የልጅነት ገናን በትዝታ፣ የአሁኑን በትዝብት

በኢያሱ ታዴዎስ

ሕይወት የትናንት እና የዛሬ ውህድ ናት፡፡ ትናንት ያልተሰራ ማንነት ዛሬ በሚባለው የጊዜ ኡደት ውስጥ ስፍራ የለውም፡፡ ለዚህም የድሮ ትዝታዎቻችን የዛሬን ሕይወት እንድናጣጥም የሚያደርጉን ቅመሞች ናቸው፡፡ እኔም የገና የድሮ ትዝታዬን ላስቃኛችሁ። በልጅነት አዕምሮዬ ቢሆንም ገና የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ነው ስለሚባል ብቻ በደስታ እፍነከነክ እንደነበር አስታውሳለሁ። በዓሉን ያደምቅ የነበረው ደግሞ ሽርጉዱ ነው። ልጆች እንደ ልጅነታችን የምንሯሯጠው ቤት ማሰማመሩ ላይ ነበር፡፡ የገናን የቤት ድምቀት ደግሞ ያለገና ዛፍ አይታሰብም። የአንድ ቤት ልጆች ከሰፈራችን ልጆች ጋር ራቅ ወዳለ ስፍራ ተጉዘን ለገና ዛፍ የሚሆነውን የፅድ ተክል እስክናገኝ ድረስ እናዘግማለን፡፡ ለገና ዛፍ የሚሆነው የፅድ ዛፍ በመሆኑ ዛፉን ለማግኘት መኳተኑ የግድ ነበር። በአብዛኛው ዛፉ በመንግስት ይዞታ ስር በሚገኙ ግቢዎች ውስጥ ነበር መገኛው። ወደ መንግስት ግቢ ደፍሮ በመግባት ዛፍ መቁረጥ በራሱ ዘበት ነበር፡፡

ግን ደግሞ ጥበቃዎቹ ስለሚያዝኑልን ከፅዱ ቆርጠን ወደ ቤታችን ይዘን እንድንሄድ ይፈቅዱልናል፡፡ ይህ የሚሆነው ታዲያ ዕድል ከቀናን ነው፡፡ ዕድል ያልቀናው ልጅ የፅዱን አማራጭ ይተውና “ሸውሸዌ” የተባለውን በብዛት የሚገኝ ዛፍ ቆርጦ ቤቱን ለማሰማመር ይጠቀማል፡፡ የዚህን ልክ ዋጋ የተከፈለለትንም የፅድ ቁራጭ በትከሻችን ተሸክመን እንደ አመጣጣችን በእግራችን ወደ ቤታችን እንመለሳለን፡፡

የዚህን ጊዜ የወላጅ ምርቃቱ እንደ ክምር ጤፍ በላይ በላዩ ነው፡፡ “ጎሽ ልጆቼ አበጃችሁ፤ ሕይወታችሁ እንደ ልደቱ በብርሃን ይሞላ” ተብለን ከተመረቅን በኋላ ቤቱን ወደ ማስዋብ እናመራለን፡፡ ቤቱንም ያመጣነውን የገና ዛፍ በማቆም እላዩ ላይ ጥጥ፣ ፖስትካርዶችን፣ ፊኛዎችንና የግድግዳ መብራቶችን በመለጠፍ እናሰማምረዋለን፡፡ ቤት ማሰማመር ሲባል ደግሞ የቤቱን ሙሉ ፅዳትም ይመለከታል፡፡

እኛ እንደ ልጆች የአቅማችንን ተፍ ተፍ የምንልበትን የበዓል ዝግጅት በዚህ መልኩ እናጠናቅቃለን፡፡ ከአዋቂዎች ደግሞ ከዓይነ ሕሊናዬ የማይጠፋው በዓሉን በማስመልከት የሚከወነው የገና ጨዋታ ነው፡፡

ለነገሩ በእኔ ደረጃ ሳስበው “አዋቂዎች” አልኩኝ እንጂ ወጣቶች ነበሩ በአብዛኛው የገና ጨዋታ ላይ የሚሳተፉት፡፡ ገላጣ በሆነ ሜዳ ለሁለት ተቧድነው ለጨዋታው በተዘጋጀ ዱላ “ሩር” የተሰኘችውን መጫወቻ ኳስ እያሳደዱ፣ እነሱ ጋ ስትጠጋ እየለጓት ተጋጣሚያቸው ላይ ግብ ለማስቆጠር ይረባረባሉ፡፡

ቀንቶት ግብ ያስቆጠረ ቡድን ደስታው አይጣል ነው፡፡ ጨዋታውም ቢሆን ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ በናፍቆትና በደስታ ነው የሚካሄደው፡፡ ዘር፣ ብሄር፣ መደብ፣ ቋንቋ ሳይለያቸው ሰብዓዊነትን በሚያሳብቁ ስሜቶች ተሞልተው ፍልሚያቸውን ያደርጋሉ፡፡

ታዲያ ያ የደስታ ስሜት በተመልካችነት ወደ ታደምነው ልጆችም ይስተጋባ ነበር። በዓሉን ስናስበው እንድንናፍቀው ከሚያደርገን ነገር አንዱ ይኸው የገና ጨዋታ ነበር፡፡

የገናን ጨዋታ በባህላዊ መንገድ በዓሉን አስታከን የምንጫወተው እኛ (ኢትዮጵያዊያን) ብቻ መሆናችን ደግሞ በራሱ ኩራት ነው፡፡ ከዚያ ውጪ በዓሉ በተቃረበበት ጊዜ ወላጆቻችን የሚያደርጉት ዝግጅት ሌላው የማይረሳ ትዝታችን ነበር፡፡

ሁሉም እንደየኑሮው ደረጃ የየአቅሙን አድርጎ ማሳለፍ የግድ ቢሆንም አንዱ ከአንዱ መንፈሳዊ ቅናት አድሮበት ለመመሳሰል የሚያደርገው ጥረት የተለየ ነበር፡፡ የለውም የተባለ ቤተሰብ ቢያንስ ለበዓሉ ብሎ ከቋጠራት ገንዘብ አውጥቶ ቤት ባዶ ከሚሆን በሚል የቻለውን ሸምቶ ይመለሳል።

ቤቱም እንደ ቤተሰቡ አቅም በዓል በዓል በሚሸቱ ዝግጅቶች ይሞላል፡፡ እርግጥ በዓልን ተበድሮ የሚያሳልፍም ቢሆን ጥቂት አይደለም፡፡ የበዓሉን አከባበር ግን ልዩ የሚያደርገው ሁሉ በየቤቱ ምግብና መጠጡን ሙሉ አድርጎ ሲያበቃ ከወዳጅ ዘመዱ ጋር በጋራ መቋደሱ ነው፡፡ ያኔ እንደ ዛሬ ግለኝነት ባልበዛበት በዚያ ጊዜ፣ በዓል ለብቻዬ ብሎ ነገር አይታሰብም።

ጎረቤት ከጎረቤት፣ ዘመድ ከዘመዱ፣ ወዳጅ ከወዳጁ እንደ ኢትዮጵያዊ ባህል በመጠያየቅ ነበር በዓልን የሚያሳልፈው፡፡

ሥጦታ መለዋወጡም ሌላው ወግ ነበር፡፡ ገና ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሀጢአታችን ስርየት ከእግዚአብሔር አብ ዘንድ ሥጦታ ተደርጎ የተሰጠበትን (ወደ ዚህ ምድር የመጣበትን) መታሰቢያ በዓል የምናከብርበት ነው፡፡ ሰዎችም እርስ በእርስ ሥጦታ በመሰጣጠት እና ፍቅራቸውን በመገላለጽ ነው በዓሉን የሚያከብሩት፡፡

ያለው ለሌለው ያለስስት ያካፍላል፡፡ ያኔ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በማህበራዊ ሕይወት የተሳሰረ በመሆኑ ሰዎች እምብዛም ለግለኝነት አያጋልጡም ነበር፡፡ “ይህ የእኔ ድንበር ነው፤ ዘልቀህ እንዳትገባ” የሚል የተዓብዮ ፈሊጥ ቦታ አልነበረውም። ወዳጅ እንደ ወዳጅ እንጂ እንደባዳ አይታይም። አንድ ሰው ጓዳውም ሆነ ሳሎኑ ለወዳጁ ክፍት ነው፡፡ ይህ ማህበራዊ ትስስር በሴቶች ዘንድ ይበልጥ ይጠነክራል፡፡ ሴቶች እንጀራ፣ በርበሬም ሆነ የትኛውንም ጓዳቸው ውስጥ የተሟጠጠን ነገር የሚያሟሉት ከጎረቤታቸው ተበድረው ነው፡፡

አንዲት ሴት እንጀራ ቸግሯት ሌላኛዋን ብትጠይቅ የትኛዋም ሴት እያላት የለኝም አትልም፡፡ “ባይሆን ስትጋግሪ ትመልሺኛለሽ” ብላ ካላት ትሰጣታለች፡፡ ብቻ ቸርነት የማህበረሰቡ መለያ ነበር፡፡ በዓል ሲሆን ደግሞ ይለያል፡፡ ሁሉም ተሳስቦ ነው የሚያሳልፈው፡፡ አንዱ ጠግቦ ሌላው ባዶ ሆዱን በፍጹም አያድርም፡፡ በበዓል ሆድ ሁሉ ጠግቦ ነው የሚያድረው፤ ያለው ለሌለው በማካፈል፡፡ ታዲያ ይህ ሁሉ ያካፈልኳችሁ የልጅነት ትዝታዬ ነው፡፡

ዛሬስ? ካላችሁኝ ዛሬማ ብዙ ነገር ተለዋውጧል፡፡ የዛሬ በዓል አከባበር “ዘመናዊ” በተሰኘ የስስትና መረን ካባ ተሸፍኖ አጉል ነገር ውስጥ ከትቶን ኢትዮጵያዊነታችንን እያስረሳን ነው፡፡

የሥጦታ እና የፍቅር በዓል ተደርጎ በሚወሰደው የገና በዓል እንኳን ተቃራኒው ነው የሚስተዋለው፡፡ የገና ዛፉም ቢሆን ምዕራባዊያን አመጣሽ በሆነ አርቲፊሻል ዛፍ ተተክቷል፡፡ በዚያ ላይ ትርጉሙን በቅጡ በማናውቀው “ሳንታ” በተሰኘ ነጭ ሽማግሌ አሻንጉሊት ታጅቦ ከኢትዮጵያዊነት ወግ ወጣ ያለ ስርዓት ይስተናገድበታል፡፡

ወጣቶች እንደ በፊቱ ለበዓሉ ብለው ቤት አያሰማምሩም፡፡ የገና ጨዋታንም ከነአካቴው ረስተውታል፡፡ ብቻ ሥራዬ ብለው የተያያዙት የበዓል ዋዜማን በማስመልከት የሚዘጋጁ የሙዚቃ ድግሶችን በመታደም ነጭ ላባቸው እስኪወጣ ዳንኪራ መምታት ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ደግሞ ከፍቅረኞቻቸው፣ አሊያም ከጓደኞቻቸው ጋር ሌላ ዳንኪራ መወጣጫ ወደ ሆኑት የምሽት ክበቦች በመሄድ እነሱ እንደሚሉት “ዓለማቸውን” ይቀጫሉ፡፡ አስቡት እንግዲህ በዓሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሰው ልጆች ሀጢአት ለዓለም ቤዛ ይሆን ዘንድ በሥጦታነት የተበረከተበት ዕለት መታሰቢያ ነው፡፡

ወጣቱ ግን በዚህ በዓል ስም የሚተምመው ወደ ዋናው የሀጢአት መናኸሪያ ነው፡፡ እንዲያውም አሁን አሁን በዓሉን በዳንኪራ እና በሙዚቃ ድግስ የማያሳልፍ ሰው ጸረ-ዘመናዊ ተደርጎ ነው የሚወሰደው፡፡

በዳንኪራው ብቻ አያበቃም፤ መጠጥ፣ ከዚያም ስካር፣ ከዚያም … ብቻ የፅድቁን በዓል የሰይጣን የሀጢአት ፈረስ በመሆን ያሳልፉታል፡፡ በዕድሜ ጠና ያሉትም ቢሆኑ እንደ ድሮ ከወዳጅ ዘመድ ጋር እምብዛም በጋራ ሲያሳልፉ አይስተዋልም፡፡ ሁሉም በየጓዳው ጉድጓድ ውስጥ እንደመሸገ አይጥ ተቀርቅሮ ድምጹን አጥፍቶ ነው በዓሉን የሚያሳልፈው፡፡ ይህ ሲባል ግን ኢትዮጵያዊ እሴታቸውን ሳይረሱ ቤት ያፈራውን አቅም ከሌለው ጋር በማካፈል የሚያሳልፉ የለም ማለት አይደለም፡፡

ግን በአብዛኛው አሁን እየተስተዋለ ያለው እንደ ቀድሞው የጠበቀ ማህበራዊ ወዳጅነት አይደለም፡፡ ጎረቤት ከጎረቤቱ ጋር ተጠራርቶ ማዕድ ከመካፈል ይልቅ ሁሉም በየፊናው ቤቱን ጠርቅሞ ማሳለፍን ይመርጣል። ችግረኞችን መርዳቱም ቢሆን አስቦበት ሳይሆን፣ ምንአልባት በሩ ከተንኳኳ፣ እሱንም ትራፊ ምግብ ካለ ነው።

ይሄ ደግሞ ከበዛ ግለኝነት ወይም ደግሞ ራስ ወዳድነት የመነጨ ነው፡፡ አሁን አሁንማ የኑሮ ውድነቱ ምክንያት እየሆነ ለወዳጅ ጀርባ መስጠት እንግዳ ተግባር አይደለም። ኑሮ ውድነቱንም እኮ ያመጣው ስስት፣ ወይም ከልክ ያለፈ ግለኝነት ነው፡፡ ሥልጣኔ መስሎን ከማህበራዊው ሕይወት ይልቅ ግለኝነት መምረጣችን ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል፡፡

የቁጠባ ባህል በማዳበር የተሻለን ነገ መፍጠር አንዱ ብልሃት ነው። ነገር ግን ለወዳጅነት አጥር አበጅቶ “አትድረስብኝ አልደርስብህም” በሚል ግለ-ወግ ታስሮ እንደ ፍጥርጥር መሆን ሰብዓዊነትም ኢትዮጵያዊነትም አይደለም፡፡ እኛ የሚያምርብን አጥር ገደብ ሳይሆነን በክፉም በደጉ የወዳጃችንን ቤት እየጎበኘን ሰብዓዊ ስሜቶቻችንን ስንጋራ ነው። “ፍቅር ካለ አንድ እንጀራ ለአራት ሰው ይበቃል” ይባል የለ! በረከት የሚባለው የገንዘብ ክምችት ወይም የሃብት ማግበስበስ አይደለም፡፡ በረከት ማለት ያለችንን ጥቂቷን ነገር በፍቅር አብረን መቋደስ ነው፡፡ ይህንን ጥንት የምንታወቅበት መገለጫችንን አስቀጥለን ቢሆን ኖሮ እኮ ኑሮም አይከፋብንም ነበር።

ኑሮው የከፋው እኛ ስንከፋ ነው፡፡ ያው ምድር የዘር አይደል! የዘራነውን አጨድነው። ለማንኛውም የገና በዓል ባለንበት ዘመን ኢትዮጵያዊ መልኩን አጥቶ እንዳይሆን ሆኗል፡፡ በቅጡ ባልተረዳነው፣ ደግሞም ባልጠቀመን በምዕራባዊያን ወግ ተይዘን የራሳችንን ጥለነዋል፡፡ ዛሬም ግን የጥንቱን ማንሳት እንችላለን፡፡ ያውም እንደ አዲስ። ይህም የሚሆነው ወደ ሰብዓዊነታችንና የቀድሞ ኢትዮጵያዊ መልካችን ስንመለስ ነው፡፡