የብሩኖ ፈርናንዴስ መኖሪያ ቤት ተዘረፈ
የማንችስተር ዩናይትድ አምበል ብሩኖ ፈርናንዴስ በሜዳ ላይ ከደረሰበት የሽንፈት ዋዜማ በኋላ ሌላ አሳዛኝ ክስተት አስተናግዷል።
ቡድኑ ረቡዕ ምሽት በሻምፒዮንስ ሊጉ ከጣሊያኑ ክለብ ኮሞ ጋር ባደረገው ጨዋታ 4 ለ 1 ከተረታ በኋላ፣ ምሽት ላይ ብሩኖ መኖሪያ ቤት በሌቦች መዘረፉ ተዘግቧል።
የቼሻየር ፖሊስ ባወጣው መግለጫ መሠረት፣ ዝርፊያው የተፈጸመው በእንግሊዝ የሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 2 ሰዓት ተኩል ገደማ ሲሆን፣ ሦስት ማንነታቸው ያልታወቀ ወንበዴዎች ወደ ተጫዋቹ መኖሪያ ቤት ሰብረው ገብተዋል።
አንድ የቅርብ ጎረቤት አጠራጣሪ እንቅስቃሴ በመመልከቱ ለአካባቢው ፖሊስ ጥቆማ መስጠቱ ተገልጿል።
ፖሊሶች በቦታው ሲደርሱ ዘራፊዎቹ ከአካባቢው ቢሰወሩም፣ ጌጣጌጦችን እና ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን ሌሎች ንብረቶች ይዘው መሰወራቸውን ዘ ቴሌግራፍ አስነብቧል።
በዝርፊያው ወቅት ብሩኖ ፈርናንዴስም ሆነ ቤተሰቡ በቤት ውስጥ አልነበሩም።
ዘራፊዎቹ በቤቱ ውስጥ የቆዩት ከ5 ደቂቃ ላነሰ ጊዜ እንደሆነና ማንችስተር ዩናይትድ ለአምበሉና ለቤተሰቡ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቋል።
ይህ የዝርፊያ ወንጀል የተከሰተው፣ ፈርናንዴስ ከኮሞ ሽንፈት በኋላ የአሰልጣኝ ማይክል ካሪክን የታክቲክ አቀራረብ በይፋ ከተየቸም በኋላ ነው።
ተጫዋቹ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጠው አስተያየት“በዚህ ክለብ ውስጥ አሁንም ትኩረቱ ባለፉት የስኬት ዘመናት ላይ ነው፤ እኛ ግን ያኔ የነበሩት ሰዎች አይደለንም። ክለቡም ሆነ ተጫዋቾች ይህንን እውነታ ሊረዱት ይገባል” ሲል ተናግሯል።
በጨዋታው በ67ኛው ደቂቃ ላይ የተቀየረው ፈርናንዴስ፣ ክለቡ ካለበት የውጤት ቀውስ እንዲወጣና እውነታውን ተቀብሎ እንዲሰራ ጥሪ አቅርቧል።
የፈርናንዴስ አስተያየት በክለቡ አመራሮች ዘንድ ቅሬታን የፈጠረ ቢሆንም፣ አስተያየቱ በጨዋታው ብስጭት የተሰጠ በመሆኑ ምንም ዓይነት የዲሲፕሊን ቅጣት እንደማይጣልበት ተገልጿል።
በዚህም መሠረት ብሩኖ ፈርናንዴስ ቡድኑን በአምበልነት እየመራ እሁድ በኦልድትራፎርድ ከቦርንማውዝ ጋር በሚደረገው ወሳኝ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ላይ እንደሚሰለፍ ተረጋግጧል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ
የብሩኖ ፈርናንዴስ መኖሪያ ቤት ተዘረፈ

More Stories
የከብቶቻቸውን ዝርያ በማዳቀል ከወተትና ሥጋ ምርት ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን በኣሪ ዞን የሚገኙ አርሶ አደሮች ገለፁ
በርዕሰ መስተዳድር አቶ ፍቅሬ አማን የተመራ ህዝባዊ ውይይት በካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው
ወጣቶች የስራ ጠባቂነት አመለካከትን በማስወገድ የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ በመሰማራት ለሀገራቸው እድገት አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለባቸው ተጠቆመ