ወጣቶች የስራ ጠባቂነት አመለካከትን በማስወገድ የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ በመሰማራት ለሀገራቸው እድገት አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለባቸው ተጠቆመ
ወጣቶች የስራ ጠባቂነት አመለካከትን በማስወገድና የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ በመሰማራት፣ ከራሳቸው አልፎ ለሀገራቸው እድገት አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለባቸው ተመላክቷል፡፡
“ገሪል ኢፌክት የኛ ጊዜ” የተሰኘ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀዲያ ዞን ሌሞ ወረዳ ከተለያዩ ቀበሌያት ለተውጣጡ ከ600 በላይ ወጣቶች በሆሳዕና ከተማ የክህሎትና የአቅም ግንባታ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።
በመርሐ-ግብሩ ላይ የተገኙት የሌሞ ወረዳ ረዳት የመንግስት ተጠሪና የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዳዊት መሐመድ፤ የሀገር ትልቅ ሀብት የሆነውን ወጣቱን ኃይል ያላካተተ የሀገር እድገት ሊታሰብ እንደማይችል ገልጸዋል።
አቶ ዳዊት አክለውም «ሰው ሁሉ ሲፈጠር እኩል በመሆኑ ለለውጥና ለስራ ዕድል ፈጠራ ዋናው ነገር አእምሮን ማሰራት ነው» ብለዋል።
ከስደት ይልቅ ኢትዮጵያ ውስጥ የተሻለ ሀብትና ዕድል ስላለ ወጣቶች ስደትን አማራጭ ማድረግን ትተው “አይቻልም” የሚለውን አስተሳሰብ “እችላለሁ” በሚል መንፈስ ተክተው ከትንሽ ተነስተው በሀገራቸው ሰርተው ለመለወጥ መትጋት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የድርጅቱ የተሳትፎ ድህነት ቅነሳ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስተባባሪ አቶ ደምሴ ሎብዱኖ እንደገለጹት፤ ስልጠናው ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው ብለዋል።
የስልጠናው ዋና ዓላማም የወጣቶችን አስተሳሰብ በመቀየርና አቅማቸውን በማጎልበት በሀገራቸው ሰርተው መለወጥ እንደሚችሉ ግንዛቤ መፍጠርና በተለያዩ የስራ ፈጠራ ዘርፎች ውጤታማ እንዲሆኑ ማስቻል ነው ብለዋል።
በተጨማሪም በስራ ፈጠራ ዘርፍ ስኬታማ የሆኑ ወጣቶች የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ መድረኩ መመቻቸቱን አብራርተዋል።
በዚህ ስልጠና ላይ በስራ ፈጠራ ውጤታማ የሆኑ ወጣቶች ተሞክሯቸውን ያካፈሉ ሲሆን ለሁለት ቀናት የሚቆየው ይህ የአቅም ግንባታ መርሐ-ግብር ወጣቶች በተለያዩ የስራ ዕድል ፈጠራ ዘርፎች እንዲሰማሩ መንገድ የሚከፍት መሆኑ ተጠቁሟል።
ዘጋቢ፡ ታምራት አለሙ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
በርዕሰ መስተዳድር አቶ ፍቅሬ አማን የተመራ ህዝባዊ ውይይት በካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው
በርዕሰ መስተዳደር አቶ ፍቅሬ አማን የሚመራ ህዝባዊ ውይይት በኮንታ ዞን አማያ ከተማ በመካሄድ ላይ ነው
የመደመር መንግስት አሳታፊ የሆነ የልማት ተግባራትን እያከናወነ የህዝብን የመልማት ጥያቄዎች እየመለሰ ይገኛል – የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ፍቅሬ አማን