ከደን ምንጣሮ የፀዳ ቡና በማምረት አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን እተየሰራ ነው
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 03/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደንና አካባቢ ልማት ጥበቃ ቢሮ ከ”ፍሎር ኢትዮጵያ ፕሮጀክት” ጋር በመቀናጀት ከደን ምንጣሮ የፀዳ ቡና በማምረት አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን እየሰራ መሆኑን ገልጿል፡፡
ፕሮጀክቱ ከክልሉ ቢሮ ጋር በመቀናጀት የአየር ብክለትን በመከላከልና በደን ልማት አጠባበቅ ዙሪያ ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ለባለድርሻዎች ሰጥቷል፡፡
በመድረኩ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደን አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ ምክትልና የደን ልማት ዘርፍ ኃላፊ ዮሴፍ ማሩ (ዶ/ር) የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የተራቆቱ መሬቶችን በደን ለመሸፈን የሚደረገውን ጥረት ከግብ ለማድረስ ፍሎር ኢትዮጵያ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ ክስተቶች የተጎዱ መሬቶችን መልሶ ለማልማት ከፕሮጀክቱ ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን ኃላፊው በመግለፅ ለማህበረሰቡ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን በማሰራጨት ድጋፍ ማድረጉንም አንስተዋል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፍሎር ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አለምበጁ ክፍሌ እንደገለፁት፥ በተቀናጀ መሬት አያያዝ፣ የቡና ምርታማነትን ማሳደግና የምግብ ስርዓትን ማሳለጥ፣ የተፈጥሮን ደን መጠበቅና መንከባከብ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሰፍን በማድረግ ቀጣይነት ያለውን ልማት ለማስፋፋት ፕሮጀክቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው፡፡
የአየር ብክለት ለመከላከል ከ4 ሺህ 6 መቶ በላይ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃ በፓይለት ፕሮጀክቱ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጌዴኦ ዞን ባቀፋቸው በይርጋጨፌ፣ በወናጎና ኮቾሬ ወረዳ ማሰራጨታቸውንና በአጠቃቀም ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ስልጠና መስጠታቸውን አቶ አለምበጁ አብራርተዋል፡፡
በስልጠናው ከተሳተፉት ወ/ሮ ወጋየሁ ተስፋዬና ሌሎችም በሰጡት አስተያየት ባለሶስት ጉልቻ ምድጃ ሲጠቀሙ በጊዜያቸው ፣ በጤናቸውና በገንዘባቸው ይደርስ የነበረውን ብክነት ከፕሮጀክቱ የተሰጠው ማገዶ ቆጣቢ ምድጃ እንደቀነሰላቸው ተናግረዋል፡፡
ማገዶ ቆጣቢ ምድጃን ለፕሮጀክቱ በማቅረብ የስራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ወጣት ኤልያስ ማሩ ተናግሯል፡፡
ዘጋቢ፦ ውብሸት ኃ/ማርያም – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
የሣውላ ከተማ ህዝብ ምክር ቤት አባላትና ከፍተኛ አመራሮች የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን ተዘዋውረው ጎብኙ
ክርስቲያን የቡና ግብይትና ሁለገብ የሕብረት ሥራ ማህበር በቡና ጥራት ዙሪያ በልዩ ትኩረት እየሠራ መሆኑን ገለፀ
ደም መለገስ ለተጎዱ ወገኖች ህይወትን መስጠት፣ የአይን ብሌን መለገስ ደግሞ የህይወት ብርሀን መመለስ መሆኑ ተገለፀ