የሣውላ ከተማ ህዝብ ምክር ቤት አባላትና ከፍተኛ አመራሮች የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን ተዘዋውረው ጎብኙ
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 03/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሣውላ ከተማ ህዝብ ምክር ቤት አባላትና ከፍተኛ አመራሮች በከተማው እየተሠሩ ያሉ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
የኮሪደር ልማት፣ በህብረተሰብ ተሳትፎ የተገነባው የተጠርጣሪ ማረፊያ ቤት እንዲሁም የከተማው ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጽህፈት ቤት የተቋም ማዘመን ሥራዎች ምልከታ ተካሂዷል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የሣውላ ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍጹም ጳውሎስ በከተማዋ የተሰሩ የኮሪደር ልማትና የተቋም ማዘመን ሥራዎችን ባስጎበኙበት ወቅት እንደተናገሩት በመከናወን ላይ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ እንድትሆን ከማድረግ ባለፈ ገፅታዋን የቀየረ አረንጓዴና ነፋሻማነትን የሚያላብሳት መሆኑን ተናግረዋል ።
ኮሪደር ልማቱ የእግረኞችና የብስክሌት መንገዶችን፣ የሕፃናት መጫወቻ፣ የአካል ጉዳተኛ መንቀሳቀሻ፣ አረንጓዴ ቦታ፣ መዝናኛዎችን ያካተተ መሆኑን አብራርተዋል ።
ተቋምን ማዘመን ምቹ የሥራ ቦታን ከመፍጠር ባሻገር ለተገልጋዩ ማህበረሰብ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ብሎም የተገልጋይ እርካታን ከፍ ለማድረግ የጎላ ሚና እንዳለው የጠቀሱት አቶ ፍጹም፥ ሠራተኛው በስራ ቦታው ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ከማድረግ አኳያ የደህንነት ካሜራ የተገጠመለት መሆኑን ጠቁመዋል ።
በተጨማሪም የህብረተሰቡን የመሠረተ ልማት ፍላጎት ደረጃ በደረጃ ለማሟላት የማሽነሪዎች ግዥ መፈጸሙን አንስተው፥ የማሽነሪ ግዥው ከተማው ዘመናዊነቱን ጠብቆ በአግባቡ እንዲለማና የመጪውን ጊዜ መሠረተ ልማት ሥራዎች ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል ።
ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በህብረተሰብ ተሳትፎ እየተገነባ የሚገኘው የተጠርጣሪዎች ማረፊያ የምክር ቤት አባላቱ ጎብኝተዋል።
የፖሊስ ተቋሙ ከዚህ ቀደም ለአገልጋዩም ሆነ ለተገልጋዩ ማህበረሰብ ምቹ ያለመሆኑን ያስታወሱት የከተማው ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ደሳለኝ ጩቱሎ፥ ይህንን ለመቀየር ሠላም ወዳድ የሆነውን የህብተሰብ ክፍል በማሳተፍ የተቋሙን ጤናማነት ለመጠበቅ በጥናት ላይ የተመረኮዘ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ተናግረዋል ።
ተቋሙ ከሚያከናውናቸው ተግባራት ባሻገር ለህብረተሰቡ አርአያ የሚሆኑ ስራዎችን መስራቱን የጠቀሱት አዛዡ፥ ከወንጀል መከላከል ጎን ለጎን የተጠርጣሪዎችን ሰብዓዊ መብት ከማስጠበቅና ምቹ የሥራ ቦታን ከመፍጠር አኳያ ከፍተኛ እንቅስቃሴ መደረጉን ነው የገለጹት ።
በልማት ፕሮጀክቶቹ ጉብኝት ላይ የሣውላ ከተማ ከንቲባ ዶ/ር ንጉሴ መኮንንን ጨምሮ የምክር ቤት አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡
ዘጋቢ: አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን
More Stories
ከደን ምንጣሮ የፀዳ ቡና በማምረት አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን እተየሰራ ነው
ክርስቲያን የቡና ግብይትና ሁለገብ የሕብረት ሥራ ማህበር በቡና ጥራት ዙሪያ በልዩ ትኩረት እየሠራ መሆኑን ገለፀ
ደም መለገስ ለተጎዱ ወገኖች ህይወትን መስጠት፣ የአይን ብሌን መለገስ ደግሞ የህይወት ብርሀን መመለስ መሆኑ ተገለፀ