“በአጨዋወታችን ላይ የሚሰነዘረው ሂስ ጥቂቶችን ብቻ የሚወክል ነው” – ሚኬል አርቴታ
የአርሰናል አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ቡድናቸው በዚህ የውድድር ዘመን የሚያሳየውን የአጨዋወት ዘይቤ አስመልክቶ የሚሰነዘረው ትችት “በጣም ጥቂት ከሆኑ ወገኖች” ብቻ የሚነሳ ነው ሲሉ አስተባብለዋል።
መድፈኞቹ በያዘነው የውድድር ዘመን በሁሉም ውድድሮች ካደረጓቸው 11 ጨዋታዎች 10ሩን በማሸነፍ በጥሩ አቋም ላይ ቢገኙም፣ በብዛት ግቦችን አለማስቆጠራቸው እና ወደ ኋላ አፈግፍገው በሚከላከሉ ቡድኖች ላይ ክፍተቶችን ለማግኘት በመቸገራቸው ምክንያት ትችቶች ሲሰነዘሩባቸው ቆይተዋል።
ባለፈው እሁድ አርሰናል ኖቲንግሃም ፎረስትን 1 ለ 0 በረታበት ጨዋታ፣ ብቸኛዋን የማሸነፊያ ግብ ተቀይሮ የገባው ኖኒ ማዱኤኬ በ80ኛው ደቂቃ ላይ ነበር ያስቆጠራት።
ይህም ቡድኑ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች ያስቆጠረውን የግብ መጠን 11 ብቻ አድርጎታል።
ባለፈው የውድድር ዘመን አርሰናል የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ሲያነሳ በሊጉ ትንሹን ግብ ያስቆጠረበት እና ከቆመ ኳስ ደግሞ ከፍተኛውን ግብ ያስመዘገበ ቡድን የነበረ ቢሆንም፣ ዘንድሮ ግን በምንም ዓይነት ውድድር እስካሁን ከቆመ ኳስ ግብ ማስቆጠር አልቻለም።
በቡድናቸው የአጫዋወት ዘይቤ ዙሪያ ለተነሳላቸው ጥያቄ አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ሲመልሱ”ቡድኑ ጥሩ አልተጫወተም የሚል ስሜት የለኝም፤ ምክንያቱም የአጫዋወት ዘይቤያችን ድንቅ እንደነበር ነው የሰማሁት። በርካታ ግቦችን አስቆጥረናል፣ ኳስ በብዛት ተቆጣጥረናል፣ ብዙ የግብ ሙከራዎችን አድርገናል፣ እንዲሁም የተለያዩ ተጫዋቾች በጨዋታው ተሳትፈዋል። እስካሁን ከቆመ ኳስ ግብ ባናስቆጥርም፣ የዘንድሮው ታሪካችን ከባለፈው ዓመት ሙሉ በሙሉ የተለየ ነው” ብለዋል።
አርቴታ አክለውም “ቡድኑን የሚተቹት በጣም ጥቂቶች ናቸው ብዬ አስባለሁ። ሌሎቹ ግን እውነታውን ያውቃሉ። ዘንድሮ የተጫወትንበትን እና ጨዋታዎችን የበላይ ሆነን የመራንበትን መንገድ በጣም እንደወደዱት አምናለሁ፤ ይህንንም በውጤታችን አስመስክረናል” ሲሉ ተናግረዋል።
ሆኖም አሰልጣኙ ወደ ኋላ አፈግፍገው በሚከላከሉ ቡድኖች ላይ ቡድናቸው ገና ማሻሻል የሚገቡት ነገሮች እንዳሉ አምነዋል።
“ወደ ኋላ አፈግፍጎ የሚከላከል ቡድን እና አጥቅቶ የሚጫወት ቡድን የተለየ አቀራረብ ይፈልጋሉ። ከፎረስት ጋር በነበረው ጨዋታ እንኳን ከዚህ የተሻለ ነገር ማድረግ እንችል ነበር፤ ይህም በእጃችን ያለ ነገር በመሆኑ ክፍተታችንን በግልጽ ማወቅ አለብን” ሲሉ አብራርተዋል።
የቡድኑ ግብ ጠባቂ ዳቪድ ራያ በበኩሉ፣ ተጫዋቾች በአጫዋወታቸው ላይ በሚነሱ ጥያቄዎች እንዳልተበሳጩ ገልጾ የአርሰናል የዘንድሮ ውጤት ለራሱ መልስ እንደሚሰጥ ተናግሯል።
“ሰዎች የራሳቸው አስተያየት አላቸው፤ እኛም የራሳችን እይታ አለን” ሲል የተናገረው ራያ “በመጨረሻም በዚህ የውድድር ዘመን ካደረግናቸው 11 ጨዋታዎች የተሸነፍነው አንዱን ብቻ ነው፤ ይህንን ውጤት ‘አሰልቺ’ ወይም ‘ሚያበሳጭ’ ካላችሁት ምን እንደሚባል አላውቅም። እኛ እግር ኳስ መጫወትን እንወዳለን፤ በየቀኑ ወጥተን ማሸነፍ ደስ ይለናል፣ ዋናው ነገር እርሱ ነው” ብሏል።
መድፈኞቹ ዛሬ ምሽት 4 ሰዓት ላይ በቻምፒየንስ ሊጉ ከባየርን ሙኒክ ጋር በአሊያንዝ አሬና ስታዲየም ወሳኝ ጨዋታ ያከናውናሉ።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
ማንችስተር ዩናይትድ ከሊድስ ዩናይትድ ጋር ሲፋለም አርሰናል ከሜዳው ውጪ ወሳኝ ጨዋታ ይጠብቀዋል
የቀድሞው የማንችስተር ሲቲ እና የሌስተር ሲቲ ኮከብ ሪያድ ማህሬዝ አዲስ ክለብ አግኝቷል።
አርሰናል ሰራተኞቹን ከስራ ሊያሰናብት ነው