለፈ በሥጋ ምርታቸው የተሻሉ መሆናቸውን ገልፀው፤ በዝርያ ማሻሻል ተግባር ላሞቻቸውን በተለያየ ምክንያት ማዳቀል ያልቻሉ አርሶ አደሮችን ከእኛ ተማሩ ሲሉም መክረዋል፡፡

‎

‎የጋዘር ከተማ አሰተዳደር ግብርና ዩኒት መሪ አቶ ጠሀ አባድር በበኩላቸው፤ የተለያዩ ዝርያዎችን በማላመድ በሩብ ዓመቱ በመደበኛ 325 ላሞችን ለማዳቀል አቅደው 125 እንዲሁም በሲንክሮናይዜሽን 400 ታቅዶ 270 ማከናወን መቻሉን ገልጸዋል።

‎

‎አርሶአደሩ አሁን ላይ የሀገር ውስጥ ዝርያ ላሞች የወተት ምርት አነስተኛ መሆኑን በመረዳታቸው የተሻሻሉ ላሞችን በማርባት ተጠቃሚ የመሆን ልምዱ እያደገ ነው ብለዋል፡፡

አሁን ላይ የተሻሻሉ ዝርያዎች በቀን ከ6 አስከ 12 ሌትር እንደሚሰጡ ገልፀው፤ የከተማው አርሶአደሮች ከ200 ሌትር በላይ ወተት ወደ ጂንካ በመላክ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን ተናግረዋል።

‎

‎አቶ ጠሀ አክለውም የተሻሻሉ ዝርያዎች በሥጋ ምርትም ከፍተኛ መሆናቸውን ጠቁመው፤ አርሶአደሩ ከ100 እስከ 200 ሺህ ብር በመሸጥ ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን አመላክተዋል።

‎

‎ዘጋቢ፡ ከተማ በየነ – ከጂንካ ጣቢያችን